የህብረት ስምምነት በሶስተኛ ወገኖች ላይ ያለው ውጤት


የሰበር መ/ቁ. 39658

ሐምሌ 23 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

ዳኞች ፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

ታፈሰ ይርጋ

ፀጋዬ አስማማው

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች ፡- የሸዋ ጥጥ ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር –

ጠበቃ አበራ ታደሰ ቀረበ

ተጠሪ ፡- አቶ ታከለ ቀፀላ – ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ     ር    ድ

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 263ዐ5 የካቲት 28 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ፍርድና የከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 65949 ሰኔ 29 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

ተጠሪ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በአመልካች ድርጅት የፈረቃ ምርት ሀላፊ መሆኑን በመግለፅ ነሐሴ 25 ቀን 1998 ዓ.ም. የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ አለአግባብ የተከለከልኩ በመሆኑ ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈለኝ በማለት ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በአንድነት ክስ አቅርቧል፡፡ አመልካች በተከሣሽነት ቀርቦ የደመወዝ ጭማሪ ያላደረገ መሆኑን የደመወዝ ጭማሪ አደረገ ቢባል እንኳን በህብረት ስምምነቱ መሠረት ተጠሪ የሥራ መሪ በመሆኑና ደመወዛቸው ከፍተኛ ስለሆነ ለሠራተኞች የተደረገው የኑሮ ውድነት የማቋቋሚያ ድጎማ እንደማይገባቸው ተከራክሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ አመልካች ተጠሪ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሠረት የሚሠሩት ተግባር የሥራ መሪ መሆናቸውን አላስረዳም፡፡ የህብረት ስምምነቱ ከአዋጁ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ የኑሮ መደጎሚያ ነው ያለው ዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው ሠራተኞች ብቻ የተደረገ መሆኑን አላስረዳም ስለዚህ ከነሐሴ 25 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ ያለውን ውዝፍ ደመወዝ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍታብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 337 መሠረት ሠርዞታል፡፡

አመልካች ሀምሌ 28 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ ተጠሪ ላቀረበው ክስ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ጉዳዩ የውል የሥራ ክርክር ስለሆነ በፍርድ ቤት መታየት የሌለበት መሆን ክሱ የይርጋ ጊዜ ያለፈበት መሆኑንና የተጠሪ የሥራ መደብ በግልፅ የሥራ መሪ የሥራ መደብ መሆኑ በህብረት ስምምነቱ የተደነገገ በመሆኑ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ እንደማይችል በማንሣት ተቃውሞናል በአማራጭም ለፍሬ ጉዳዩ ለዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው ሠራተኞች የኑሮ መደጎሚያ ያደረገና ተጠሪን እንደማይመለከት ተከራክረናል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ነው በቦርድ መታየት ያለበት ለሚለው ነጥብና በይርጋው ጉዳይ ብይን ሣይሰጥ ያለፈ በመሆኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈፅሟል፡፡ የፍሬ ጉዳዩ ክርክራችንንም አላግባብ አልፎብናል ስለዚህ የበታች ፍ/ቤቶች የፈፀሙት መሠረታዊ የህግ ስህተት በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት አመልክቷል፡፡

ተጠሪ በበኩሉ መጋቢት 1ዐ ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. በሰጠው መልስ እኔ ያቀረብኩት ጥያቄ የማየት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ አመልካች የኑሮ መደጎሚያ ነው ያደረግሁት የሚል መከራከሪያ እያነሣ ያለው የደመወዝ ጭማሪ ካደረገ ከስድስት ወር በኋላ ነው፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ የሰጠው የህብረት ስምምነቱን አስቀርቦ ከመረመረ በኋላ በመሆኑና መሠረታዊ የህግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ውድቅ አድርጎ እንዲያሰናብተኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡

አመልካች በበኩሉ በድርጅቱ የህብረት ስምምነት መሠረት በሥራ መሪነታቸው ጭማሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ከተጠሪ ጋር ተመሣሣይ የሥራ መደብ ላይ የተመደበ ሠራተኛ ክስ አቅርቦ ቦርዱ የሥራ መሪ መሆኑ ተወስኗል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ የሥራ መሪ በመሆናቸው ያቀረቡት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ውድቅ ሆኖ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰሩት መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዲታረምልኝ በማለት የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም መዝገቡን መርምረናል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤት ክስ ሲያቀርቡ የፈረቀ ምርት ሀላፊ መሆናቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ ተጠሪ በክሳቸው የገለፁት እና የተመደቡበት የኃላፊነት ቦታ በአመልካችና በአመልካች ድርጅት ያሉ ሠራተኞች ባቋቋሙት የሠራተኛ ማህበር ድርድር ባፀደቀው ሶስተኛው የህብረት ስምምነት በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 6 /ሐ/ የሥራ መሪ መሆናቸው በግልፅ ተደንግጓል፡፡

ተጠሪ የሥራ መሪ መሆናቸው አመልካችና የሠራተኛ ማህበሩ ባደረጉት ድርድር በፀደቀው ሶስተኛው የሕብረት ስምምነት በግልፅ በተደነገገበት ሁኔታ የበታች ፍርድ ቤቶች ህብረት ስምምነቱን ድንጋጌ ወደ ጎን በመተው ተጠሪ ሠራተኛ ነው በማለት የደረሱበት መደምደሚያና ለተጠሪ ደመወዝ እንዲጨመራቸው የሰጡት ውሣኔ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/2/ሐ እንደተሻሻለ የሚተላለፍ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ ተጠሪ የሥራ መሪ በመሆናቸው ጉዳያቸው በአሠሪና ሠራተኛ የሥራ ክርክር ችሎት ማየት የሥረ ነገር ስልጣን የሌለው ሲሆን በጉዳዩ ተፈፃሚነት የሚኖረው ህግም በፍታብሔር ህጉና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎች ስለ ሥራ መሪ የተደነገጉት ናቸው፡፡

ስለሆነም ከላይ የጠቀስነውን የህግ ድንጋጌ በመተላለፍ ተጠሪ ሠራተኛ ናቸው በማለት አመልካች ውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ እንዲከፍላቸው የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት ወስነናል፡፡

ው    ሣ     ኔ

  1. የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሽሯል፡፡
  2. የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ የሥራ ክርክር ችሎት እና ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የላቸውም ብለናል፡፡
  3. ወጭና ኪሣራ ለየራሣቸው ይቻቻሉ፡፡

ይህ ፍርድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሙሉ ድምፅ ተሰጠ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ጽ/ሽ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s