ስንብትና የማስረዳት ጫና


የሰ/መ/ቁ 43610

ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- 1. ዓብዱልቃድር መሐመድ

2. ሐጉስ ወልዱ

3. ሒሩት መለሠ

4. በላቸው አንሺሶ

5. ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡– ናይኮን ኃ/የተ/የግ/ማ – ጠ/ማስተዋል ሐብታሙ

ተጠሪ፡- አቶ ሠለሞን ተሠማ – ቀረቡ

ፍ ር ድ

ለሠበር አቤቱታ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የጀመረው ተጠሪ በፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ነው፡፡ በክሣቸውም ያለአግባብ ከስራ ስለተሠናበቱ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ካልሆነ ህጉ የሚፈቅደው ክፍያዎች እንዲከፈሏቸው ጠይቀዋል፡፡ አመልካችም ድርጅቱ ሣይሆን ከስራ ያሠናበታቸው በራሣቸው ፈቃድ ከሥራ በመቅረታቸው ነው ውሉ የተቋረጠው በማለት የተከራከረ ሲሆን ፍ/ቤቱ ተጠሪ በራሳቸው ፍቃድ ነው ስራውን የለቀቁት በማለት ክሱን ሣይቀበለው ቀርቷል፡፡

ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር ተሠኝተው ይግባኛቸውን ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ ስንብቱ ህገ-ወጥ ነው በማለት የ7 ወር ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ወስኗል፡፡

የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሣኔ ላይ ነው፡፡ ችሎቱም አቤቱታው ለሠበር ችሎት ያስቀርባል በማለቱ ግራ ቀኙ ቀርበው የቃል ክርክራቸው ተሠምቷል፡፡ መዝገቡም እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡

ተጠሪ በስር ፍ/ቤት በመሠረቱት ክስ የአመልካች ድርጅት ባለቤት ስልክ ደውለው ከስራ ያሠናበቷቸው መሆኑን ነው የገለፁት በመሆኑም በዚህ መልኩ የስራ ውላቸው መቋረጡን በቅድሚያ የማስረዳት ሸክም ያለባቸው ተጠሪ ናቸው፡፡ ይህንንም ለማስረዳት ተጠሪ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡ በተጠሪ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ግን በተጠሪ የክስ አቀራረብ መሰረት እንዳላስረዱ የሥር ፍ/ቤት አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ በስልክ የስራ ውላቸው መቋረጡን አላስረዱም ማለት ነው፡፡ ይግባኝ ሠሚው ፍ/ቤትም ቢሆን ስልክ ተደውሎ የተጠሪ የሥራ ውል መቋረጡን ተጠሪ አስረድተዋል አላለም፡፡ ይህም ተጠሪ ክስ የመሠረቱበትን ጉዳይ አለማስረዳታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ይልቁንም ተጠሪ በሥር ፍ/ቤት ያቀረቧቸው 3ኛ ምስክር የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ ስልክ ላይ ደውለው የስራ ቦታቸው በመቀየሩ ወደ ተቀየሩበት ቦታ እንዲሄዱና ወደ ቀድሞ ስራ ቦታቸው እንዳይገቡ መከልከላቸውን ነው ያስረዱት ይህ ደግሞ የሚያስረዳው ለተጠሪ በስልክ የተነገራቸው የስራ ቦታቸው መቀየሩን እንጂ የሥራ ውላቸው መቋረጡን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ተጠሪ በስልክ የተገለፀላቸው የሥራ ቦታ ሄደው እንዳይገቡ ወይም እንዳይሠሩ መከልከላቸውን ያቀረቡት ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ በአጠቃላይ ተጠሪ አመልካች ከሥራ ያሠናበታቸው መሆኑን ያለባቸውን የማስረዳት ሸክም ሣይወጡ ይግባኝ ሠሚው ፍ/ቤት የተጠሪ የሥራ ስንብት ህገ-ወጥ ነው በማለት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 70728 ታህሣስ 28/2001 ዓ.ም የሠጠው ውሣኔ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 31913 ሐምሌ 18 ቀን 2000 ዓ.ም የሠጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡
  3. የተጠሪ የሥራ ውላቸው በህገ-ወጥ መንገድ የተቋረጠ መሆኑን ገልፀው ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት የለውም ብለናል፡፡
  4. ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment