የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ስልጣን- የደመወዝ ጭማሪና የስራ መደብ


የሰ/መ/ቁ. 37ዐ16

3/6/2ዐዐ1

ዳኞች፡- አቶ አብዱልቃድር መሐመድ

አቶ ሐጎስ ወልዱ

አቶ ታፈሰ ይርጋ

አቶ በላቸው አንሺሶ

አቶ ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡– የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – ነ/ፈጅ ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡- አቶ ተስፋዬ ማሞ – ቀረቡ፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ቀጥሎ የተመለከተው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ይህ ጉዳይ የሥራ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ተጠሪ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ በተከሣሽ ድርጅት በበላይ ገንዘብ ያዥነት /senior teller/ በማገልገል ላይ ሳለሁ በ1ዐኛው ኀብረት ስምምነት መሠረት የሥራ መደቡ መጠሪያ ስያሜ ተለውጦ ኦፊሻል 3 የሚል መጠሪያ በመሰጠቱ ምክንያት ለሥራ መደቡ ማግኘት የሚገባኝን ልዩ ጭማሪ ብር 219 /ሁለት መቶ አሥራ ዘጠኝ ብር/ ተከሣሽ ከልክሎኛል፡፡ ስለሆነም ተከሣሽ ከ24/5/99 ዓ.ም. ጀምሮ ማግኘት የሚገባኝን ልዩ ጭማሪ በመክፈል ወደ ቀድሞው የበላይ ገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ እንዲመልሰኝ ይወሰንልኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡

ተከሣሽም /የአሁን አመልካች/ ቀርቦ በሰጠው መልስ ከሣሽ የሚሠሩበት የሥራ ደረጃ 14 ሲሆን በዚህ ደረጃ የሚከፈለው ደመወዝ አሁን እየተከፈላቸው ካለው ደመወዝ የሚያንስ ሲሆን የተሻለ ደመወዝ እየተከፈላቸው ባለበት ሁኔታ ልዩነት ብር 219 ሊከፈለኝ ይገባል ያሉት በተገቢው አይደለም፡፡ በከሣሽ ላይ የሥራ ለውጥ ያልተደረገ ሲሆን ተደርጓል ቢባል እንኳን የከሣሽ የትምህርት ዝግጅት ማነስ የሥራ አፈፃፀም ዝቅተኝነት፣ የደንበኞች ቅሬታና የቅርብ ኃላፊዎች ግምገማ ተጨምሮበት በባንኩ የአደረጃጀት የአሠራር ለውጥ /BPR/ መሠረት ከሣሽ እንዲሠሩ የታመነበት አሁን እየሠሩ ያሉበት የሥራ መደብ ስለሆነ ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ መልኩ የቀረበለትም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ማስረጃ ሠምቶ በተከሣሽ መ/ቤት ሥራ የተቋቋመው የመሠረታዊ የአሠራር ለውጥ /BPR/ ኮሚቴ አባላት ቀርበው በሰጡት የምስክርነት ቃል ከሣሽ ለነበሩበት የሥራ መደብ ብቃት እንደሌላቸው የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ቢሆንም የግል ማኀደራቸውን ፍ/ቤቱ አስቀርቦ እንደተመለከተው መልካም የሥራ አፈፃፀም እንደነበራቸው ስለሚያሳይ የኮሚቴው ውሣኔ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባመሆኑ ከሣሽ ወደ ቀድሞ ከፍተኛ ገንዘብ ያዥነት የሥራ መደብ ሊመለሱ እና የመደቡ የደመወዝ ልዩነትም ሊከፈላቸው ይገባል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሣሽ በዚሁ ውሣኔ ቅሬታ አድሮበት የይግባኝ ቅሬታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ቢሆንም የሥር ፍ/ቤት ውሣኔ ጉድለት የሌለው ነው በሚሉት ይግባኙን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

የሰበር አቤቱታውም የቀረበው ይህንኑ ውሣኔ በመቃወም ሲሆን ይህም ችሎት አቤቱታውን መርምሮ ተጠሪ ወደ ቀድሞው የሥራ መደብ ሊመለሱ ይገባል ተብሎ በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ አግባብነቱ ተጠሪ ባሉበት ሊጣራ እንደሚገባ በማመኑ ተጠሪን በመጥራት ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከፍ ብሎ የተመለከተው ሲሆን የሰበር አቤቱታው እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡

በቅድሚያም ችሎቱ የተመለከተው የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ይህን ጉዳይ ለማየት የሥረ ነገር ሥልጣን ያለው መሆኑን በተመለተ ነው፡፡

ተጠሪ በፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በክስ አቤቱታቸው ዳኝነት የጠየቁት ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ቀድሞ ስሰራበት ወደነበረው የሥራ መደብ እንድመለስና ለመደቡም የተሰጠው ልዩ ጭማሪ እንዲከፈለ በማለት ነው፡፡

የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት በሚገዛው በአዋጅ ቁጥር 377/96 ለወልም ሆነ ለግል የሥራ ክርክር የተሰጠ ትርጉም ባይኖርም ነገር ግን አንድ የሥራ ክርክር የወል የሥራ ክርክር ወይንም የግል የሥራ ክርክር ነው ለማለት የሠራተኛው ቁጥር እንደ መለያ መስፈርት ሊያገለግል እንደማይችል ከአዋጁ አንቀጽ 138 እና 142/1/ ዝርዝር ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻል ሲሆን ክርክሩ የወል ነው ለማለት የጋራ የሆነን የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ጋር ግንኙነት ያለው ማለትም የደመወዝም ሆነ የሌላ ጥቅም፣ የቅጥርም ሆነ የዕድገት አሰጣጥ፣ የዝውውርም ሆነ የሥልጠና ከመሣሰሉት ጋር ግንኙነት ኖሮት በጋራ በሆነ ሠራተኞች መብትና ጥቅም ላይ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት በሚያስከትል ጊዜ እንደሆነ ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው አንቀጽ 142/1/ ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በተያዘው ጉዳይ የተጠሪ ጥያቄ ወደ ቀድሞ የሥራ መደቤ እንድመለስና ለመደቡም የተሰጠው ልዩ ጭማሪ እንዲከፈለኝ ይወሰንልኝ የሚል እንደመሆኑ መጠን የዚህ ዓይነቱ ጥያቄ በአንቀጽ 142/1/ሀ/ እና /ሰ/ ሥር የሚሸፈንና የወል የሥራ ክርክር ተብሎ የሚመደብ ነው፡፡ ክርክሩ የወል ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ የሚታየው በአስማሚ ወይም በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አማካኝነት እንጂ በፍ/ቤት በኩል ስላልሆነ የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በዚህ ሁኔታ ጉዳዩን ተቀብሎ ውሣኔ መስጠቱ በአንቀጽ 138/1/ ሥር ከተሰጠው የሥረ ነገር ሥልጠና ውጭ እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ስለሆነም የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በዚህ መልኩ የሰጠው ውሣኔ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይህንኑ ስህተት ሳያርም መቅረቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 21652 በ5/5/2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ እንደዚሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 63054 በ26/7/2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ጉዳዩን ለማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የለውም ተብሎ ተወስኗል፡፡
  3. ግራ ቀኙ ወጭና ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡
  4. መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ነ/ዓ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s