አሰሪው ክፍያ አዘገየ የሚባለው መቼ ነው?


የሰበር መ/ቁ 44405

ግንቦት 19 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- 1. ሂሩት መለሰ

2. ተሻገር ገ/ስላሴ

3. ታፈሰ ይርጋ

4. አልማው ወሌ

5. ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- ፊንፊኔ የቤትና የቢሮ እቃዎች ፋብሪካ ኃ.የተ.የግል ማህበር

ነ/ፈጅ ወ/ዮሐንስ ይርጉ ቀረቡ

ተጠሪ፡- አቶ ደጃ ደምሴ ጎበና – ወኪል ጥሩነሽ ዘውዴ ቀረቡ

መዘገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96ን መሰረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ ከአመልካች ጋር የመሰረቱትን የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ውል በራሳቸው ፈቃድ ያቋረጡ መሆኑን ገልፀው ስራ ሰርተው ያልተከፈላቸውን የሐምሌ ወር 2000 ዓ.ም ደመወዝ አመልካች የፕሮቪደንት ፈንድ ክፍያ እና ክፍያው ለዘገየበት ክፍያ እንዲከፈላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም ከተጠሪ ጋር የስራ ውል ግንኙነት የነበረው መሆኑንና ተጠሪ ግንኙነቱን በገዛ ፈቃዳቸው ያቋረጡ መሆኑን እንዲሁም የፕሮቪደንት ፈንድ ክፍያ ሳይከፈላቸው የቀረና የዘገየ መሆኑን ሳይክድ ክፍያው ያልተፈፀመው ተጠሪ የተረከቡትን ንብረት በአግባቡ ያልመለሱና ጉድለት የታየባቸው መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ አመልካች በተጠሪ ላይ ጉድለት ታይቷል የሚል ከሆነ ዳኝነት ከፍሎ በሌላ ክስ ከሚጠይቅ በስተቀር የስራ ስንብት ክፍያውን አልከፍልም ለማለት አይችልም የሚል ምክንያት ይዞ የአመልካችን ክርክር ውድቅ አድርጎ አመልካች ለተጠሪ የሐምሌ ወር 2000 ዓ.ም ደመወዝ፣ የፕሮቪደንት ፈንድ ክፍያ እንዲከፍላቸውና ስራ ልምድ ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ የካቲት 14 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ አንድ ገፅ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪ በስራ ምክንያት የተረከቧቸውን ንብረቶች ያጎደሉ በመሆኑ ክፍያውን አመልካች በወቅቱ ያለመፈፀሙ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 36 መሰረት ሕጋዊ ሁኖ እያለ የአመልካች ክርክር ታልፎ ክፍያውን እንዲፈፅም መደረጉ ያላግባብ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል ተብሎ የተጠሪ ወኪል ቀርበው መጋቢት 30 ቀን 2002 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡ የመልሳቸው ይዘትም ባጭሩ አመልካች ተጠሪ አጎደሉ ለተባለው ንብረት ሌላ የፍትሐብሔር ክስ መስርቶ በክርክር ላይ ያሉ መሆኑን ገልጸው በዚህ ጉዳይ የተሰጠው ውሳኔ ግን ሊጸና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ ሊፀና ይገባል ሲሉ መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅ በበኩላቸው ሚያዚያ 15 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ አንድ ገፅ ማመልከቻ የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርከር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ተጠሪ በስራ ምክንያት የተረከቧቸውን ንብረቶች ያጎደሉ በመሆኑ ጉድለቱን ሳያወራርዱ የሚፈፀም ክፍያ የለም በማለት ገልጾ ያቀረበው ክርክር ታልፎ አመልካች ክፍያዎችን እንዲከፍል መወሰኑ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ ከአመልካች ጋር የመሰረቱትን የስራ ግንኙነት በገዛ ፈቃዳቸው ያቋረጡ መሆኑን፣ ተጠሪ አመልካች ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ዳኝነት የጠየቁት የፕሮቪደንት ፈንድ ክፍያ እና ስራ ሰርተው ያልተከፈላቸው የሐምሌ ወር 2000 ዓ.ም ደመወዝ መሆኑን፣ አመልካች ለተጠሪ ክፍያዎችን አልከፍልም በማለት የሚከራከረው ተጠሪ በስራ ምክንያት የተረከቧቸውን ንብረቶችን ያጎደሉ በመሆኑ የማወራረድ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

በመሰረቱ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 36 ስር የስራ ውል ሲቋረጥ የሰራተኛው ደመወዝና ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ክፍያዎች ሁሉ በሰባት የስራ ቀናት ውስጥ መከፈል ያለበት ሲሆን የክፍያው ጊዜ ሊራዘም የሚችለው ሠራተኛው ከአሰሪው የተረከበውን ንብረት የማስረከብ ወይም የሚፈለግበትን ማናቸውንም ሂሳብ በማወራረድ የራሱ ጥፋት በሆነ ምክንያት ካዘገየ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ሠራተኛው ስለጠየቀው ክፍያ አለመግባባት የተፈጠረ እንደሆነ አሠሪው በአንቀፅ 36 በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለሰራተኛው ያመነውን ያህል ሊከፍል እንደሚገባ ደግሞ የአዋጁ አንቀፅ 37 ደንግጓል፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ የክፍያ ማዘግየት ውጤቱ በአንቀፅ 38 ስር የተመለከተው የሰራተኛውን እስከ ሶስት ወር ሊደርስ የሚችል ደመወዝ መክፈል ነው፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው ሠራተኛው ለአሰሪው ማስረከብ ያለበት ንብረትና ማወራረድ ያለበት ማናቸውም ሂሳብ አለመግባባት የሌለበት መሆን እንዳለበት እና አለመግባባት ካለ ግን ሰራተኛው ክፍያውን ከአሰሪው ለመጠየቅ ክስ ከማቅረብ ሙሉ በሙሉ ሊከለከል የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ሠራተኛው ጉድለት ስለአለበት ሂሳቡን ሳያወራርድ ተገቢ ክፍያዎችን ሊጠይቅ አይችልም ከተባለ በሕጉ የጊዜ ገደብ መብቶችን የማስከበር መብቱንም ዋጋ የሚያሳጣ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በመሆኑም አንድ ሰራተኛ የማያምንበት ጉድለት ካለ አሰሪው በተገቢው መንገድ ክስ መስርቶ መብቱን ከሚያስከብርና ምናልባት በራሱ ክስ ረቺ የሚሆን ከሆነ በአፈፃጸም ጊዜ ስርአቱን ጠብቆ የዕዳ ይቻቻልልኝ ጥያቄ ከሚያቀርብ በስተቀር ለሠራተኛው መክፈል ያለበትን ክፍያ ከመጠየቅ ክስ ሊቀርብ አይገባም ወይም ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ሲከራከር ተቀባይነት ያገኛል ማለት አለመሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 36 እስከ 38 ድረስ ከተመለከቱት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች በበታች ፍርድ ቤቶች ያቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉ ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መንፈስ እና ባሁኑ ጊዜ አመልካችና ተጠሪ በንብረት ጉድለቱ ላይ በፍትሐብሔር ጉዳይ ክርክር ላይ ያሉ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለበት ለማለት አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 35485 ታህሳስ 27 ቀን 2001 ዓ.ም ተሠጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 75673 ጥር 28 ቀን 2001 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡
  2. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s