የቦርድ ስልጣን -የዕድገት ጥያቄ


የሰ/መ/ቁ. 44551

ሐምሌ 28 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

በላቸው አንሺሶ

ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡- የራስ ሆቴሎች ድርጅት ነገረ ፈጅ አቶ ጌታቸው ዘውዴ ቀረቡ

ተጠሪ፡– ሲሳይ ኃይሌ ቀርበዋል፡፡

መዝገቡን መርምረን የሚተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሆኖ አመልካች ተከሳሽ ተጠሪ ደግሞ ከሳሽ ነበሩ፡፡ የክሱም ምክንያት የእድገት ውድድር ማግኘት ሲችል እንዳላገኘ በማድረግ ያለአግባብ የስራ ውል ያቋረጠ በመሆኑ ወደ ስራ እንዲመለስና እድገቱንም እንዲያገኝ ይወሰንልኝ የሚል ነው፡፡

አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስ የስራ ውሉ የተቋረጠው ተጠሪ እድገት ለማግኘት በሚል በሐገር መከላከያ ሚኒስቴር 5 ዓመት በፔርሶኔልና ሰው ኃይል ክፍል ሰርቼለሁ በማለት የተጭበረበረ የስራ ልምድ ማስረጃ በማቅረቡ ነው በማለት ክሱ ውድቅ እንዲሆን ተከራክሯል፡፡

ግራ ቀኙን ያከራከረው ፍ/ቤት ማስረጃው በትክክል ከሐገር መከላከያ የተሰጠው መሆኑን ለማጣራት ስንብቱ ከሕግ ውጪ ነው የ6 ወር ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎ ወደ ስራ ይመለስ የፐርሶኔል ፀሐፊ ክለርክ ስራ መደብ እንዲመደብ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም ውሳኔውን በማጽናቱ የቀረበ የሰበር አቤቱታ ነው፡፡

አመልካች መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም ጽፎ ባቀረበው ቅሬታ መነሻነት እድገት እንዲሰጠው በፍ/ቤት የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ እንዲቀርብ ታዞ ሰኔ 3 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ግራ ቀኙ ቀርበው የቃል ክርክር አሰምተዋል፡፡

እኛም ክርክራቸውን በሕግ ረገድ እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

በመሰረቱ ለስንብቱ መነሻ የሆነውና የተጭበረበረ የስራ ልምድ ነው የተባለውን ማስረጃ የስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሐገር መከላከያ ሚኒስቴር ትክክለኛነቱን እንዲያረጋግጥ በማድረግ ማስረጃው ከሚኒስቴሩ የተሰጠና ትክክለኛ ስለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ ወደ ስራ እንዲመለስና ውዝፍ የ6 ወር ደመወዝ እንዲከፈለው መወሰኑ በአግባቡ ሆኖ አግኝተነናል፡፡

በሌላ በኩል ግን ተጠሪ የድርጅቱ ፐርሶኔል ፀኃፊ ክለርክ የስራ መደብ ላይ እድገት አግኝቶና ተመድቦ እንዲሰራ መወሰኑን በተመለከተ የፍ/ቤት ስልጣን ነው ወይ? የሚለው ምላሽ ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሰራተኛ አቀጣጠርና እድገት አሰጣጥ ስርአትን በተመለከተ በሚኒስቴሩ የሚመደበው አስማሚ ተከራካሪ ወገኖችን በማስማማት ፍፃሜ እንዲያገኝ እንደሚጥር በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 142/1/ ሀ ተመልክቷል፡፡ በአስማሚ ካላለቀ ደግሞ የእድገትን ጉዳት የዳኘነት ማየት የሚችለው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እንደሆነ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 147/1/ሀ ስር በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ ተጠሪ መብት አለኝ የሚልበት ምክንያት ካለው ከፍ ሲል በሕጉ በተመለከተው መሰረት ስልጣን ላለው አካል በማቅረብ መብቱን ማስጠበቅ ከሚችል ውጪ በፍ/ቤት እንዲወሰንለት ያቀረበውን የእድገት ጥያቄ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተቀብሎ ተጠሪው የፐርሶኔል ፀሐፊ ክለርክ መደብ ላይ በእድገት እንዲመደብ መወሰኑና የከፍተኛ ፍ/ቤትም በማጽናት የሰጠው ውሳኔ በሕግ አተረጓጐም ረገድ መሰረታዊ ስህተት የተፈፀመበት ነው በለናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 25288 በ17/3/2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት የከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 74051 በ24/06/2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሻሽሏል፡፡
  2. ፍ/ቤት የእድገት ጥያቄን አይቶ ለመወሰን ስልጣን የለውም ብለናል፡፡
  3. ለተጠሪ በፍ/ቤት ውሳኔ የተሰጠው እድገት አይገባውም ብለናል፡፡ ወደ ስራ መመለስና 6 ወር ውዝፍ ደመወዝ ክፍያ ውሳኔ ፀንቷል፡፡
  4. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ ብለን መዝገቡን ዘግተናል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s