በፖሊስ ፊት የተሰጠ ቃል የማስረጃ ዋጋ


የሰበር መ/ቁ 44267

ግንቦት 23 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- ሂሩት መለሠ

ተሻገር ገ/ስላሴ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- አቶ ፍሰሐ ተክሉ – ቀረቡ

ተጠሪ፡- የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ – አልቀረቡም

በዚህ መዝገብ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ እና በመ.ቁ 53495 የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ጐን ለጐን በመመርመር ቀጥሎ የተመለከተውን ፍርድ ሠጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

ይህ ጉዳይ የወንጀል ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ተጠሪ ዐቃቤ ሕግ በዚህ መዝገብ አመልካች የሆኑትን 3ኛ ተከሳሽ በመ.ቁ 53495 አመልካች የሆኑትን ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ በማድረግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32(1) (ሀ)(ለ) እና 671(1)(ለ)(ሐ) የተመለከተውን በመተላለፍ ካልተያዘው ግብረአበራቸው ጋር በመሆን ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስበው የአሜሪካን ዶላር ይዘው ከሚዘዋወሩ ነጋዴዎች ላይ የያዙትን ዶላር ለመዝረፍ በመስማማት በ6/12/98 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡30 በሚሆንበት ጊዜ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ የአሜሪካን ዶላር ይዘው የነበሩትን የግል ተበዳይ አቶ ደስታዓለም መብራሀቶምን እና አብረው የነበሩትን አቶ ገብሬ ገብረሊባኖስን 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የግል ተበዳዮችን ለቀሩት ተከሳሾች ጠቁመው ሲያሳዩ 1ኛ፣ 2ኛ እና ያልተያዘው ተከሳሾች የግል ተበዳዩንና አብረዋቸው የነበሩትን እኛ የፖሊስ አባሎች ነን እናንተ ሕገወጥ ንግድ በማካሄድ ከጅጅጋ መሣሪያ ታመላልሳላችሁ በማለት በ2ኛ ተከሳሽ ሲሽከረከር በነበረው ንብረትነቱ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሆነው የሠ.ቁ 4-04619 ላንድክሩዘር መኪና ውስጥ አስገድደው በማስገባት በሽጉጥ እያስፈራሩ መከላከል እንዳይችሉ ካደረጓቸው በኋላ ከግል ተበዳይ ላይ 12,850 የአሜሪካን ዶላር ዘርፈው የወሰዱ በመሆኑ በፈጸሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው፡፡

የአሁን አመልካቾችም ቀርበው ክሱ ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ ክሱን እንደማይቃወሙ፣ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙና ጥፋተኛ አይደለንም በማለት ክደው ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግም የሰውና የጽሁፍ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግን ክስና ማስረጃ መርምሮ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በክሱ ጊዜ ተጠቅሶ በቀረበባቸው ድንጋጌ መሠረት የወንጀሉን ድርጊት መፈጸማቸው በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው ስለሆነ በዚሁ ድንጋጌ ሥር እንዲከላከሉ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የአሁን አመልካቾችን በተመለከተ የፈጸሙት ተግባር በወ/ሕ/ቁጥር 32(1)(ሀ)ለ እና 671(1)(ሐ) ሥር የሚሸፈን በመሆኑ በዚሁ ድንጋጌ ሥር እንዲከላከሉ በማለት ብይን ሠጥቷል፡፡

ከዚህ በኋላም አመልካቾች የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 27(2) መሠረት የሰጠነው የተከሳሽነት ቃል በምርመራ ወቅት በደረሰብን ከፍተኛ ድብደባና ተጽዕኖ የተሰጠ የዕምነት ቃል እንደሆነ ወንጀሉ ተሰራ በተባለበት ጊዜም በሥፍራው ያልነበርን ስለመሆናችን ያስረዱልናል በማለት ጭብጥ አስይዘው የመከላከያ ምስክሮቻቸው የተሰሙ ሲሆን በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 35 መሠረትም ፍርድ ቤት ቀርበን የሰጠነው ቃል ወንጀሉን እንዳልፈጸምን በመግለጽ ስለሆነ በማስረጃነት ቀርቦ ይታይልን በማለት አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሁሉም ተከሳሾች ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው በመከላከያ ማስረጃ ያላስተባበሉ ስለሆነ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በክሱ ጊዜ ተጠቅሶ በቀረበባቸው ድንጋጌ ሥር 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ ይከላከሉ በተባሉበት ድነጋጌ ሥር ጥፋተኛ ናቸው በማለት የጥፋተኛነት ውሳኔ ሠጥቷል፡፡

ቅጣቱን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ በቅጣት አወሳሰን ረገድ በሕጉ ላይ የተቀመጡትን መርሆች መሠረት ማድረጉን በውሳኔው ላይ አስፍሮ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችን የአሁን አመልካቾችን በ6/ስድስት/ ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡና ለ2 ዓመትም ከሕዝባዊ መብቶቻቸው እንዲሻሩ ተጨማሪ ቅጣት ወስኖባቸዋል፡፡

አመልካቾች ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም የይግባኝ ቅሬታ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በየበኩላቸው አቅርበው ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ የሥር ፍ/ቤት የሰጠው የጥፋተኛነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም በማለት በወንጀለኛ መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195(1) መሠረት አጽንቶታል፡፡

የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህንኑ በመቃወም ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ አመልካቾች ጥፋተኛ የተባሉበት አግባብ ከወንጀል ጉዳይ የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል አንጻር እንደዚሁም የማስረጃው አመዛዘን መርህን የተከተለ ስለመሆኑ ተገቢነቱን ለማጣራት ለሰበር ቀርቦ መታየት የሚገባው መሆኑን በማለት በማመኑ አቤቱታው ለሰበር እንዲቀርብ አድርጎ ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡

በአጠቃላይ የጉዳዩ ይዘት ከፍ ብሎ የተመለከተው ሲሆን አቤቱታው ለሰበር ይቅረብ ከተባለበት ነጥብ አኳያ በበኩላችን ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በክሱ ላይ በተጠቀሰው አኳኋን የግል ተበዳይን ለቀሪዎቹ ተከሳሾች ጠቁመው ወንጀሉ የተፈጸመ ስለመሆኑ በዐቃቤ ሕግ ቀጥተኛ ምስክር የተነገረ ባይሆንም ነገር ግን በሁለቱም ፍ/ቤቶች የተረጋገጠው የዐ/ሕግ ምስክሮች ቃል ተጠቃሎ ሲታይ ወንጀሉን በተለያየ የተሳትፎ ደረጃ ለመፈጸም በሁሉም ተከሳሾች መካከል ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላም ለፖሊስ ጥቆማ ደርሶ ፖሊስ ባደረገው ክትትል 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ካልተያዘው ገብረአበራቸው ጋር በመሆን የግል ተበዳዩን አስፈራርተውበታል የተባለው እጀታው ቀይ የሆነ ማካሮቭ ሸጉጥ 3ኛ ተከሳሽ ሲያዝ ከእሱ እጅ እንደተያዘ መረጋገጡን ተገንዝበናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አመልካቾችን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 27(2) መሠረት የሰጡት የተከሳሽነት ቃል በዐቃቤ ሕግ ማስረጃነት ለፍ/ቤት የቀረበ ሲሆን አመልካቾች ወንጀሉን መፈጸማቸውን በዝርዝር በማመን የዕምነት ቃላቸውን እንደሰጡ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይሄው የዕምነት ቃላቸውም በነጻ ፈቃዳቸው የተሰጠ ስለመሆኑ የምሰክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ ከነበሩት ምስክሮች መካከል የተወሰኑት ፍ/ቤት ቀርበው ተከሳሾች በነጻ ፈቃዳቸው የተከሳሽነት ቃላቸውን እንደሰጡ አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩልም አመልካቾች ተጠሪ ዐቃቤ ሕግ ላገኛቸው አልቻልኩም ያላቸው ምሰክሮቹ ለፖሊስ የሰጡት የምስክርነት ቃል ፍ/ቤቱ ተቀብሎ ለውሳኔው መሠረት ማድረጉ ሕጋዊነት የጎደለው ነው በማለት በሰበር አቤቱታቸው ያቀረቡትን ቅሬታ እንደመረመርነው አንድ ምስክር በተከሳሹ ላይ የምስክርነት ቃል በሚሰጥበት ወቅት ተከሳሹ ምስክሩን በመጠየቅ የምስክርነት ቃሉ በሕግ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ ከጉዳዩ ጋርም አግባብነት ያለው ስለመሆኑና በአጠቃላይም የምስክርነት ቃሉ ተዓማኒነት ያለው መሆኑን በተመለከተ ምስክሩን በዚህ ረገድ የመፋለም መብት /The Right to confront a witness/ በሕገ መንግስት ደረጃ ጭምር የተረጋገጠ የምስክሩ መብት ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ጉዳይ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀርቦ የተመለከተው አመልካቾች የተከሳሽነት ቃላቸውን ሲሰጡ ያለምንም ተጽዕኖ እንደነበር ያስረዳሉ የተባሉ ምስክሮችን እንደመሆኑ መጠን የእነዚህ ምስክሮች ቃል አመልካቾች በነጻ ፈቃዳቸው የዕምነት ቃል መስጠት አለመስጠታቸውን ከሚያስገነዝብና በዕምነት ቃሉ ላይ ብቻ የሚመሰረት ስለሚሆን የአመልካቾችን ምስክርን የመፋለም መብት የሚጋፋ አይሆንም፡፡

ስለሆነም አመልካቾች ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በማስረጃ ተረጋግጧል በማለት እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱ ጉድለት የሌለበት ሲሆን እንዲከላከሉ ብይን ከተሰጠ በኋላም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 27(2) መሠረት የሰጡት ቃል በተጽዕኖ የተገኘ ስለመሆኑና ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ጊዜ ሌላ አካባቢ እንደነበሩ በመግለጽ ጭብጥ አስይዘው የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የመከላከያ መስክሮቻቸው ቃል ተመዝኖ ዕርስ በርሱ የማይጣጣም ስለመሆኑና የዐ/ሕግን ማስረጃ የማስተባበል አቅም እንደሌለው የሥር ፍ/ቤቶች ማረጋገጣቸውን ተገንዝበናል፡፡ የተከሳሾች መከላከያ ምስክሮች ቃል ወጥነት ያለው መሆን አለመሆኑ በፍሬ ነገር ላይ የተመሠረተና የሕግ ትርጉም የሚያሻው ባለመሆኑ ይህ ሰበር ችሎት ተመልሶ የሚያጣራው አይሆንም፡፡

ከዚህም አንጻር የሥር ፍ/ቤቶች አመልካቾች ጥፋተኛ ናቸው በማለት የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ቅጣቱን በተመለከተም ሕጉ ስለ ቅጣት አወሳሰን ያስቀመጣቸውን መርሆች በሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መንፀባረቁን ስለተረዳን በዚህ ረገድም የሕግ ስህተት የተፈጸመ ሆኖ አላገኘውም፡፡

 

ው ሣ ኔ

  1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 55048 በ16/11/2000 ዓ.ም የሰጠው የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ እንደዚሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች ፍስሐ ተክሉን በተመለከተ የጥፋተኛነቱንና የቅጣት ውሳኔውን በማጽናት በመ.ቁ 40309 ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ አመልካች ንጉሴ ገ/ዮሐንስን በተመለከተም በመ.ቁ 51484 ጥር 7 ቀን 2002 ዓ.ም በተመሳሳይ የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔውን በማጽናት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ባለመሆኑ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195(2)(ለ-2) መሠረት በድምጽ ብልጫ አጽንተነዋል፡፡
  2. በዚህ መዝገብ የተሰጠው ፍርድ ከመዝገብ ቁጥር 53495 ጐን ለጐን ተመርምሮ የተሰጠ ስለሆነ የፍርዱ ግልባጭ ከመ.ቁ 53495 ጋር ይያያዝ ብለናል፡፡
  3. መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

የ ሀ ሳ ብ  ል ዩ ነ ት

እኔ በአምስተኛው ተራ ቁጥር ስሜ የተገለፀው ዳኛ አብላጫው ድምፅ በሰጠው ውሣኔ የማልስማማ በመሆኔ የልዩነት ሀሳብ ፅፌአለሁ ተጠሪ አመልካቾች ወንጀል የፈፀሙ መሆናቸውን ያስረዱልኛል በማለት ያቀረባቸው ምስክሮች የግል ተበዳይ የሆነው አንደኛ የዐቃቤ ህግ ምስክርና የግል ተበዳይን በመኪና ሲያጓጉዝ የነበረውና ከግል ተበዳዩ ጋር በሥር አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ በነበሩ ሰዎች ተይዞ የነበረው ሁለተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች አመልካቾች ወንጀሉ በተፈፀመበት ቦታ ያልነበሩ መሆናቸውን መሥክረዋል፡፡ የወንጀሉ ሰለባ የሆኑት ሰዎች አመልካቾች ወንጀሉ ሲሰራ ያልነበሩ መሆኑን በማረጋገጥ ለመሰከሩበት ሁኔታ የግል ተበዳዮችን ጠቁመው ያስያዙት አመልካቾች መሆናቸው አመልካቾች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 29 መሠረት በሰጡት ቃል ተረጋግጧል ተብለው ጥፋተኛ መባላቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ዕርስ በርሱ የሚቃረን የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ /contradictory evidence/ ከተገቢው ጥርጣሬ በላይ በሆነ ሁኔታ ያስረዳል የሚለው መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ መሠረታዊ የህግ ስህተቶች ነው፡፡ ምስክሮች መልስ የሰጡት ቃል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 መሠረት ከማገናዘቢያነት አልፎ እንደዋና ማስረጃ መቅረቡ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው ስለሆነም አመልካቾች ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ ተሽሮ በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል በማለት በሀሳብ ተለይቻለሁ፡፡

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s