ሳይፈረድበት ከ30 ቀናት በላይ የታሰረ ሰራተኛ ስለሚሰናበትበት ሁኔታ


የሰ/መ/ቁ 49239

የካቲት 3 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

አመልካች፡- የአ/አ ውሀና ፍሳሽ ባለሥልጣን – አልቀረቡም

ተጠሪ፡- አቶ ፍቅሩ ከበደ – ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በሥር ፍ/ቤት ተከሳሽ አመልካች ተጠሪ ደግሞ ከሳሽ ነበር፡፡ የተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ ከሥራ ያለአግባብ መሰናበቱን ጠቅሶ ካሣ እና ልዩ ልዩ ክፍያዎች እንዲወሰንለት አመልክቷል፡፡ በአመልካች በኩል የቀረበው ክርክር ተጠሪ ለሥራ በተሰጠው የጦር መሣሪያ አስፈራርቶ የዝርፊያ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ በፖሊስ መያዙን እና በዚህም መነሻ ከጥቅምት 11 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ከ30 ተከታታይ የሥራ ቀናት በላይ ሥራው ላይ ባለመገኘቱ ስንብቱ ሕጋዊ ነው እንዲባል አመልክቷል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌ/የመ/ደረጃ ፍ/ቤት ተጠሪ የማስፈራራት ወይም የዝርፍያ ወንጀል ስለመፈፀሙ አልተረጋገጠም እንዲሁም ተጠሪ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የታረሰበት ጊዜ የሥራ ውል እንዲታገድ ማድረግ እንጅ ለስንብት የሚያበቃ ምክንያት አይደለም ሲል ስንብቱ ሕገወጥ ነው በማለት ተጠሪ ወደ ሥራ እንዲመለስ ፈርዷል፡፡

ይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይግባኙን ሰርዟል የአመልካች ድርጅት ነ/ፈጅ መስከረም 14/2002 ዓ.ም የተፃፈ አቤቱታ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡ የሰበር አቤቱታቸው ይዘት ባጭሩ ተጠሪ በገፈርሳ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ በጥበቃ ሥራ ላይ እንደነበር ለዚህ ሥራ የተሰጠውን የጦር መሣሪያ ይዞ በማስፈራራት በመዝረፍና በመግደል ሙከራ ተጠርጥሮ ተይዞ በመታሰሩ በድርጅቱ የሕብረት ስምምነት ሰንጠረዥ “ለ” ተራ ቁጥር 30 መሠረት ለድርጅቱ ጥበቃ የተሰጠውን የጦር መሣሪያ ለወንጀል ተግባር መጠቀም ከሥራ የሚያሰናብት ጥፋት ስለመሆኑ ይህም በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/96 አንቀጽ 27/1/ለ መሠረት ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ እንደሚያስችል እንዲሁም በአዋጅ አንቀጽ 18 መሠረት እግድ ለመወሰን ተጠሪው የታሰረ ስለመሆኑ በአሥር (10) ቀናት ውስጥ ለአመልካች ባለማስታወቁ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ የሕግ ስህተት እንዲታረም በማለት አመልክተዋል፡፡

ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የቀረበውን አቤቱታ ከሕጉ አንፃር ለመመርመር ተጠሪን አስቀርቧል፡፡ ተጠሪ ጥር 19/2002 ዓ.ም የጽሑፍ መልስ አቅርቧል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ከ13/2/2001 ዓ.ም እስከ 13/3/2001 ዓ.ም ድረስ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ የታሰረ መሆኑን ነገር ግን በዋስ እስከተፈታበት ህዳር 15/2001 ዓ.ም ድረስ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ለድርጅቱ አለማሳወቁን እንዲሁም የተጠረጠረበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በፍ/ቤት እንዳልተወሰነበት ጠቅሶ የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የሕግ ስህተት የለውም ተብሎ እንዲፀና አመልክቷል፡፡ አመልካችም አቤቱታውን በማጠናከር መልስ ሰጥቷል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክርና የጉዳዩ አመጣጥ ከፍ ሲል የተመለከተው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡

የዚህ ችሎት ምላሽ የሚሻ ነጥብ ሆኖ የተገኘው አመልካች የሥራ ውል ለማቋረጥ በቂ የሕግ ምክንያት አለው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ ከመዝገቡ መረዳት የተቻለው ተጠሪ ከአመልካች ድርጅት ለሥራ የተሰጠውን የጦር መሣሪያ ይዞ በማስፈራራት፣ በዝርፍያ እና በመግደል ሙከራ ወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ ከጥቅምት 13/2001 ዓ.ም እስከ ህዳር 13/2001 ዓ.ም እስር ላይ የነበረ መሆኑና በዚህ ጊዜያት ውስጥም ያለበትን ሁኔታ ለአሠሪው (ለአመልካች) አለማሳወቁን ነው፡፡ ይህንን የተረጋገጠ ፍሬ ነገር የሥር ፍ/ቤቶች ተቀብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ መኖሩ በተረጋገጠ ጊዜ ተፈጻሚነት ያለው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ድንጋጌዎች መመርመር አግባብ ሆኖ አግኝተናል፡፡

የሥር ፍ/ቤት በዚህ ረገድ የወሰደው አቋም ሠራተኛው በእሥር ላይ የቆየ መሆኑ ከተረጋገጠ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 18 መሠረት ተጠሪን ከሥራ ያሳግዳል እንጂ ለማሰናበት አያበቃም ብሏል፡፡ በአመልካች በኩል ደግሞ ያለው ክርክር ተጠሪ ስለመታሰሩ በአሥር ቀናት (10) ውስጥ ለአመልካች ባለማሳወቁ ይህ አንቀጽ ተፈጻሚነት የለውም የሚል ነው፡፡ ይልቁንም አሠሪ ባላወቀው ምክንያት ሠራተኛው ከሥራው ለተከታታይ አምስት ቀናት ስለቀረ በአዋጅ አንቀጽ 27/1/ለ መሠረት ስንብቱ በአግባቡ ነው የሚል ክርክር አቅርቧል፡፡

ስለሆነም በግራቀኙ ክርክር የአዋጁ አንቀጽ 18 ተፈጻሚነት አለው መባሉ በአግባቡ ነው የሚለውን ስንመለከት በዚህ ድንጋጌ ሥር የተመለከቱት ምክንያቶች አንዱ ተሟልቶ በተገኘ ጊዜ የሥራ ውልን ለተወሰነ ጊዜ ለማገድ እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ ለተያዘው ክርክር አግባብነት ያለው አንቀጽ 18(3) እንዲህ ይነበባል፡፡

“ሠራተኛው ከ30 ቀን ለማይበልጥ ጊዜ ሲታሰር እና የሠራተኛው መታሰር በአሥር ቀን (10) ውስጥ ለአሠሪው ሲነገረው ወይም ይህንኑ አሠሪው ማወቅ ሲገባው” ለማገድ በቂ ምክንያት እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መረዳት እንደሚቻለው ሠራተኛው የታሰረው ከ30 ቀን ለማይበልጥ ጊዜ መሆኑ እና ስለመታሰሩም በአሥር ቀናት ውስጥ ለአሠሪ ማሳወቅ አስፈላጊ መስፈርቶች መሆናቸው ነው፡፡ በአማራጭም አሠሪው ሊያውቅ የሚችልበት ሁኔታ ካለ የማስታወቅ ግዴታ ላይኖርበት መቻሉን ነው፡፡

በዚህ ረገድ ከፍ ሲል እንደተመለከትነው ተጠሪ ለ30 ቀናት የታሰረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜያት ውስጥ ለአሠሪው (ለአመልካች) አለማሳወቁን ተጠሪው አምኗል፡፡ ከዚህም አልፎ አመልካች ማወቅ ይችል ነበር ወይም ስለማወቁ ተጠሪ ያቀረበው ክርክር የለም፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ ደግሞ የአዋጅ አንቀጽ 18(3) በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ላለው ክርክር ተፈጻሚ ሊሆን የሚችልበት አግባብ የለም፡፡

አንድ ሠራተኛ በዚህ አዋጅ በተመለከቱት ምክንያቶች የሥራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ መታገዱን ማስረዳት ካልቻለ አሊያም በአሠሪው ፈቃድ ከሥራ መቅረቱን ካላረጋገጠ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት መኖሩን ማስረዳት ካልቻለ በአዋጁ አንቀጽ 27(1)ለ መሠረት በመደዳው ለአምስት የሥራ ቀናት መቅረቱ ከተረጋገጠ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንፃር የአመልካች እና የተጠሪ የሥራ ውል የተቋረጠው በአዋጁ አንቀጽ 27(1)ለ መሆኑን መረዳት ችለናል፡፡ በዚህ ምክንያት የሥር ፍ/ቤት ተጠሪው በመደዳው ከአምስት ቀን በላይ ይልቁንም በጠቅላላው ከ30 ቀናት ያላነሰ ጊዜ ከሥራው ላይ ያልነበረ መሆኑን ተረድቶት እያለ በወንጀል ተጠርጥሮ ታስሯል በሚል ምክንያት ብቻ የአዋጁን አንቀጽ 18 ጠቅሶ የአመልካችን ክርክር ውድቅ ማድረጉ ተገቢነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል የሥር ፍ/ቤት ለውሳኔ ምክንያት ያደረገው ተጠሪ የተጠረጠረበትን ወንጀል ስለመፈፀሙ አልተረጋገጠም የሚል ነው፡፡ የተጠሪው በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ መባል ወይም በነፃ መሰናበት ለዚህ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ግኑኝነት ክርክር ወሳኝ ፍሬ ነገር ሆኖ መወሰድ የሚገባው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የተጠቀሰው ምክንያት የወንጀል ድርጊት መፈጸም አለመፈጸሙ ሳይሆን ያለበቂ ምክንያት እና ያለአሠሪው እውቅና ከ5(አምስት) ተከታታይ ቀናት በላይ ከሥራ በመቅረቱ መሆኑ ነውና፡፡ በመሆኑም የሥር ፍ/ቤቶች የአመልካችን ክርክር ከአዋጅ አንቀጽ 18 ድንጋጌ አንፃር በማየት የሰጡት ፍርድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡

ስለሆነም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የፌ/የመ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 51370 የሰጠው ፍርድ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 79305 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠው ተጠሪው ያለአመልካች እውቅና በመደዳው ለተከታታይ 30 ቀናት ከሥራ የቀረ መሆኑ በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 27(1)ለ መሠረት ስንብቱ ሕገወጥ አይደለም ብለናል፡፡

የዚህን ፍ/ቤት ወጪና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ

መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s