የስራ ዝውውርና የስራ ውሉን ለማሻሻል አሰሪው ስላለው ስልጣን


የሰበር መ/ቁ 44044

ሐምሌ 29 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

በላቸው አንሺሶ

ሱልጣን አባተማም

 

አመልካች፡- አራዳ ክ/ከተማ ቀበሌ 01/02/11 መዝናኛ ክበብ

ቢያ አባዳራ (ነገረ ፈጅ) ቀረበ

ተጠሪ፡- ወ/ሮ ሙላትዋ ባዬ ቀረበች

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

የሰበር አቤቱታው የቀረበው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ 26924 ታሕሣሥ 13 ቀን 2001 ዓ.ም ተሰጥቶ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 75706 የካቲት 20 ቀን 2001 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ በፀናው ፍርድ ላይ ነው፡፡ ከመዝገቡ እንደሚታየው ክርክሩ የተጀመረው ተጠሪ ቀደም ሲል ተመድቤ እሠራበት ከነበረው የገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ያለአግባብ ወደሌላ የሥራ መደብ ተዛውሬ እንድሠራ የተደረገ በመሆኑ ዝውውሩ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ወደቀድሞ ምድብ ሥራዬ እንድመለስ ይወሰንልኝ በማለት በአመልካች ላይ ክስ በመመስረትዋ ነው፡፡

አመልካች በበኩሉ ተጠሪ በተባለው ቦታ ላይ ተመድባ ትሠራ እንደነበር ያመነ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ግን ቦታው ከስዋ በፊት ተመድቦ ይሠራበት ለነበረው ግለሰብ በፍ/ቤት በተሰጠ ውሳኔ የተሰጠ በመሆኑ ተጠሪን ማዛወር የግድ እንደሆነበት በመግለጽ ተከራክሮአል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ያስተናገደው ፍ/ቤት ክርክሩን ከመረመረ በኋላ ተጠሪ በገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ላይ ተመድባ መሥራት ትቀጥል በማለት ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት ፍ/ቤትም ውሳኔው ጉድለት የለበትም በማለት ይግባኙን ሰርዞአል፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

በበኩላችንም አመልካች የካቲት 27 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈው ማመልከቻ ያቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ ክርክሩ የተሰማው አመልካች በተጠሪ ላይ የወሰደው የሥራ መደብ ለውጥ /ዝውውር/ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ መወሰኑ አግባብ ነው ወይ? በሚለው ጭብጥ ላይ በመመስረት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የተደረገውን ክርክር ከሕጉ እና አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡

ከክርክሩ እንደሚታየው ተጠሪ ከአመልካች ጋር ባላት የሥራ ውል መሠረት ተቀጣሪ ሠራተኛ ናት፡፡ አመልካች ቀጣሪ በመሆኑ የሥራው መሪ እሱ ነው፡፡ በሥራ መሪነቱ ሕጉን ተከትሎ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተጠሪ የመፈጸም ግዴታ እንዳለባትም ይታወቃል (የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ 377/96 አንቀጽ 13(2))፡፡ አመልካች በአሠሪነቱ ሊወስዳቸው ከሚችሉት እርምጃዎች ወይም ሊሰጣቸው ከሚችሉት ትዕዛዞች አንዱ ሠራተኛውን ለሥራው አመቺ ነው ባለው የሥራ መደብ አዘዋውሮ የማሠራት ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ እንደሚታየው አመልካች ተጠሪን ከገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ወደ ፈረቃ አስተባባሪነት የሥራ መደብ አዛውሮ መድቦአል፡፡ ይህ ሲያደርግም በገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ላይ ታገኝ የነበረውን ደመወዝ አልቀነሰም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠሪ በገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ላይ ተመድባ የነበረው በቦታው ላይ የነበረው ሠራተኛ በሥራ ውል መቋረጥ ምክንያት በፍ/ቤት በክርክር ላይ ስለነበረ ነው፡፡ በኋላ ግን ሠራተኛው በፍ/ቤት ውሳኔ ወደሥራው እንዲመለስ ስለመደረጉ በአመልካች ክርክር ተገልጾአል፡፡ የሥር ፍ/ቤትም ይህን ፍሬ ነገር በውሳኔው ላይ የመዘገበ ቢሆንም፤ ሊቀበለው ግን አልቻለም፡፡ ይሁንና በኋላ የተገለጸው ሁኔታ ይኑርም አይኑርም አዘዋውሮ የማሠራት ስልጣን የአሠሪው እስከሆነ ድረስ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ሲጠቃለል አመልካች ተጠሪን ከነበረችበት የገንዘብ ያዥነት ሥራ ወደ ፈረቃ አስተባባሪነት ሥራ ያዛወረው በአሠሪነቱ ባለው ስልጣን በመሆኑ ከሕግ አግባብ ውጪ የወሰደው እርምጃ ነው የሚባልበት ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ችለናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ 26924 ታሕሣሥ 13 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 75706 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 348(1) መሠረት ተሽረዋል፡፡
  2. ተጠሪ ወደገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ የምትመለስበት ምክንያት የለም ብለናል፡፡
  3. ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s