የአስተዳደር መስሪያቤቶች ስልጣን


የሰ/መ/ቁ. 31171

ጥቅምት 27 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

ዳኞች፡-አብዱልቃድር መሐመድ

ሒሩት መለሠ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

ዓሊመሐመድ

አመልካች፡- አብልሃሚድ የሱፍ – ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡- የምሥራቅ ቀጠና ጉምሩክ ጽ/ቤት – ነ/ፈጅ አጥሉ ሀብታሙ ቀረቡ፡፡

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ
ጉዳዩ የንብረት ግምት ጥያቄ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረውም የአሁኑ አመልካች ጥር ዐ5 ቀን 1997 ዓ.ም. በተፃፈ ማመልከቻ በአወዳይ ከተማ ውስጥ የንግድ ስራ በሕጋዊ መንገድ እያካሄዱ ባሉበት ሁኔታ ተጠሪ የጉምሩክ ፖሊስ እና ሌላ የፖሊስ ኃይል በማስተባበር የሱቁን ቁልፍ በመስበር በሱቁ ውስጥ የነበረውን የንግድ ዕቃ በሙሉ አውጥተው በጭነት መኪና ጭነው በመውሰድ በተጠሪ መጋዘን ማስገባቱን፣ የተወሰዱ ንብረቶችን ተጠሪ ይመለስላቸው ዘንድ ጥያቄ ቢያቀርቡም ተጠሪ ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘቱን፣ የተወሰዱባቸው በሱቁ ውስጥ የነበሩት ንብረቶች ዓይነታቸውና ብዛታቸው እንዲሁም ግምታቸው ምን ያሕል እንደሆነ በመዘርዝር ግምቱ ብር 5ዐዐ,000.00 /አምስት መቶ ሺህ ብር/ የሆነ ንብረት እንዲመለስላቸው፣ ንብረቶቹ ተሸጠው ይገኝ የነበረውን ትርፍ እንዲከፍሉ፣ ንብረቶቹን ካልመለሱ ግምቱን እንዲከፍሉ እና የተለያዩ ወጪዎችንም ጭምር እንዲከፍሉ ይወስንላቸው ዘንድ የአሁኑን ተጠሪ 1ኛ ተከሣሽ ሌሎች ሁለት የፖሊስ አባላትን 2ኛ እና 3ኛ ተከሣሽ በማድረግ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመሠረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪም በአመልካች በኩል ተዘርዝረው የቀረቡትን የንብረት ዓይነቶች በፍ/ቤት የብርበራ ትዕዛዝና በሕብረተሰቡ ትብብር የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር እና ለመያዝ በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የወሠደ መሆኑን በመግለጽ ተጠያቂነት እንደሌለበት፣ በአመልካች በኩል የቀረቡት ማስረጃዎችም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑንና ሌሎች የመከራከሪያ ነጥቦችን በማንሣት ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት በ27/ዐ7/97 ዓ.ም. በተፃፈ ማመልከቻ ተከራክሯል፡፡ ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ምስክሮችን ከሰማ በኋላ የተጠሪን መከራከሪያ ነጥቦችን ውድቅ በማድረግ ተጠሪንና በስር 2ኛ ተከሣሽ የነበሩትን የጉምሩክ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊን ለድርጊቱ አላፊ አድርጎ የአመልካችን ንብረት በክሱ በቀረበው ዝርዝር መሠረት በእራሣቸው ወጪ ከወሰዱበት ቦታ ከአመልካች ሱቅ እንዲመልሱ ይህን ካልፈፀሙ ግምቱን ብር 5ዐዐ,000.00 /አምስት መቶ ሺህ ብር/ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ፣ ወጪና ኪሣራ ዝርዝር የማቅረብ መብት ለአመልካች በመጠበቅ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ የአሁኑ ተጠሪ ባለመስማማት ይግባኙን ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርቦ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የተለያዩ ምክንያቶችን ከዘረዘረ በኋላ በአሁኑ አመልካች በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ንብረቶቹ የአመልካቹ ለመሆናቸው ለማስረዳት፣ ለማረጋገጥ የማይችሉ አጥጋቢና አሣማኝ አይደሉም ወደሚል ድምዳሜ በመድረስ የስር ፍ/ቤትን ውሣኔ በመሻር ተጠሪን በነፃ በማሠናበት ወስኗል፡፡ ከዚህም በኋላ የአሁኑ አመልካች ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነው ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለበት ያሉባቸውን ምክንያቶች ሰኔ ዐ3 ቀን 1999 ዓ.ም. በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ዘርዝረዋል፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም ለሰበር ችሎቱም ቀርቦ ሊታይ ይገባል በመባሉ ተጠሪ ጥር ዐ1 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ ማመልከቻ መልሱን አቅርቧል፡፡ አመልካችም በተጠሪው መልስ የካቲት ዐ6 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ ማመልከቻ የመልስ መልሣቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልካ ከላይ የተገለፀው ሲሆን የግራ ቀኙን የጽሁፍ ክርክር የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ጭብጥ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን ንብረቶች ተጠሪ የወሰዳቸው ከአመልካች ሱቅ ነው እየተባለ ንብረቶቹ የአመልካች መሆናቸው አልተረጋገጠም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በክርክሩ ሂደት ለክርክሩ ምክንያት የሆኑት ንብረቶች ተጠሪ የወሰዳቸው ከአመልካች ሱቅ መሆኑ፣ አመልካች ሱቁ ቁጥር የለውም ቢባልም በብር 1ዐ,ዐዐዐ.00 /አስር ሺህ/ ካፒታል ልዩ ልዩ ዕቃዎችንና ሸቀጦችን ለመነገድ ከተገቢው አካል ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ ከመልካች ሱቅ ንብረቶችን መወሰዱን ሣይክድ ተግባሩን የፈፀመው በሕጉ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሆኑንና ንብረቹ የአመልካች ስለመሆናቸው ተቀባይነት ያለው ማስረጃ አለመቅረቡን በመጥቀስ የሚከራከር መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የተጠሪ መ/ቤት ስልጣንና ተግባር በአዋጅ ቁጥር 6ዐ/1989 በአንቀጽ 6 እና 58 ስር ተዘርዝሯል፡፡ እነዚህ የአዋጁ ድንጋጌዎች የሚያሣዩት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የጉምሩክ ባለስልጣንና ሹም የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባራት በዝርዝር መቀመጣቸውን ነው፡፡ የጉምሩክን ባለስልጣንን እንደገና ለማቋቋምና አሠራሩን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 368/1995 ደግሞ ኮንትሮባንድ ማለት ሕጎችንና ሕግ መሠረት የወጡ መመሪያዎች በመተላለፍ ወደ ጉምሩክ ክልል ዕቃወችን በማስገባት ወይም ከጉምሩክ ክልል በማስወጣት በሕጋዊ መንገድ የመጡትን በሕገ ወጥ መንገድ መልሶ ማስባት፣ መያዝ፣ ማከማቸት፣ ማዘዋወር ማስተላለፍ እንዲገቡ ወይም እንዲወጡ ለማድረግ መሞከር እና ከእንደዚህ ያሉ ድርጊቶች መተባበርን እንደሚጨምር በአንቀጽ 2/28/ ትርጓሜ ሠጥቶበታል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ተጠሪ ተግባሩን ሕጋዊ ነው ብሎ ሲከራከር በተለይም መሠረት ያደረጋቸው የአዋድ ቁጥር 6ዐ/89 አንቀጸ 6/5/ እና 58/1/ለ/ ድንጋጌዎችን ነው፡፡ የአንቀጽ 6/5/ ሙሉ ይዘቱ ሲታይም ባለስልጣኑ “በኮንትሮባንድ ወደ አገር የሚገቡትን ወይም ከአገር የሚወጡትን ዕቃዎች እንቅስቀሴ ይቆጣጠራል፣ ይከላከላል፣ በዚሁ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ዕቃዎችንና ማጓጓዣዎችን ይይዛል፣ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል” በማለት ሲደነግግ አንቀጽ 58/1/ለ/ ደግሞ ወደ አገር እንዳይገቡ ወይም ከገር እንይወጡ የተከለከሉ ገደብ የተደረገባቸው ወይም ቀረጥ እንዳይከፈልባቸው በማሠብ የተደበቁ ዕቃዎች በፍተሻ ሲገኙ ዕቃዎችን የመያዝ እንዲሁም እንደሁኔታው ማጓጓዣውን የማጓጓዣውን ኃላፊ ወይም የዕቃውን ባለቤት ይዞ ለምርመራ በጥበቃ ሥር የማቆየት ስልጣንና ኃላፊነት የጉምሩክ ሹም ያለው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ የሚቻለው የጉምሩክ ባለስልጣን በኮንትሮባንዱ ወደ አገር የሚገቡትን ወይም ከአገር የሚወጡትን ዕቃዎች እንቅስቃሴ የመቆጣጠር የሚንቀሳቀሱ ዕቃዎችንና ማጓጓዣዎችን የመያዝና አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ በሕገ ወጥ መንገድ መገልገያ የሆኑ መጓጓዣዎችን ጭምር ይዞ ለምርመራ በጥበቃ ስር የማየቆት ስልጣን በሕጉ የተሰጠው መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት የሚያከናውነው ግን ኮንትሮባንድ ተብሎ በሕግ የተሰጠው ትርጓሜ ተሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ ማንኛውምን የዕቃ እንቅስቃሴ ኮንትሮባንድ ስለመሆኑ አሣማኝ እና በቂ ምክንያት ሣይኖረው ባለስልጣኑ መ/ቤት እንዲይዝና እንዲቆጣጠር ሕጉ ስልጣን ሠጥቶታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የአንድን ሰው መኖሪያ ቤት ወይም የንግድ ቤት የኮንትሮባንድ ዕቃ የተደበቀበት ስለመሆኑም ባስልጣኑ ጥርጣሬ ሲኖረው ሰብሮ በመግባት ዕቃዎችን እንዲይዝ ሕጉ ይፈቅድለታል ወደሚለው ድምዳሜ መድረስ በኢ/ፌ/ዲ/ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 26/1/ ስር ጥበቃ የተደረገውን የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት ዋስትና የሚያሣጣ ነው፡፡ በመሆኑም የጉምሩክ ባለስልጣን ተግባር ሕጋዊ ነው ሊባለ የሚችለው በሕጉ መሠረት ሊሟሉ የሚችሉትን ሁኔታዎች አሟልቶ ሲገኝ ብቻ እንጂ በማንኛውም ጥርጣሬና ምክንያት ሁሉ የግለሰብን ንብረት በመያዝ ሊሆን አይችልም፡፡
እጃችን ወዳለው ጉዳይ ስንመለስ በተጠሪ ተወሰዱ የተባሉ ንብረቶች በአመልካች ይዞታ ስር የነበሩ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ. 1193/1/ ሥር በተደነገገው አኳኋን አመልካች የንብረቶቹ ባለሀብት መሆናቸውን ሕጉ ግምት ይወስዳል፡፡ ይህ ሕጋዊ ግምት ተቃራኒ ማስረጃ ለማቅረብ ሊፈርስ የሚችል ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁ. 1193/2/ ድንጋጌ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለይዞታነት የሰው ወይም የጽሁፍ ማስረጃ በማቅረብ ካልፈረሰ በቀር ባለይዞታው የንብረቱ ሕጋዊ ባለሀብት ስለመሆኑ ግምት የሚወሰድበት እና ባሀብትነትን የማስረዳት /proof of ownership/ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ተጠሪ ንብረቶቹ የአመልካች አለመሆናቸውንና በኮንትሮባንድ ስራ ወደ አመልካች እጅ የገቡ ናቸው በማለት የሚከራከረው በአመልካች በኩል የቀረቡት ደረሰኞችን የንግድ ፈቃድ ካፒታል መጠንና የንግድ ዓይነትን መሠረት በማድረግ እንጂ ያላግባብ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ የተገኘ መሆኑን በማስረዳት አይደለም፡፡ በተለይም ተጠሪ የአመልካችን ንብረትቶችን ያዝኩ የሚለው በፍ/ቤት የብርበራ ትዕዛዝ ቢሆንም ይኸው ትዕዛዝ ብርበራው ከተፈፀመ በኋላ ፍ/ቤቱ ማንሣቱ መረጋገጡ የተጠሪን ተግባር ሕጋዊነት ቀሪ ማድረጉን ከሚጠቁም በስተቀር አመልካች የንብረቶቹ ሕጋዊ ባለቤት አለመሆናቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ በመሆኑም ተጠሪ የአመልካች ንብረቶች ኮንትሮባንድ ስለመሆናቸው አላስረዳም፡፡ በአንፃሩ ንብረቶችን በይዞታ በማድረግ ይጠቀሙባቸው የነበረ አለመሆኑ አመልካች ያረጋገጡ በመሆኑ በማስረጃ ምዘና መርህ ረገድ ሲታይ የተሻለ ማስረጃ ያቀረቡትም አመልካች ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ ያቀረቡትን ማስረጃዎች የመዘነበት መንገድ በፍ/ሕ/ቁ. 1193 /1/እና /2/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ባላገናዘበ ሁኔታ ነው፡፡
ስለሆነም የአመልካች ዕቃዎች ከአመልካች ሱቅ መወሰዳቸው ተረጋግጦ እያለና ንብረቶቹ በኮንትሮባንድ ተግባር ወደ አመልካች ዕጅ የገቡ መሆናቸውን ተጠሪ ባላስረዳበት ሁኔታ ተጠሪ ተጠያቂነት የለበትም መባሉ ባግባቡ ሆኖ ስላልተገኘ ውሣኔ የፍ/ሕ/ቁ 1193፣ አዋጅ ቁ. 6ዐ/1989 አንቀጽ 6/5/ እና 58/1/ለ/ እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 368/1995 አንቀጽ 2/28/ ድንጋጌዎችን መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተጠሪ በሕገወጥ መንገድ የአመልካችን ንብረቶችን መወሰዱ በበቂ ሁኔታ ስለተረጋገጠ በፍ/ሕ/ቁ. 2ዐ27፣ 2ዐ35 እና 2ዐ54 ስር በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት አላፊ ሊባል የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የካሣውን መጠን በተመለከተም አመልካች ከተጠየቁት ዳኝነትና ከአቀረቡት ማስረጃ እንዲሁም ከፍ/ሕ/ቁ. 2118 አኳያ ሲታይ ተጠሪ ተዘርዝረው የቀረቡትን ንብረቶች በዓይነት እንዲመልስ ወይም ግምታቸውን እንዲከፍል መወሰኑ ፍትሐዊነት ያለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች የሚከተለው ተወስኗል፡፡

ው ሣ ኔ
1. በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 32974 ሰኔ ዐ8 ቀን 1998 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 26383 መጋቢት 19 ቀን 1999 ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡
2. የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. ዐ2282 ሐምሌ ዐ7 ቀን 1997 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት ፀንቷል፡፡ ይፃፍ፡፡
3. ተጠሪ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን ንብረቶች ከአመልካች ይዞታ ያላግባብ የወሰዳቸው መሆኑ ስለተረጋገጠ ንብረቶቹን በዓይነት እንዲመልስ ወይም ግምታቸውን ብር 5ዐዐ,000.00 /አምስት መቶ ሺህ ብር/ ሊከፍል ይገባል ብለናል፡፡
4. በዚህ የሰበር ችሎት በተደረገው ክርክር ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
5. መዝገቡ ያለቀለት ስለሆነ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ነ/ዓ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s