በተቀጣሪና በመንግስት ሰራተኛ መካከል ያለው ልዩነት


የመዝገብ ቁጥር 464ዐ2

የካቲት ዐ9 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተገኔ ጋታነህ

መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጎስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

አልማው ወሌ

አመልካች፡– አዋሽ ተፋሰስ ባለሥለጣን ነ/ፈጅ ዘላለም ወ/ተንሣይ ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1. አቶ መኰንን ያሊ

2. አቶ ሁሴን ይመር    ቀረቡ

3. አቶ ማሞ ሀ/ማርያም

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሊቀርብ የቻለው የአገልግሎት የስራ ስንብት ክፍያ በስራ እያሉ ያልተከፈላቸው በይርጋ ቀሪ ከሚሆነው ውጪ የሰሩት የእሁድ እረፍት ቀን የትርፍ ሰዓት የበዓል እና የዓመት ፈቃድ ክፍያ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት አመልካች ለተጠሪዎች እንዲከፍል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአሚባራ ወረዳ ፍ/ቤት የተሰጠው ውሣኔ በገቢረሱ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትም በመጥናቱ አመልካች በሰበር አቤቱታ ስላቀረበ ነው፡፡

በስር ፍርድ ቤት ከሣሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ በመሠረቱት ክስ የሥራ ውሉን አመልካች ከሕግ ውጭ ማቋረጡን ገልፀው የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉዋቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኑ አመልካችም በሰጠው መልስ፤ ተጠሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 515/99 መሠረት የሚታይ እንጂ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት በሥራ ክርክር ችሎት ሊታይ እንደማይገባ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ጠቅሶ የተከራከረ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም የአመልካwች የክፍያ ጥያቄዎች አግባብነት የላቸውም የሚልባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን በመጀመያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአመልካችን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥብ ውድቅ አድርጎ በተጠሪዎች የተጠየቁት ክፍያዎች እንዲከፈሉ በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለገቢረሱ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሠረት ተሠርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረፈጅ ሰኔ ዐ1 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ አመልካች የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ ከተጠሪዎች ጋር የመሠረተው ግንኙነት የሚታየው በአዋጅ ቁጥር 515/99 መሠረት መሆኑን አዋጅ ቁጥር 534/1999 እና ደንብ ቁጥር 156/2ዐዐዐ የሚያሣዩ ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ማየታቸው መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሰለሆነ ሊታረም ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት መሥሪያ ቤቱ ይተዳደራል በማለት ያቀረበው ክርክር በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ተደርጎ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ጉዳዩ መታየቱ ከአዋጅ ቁጥር 534/1999 እና ከደንብ ቁጥር 156/2ዐዐዐ አንፃር ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀረብ ተደርጎ ተጠሪዎች ህዳር ዐ3 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገጽ ማመልከቻ የጽሑፍ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ የአመልካች ነገረፈጅ በበኩላቸው ኀዳር 28 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ ማመልከቻ የመልስ መልሣቸውን አቅርበዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

አዋጅ ቁጥር 534/1999 የተፋሰስ ምክር ቤቶችና ባለሥልጣናት አዋጅ ሲሆን ይህ አዋጅ በቁጥር ንዑስ ቁጥር አንድ ስር የተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤቶችና ባለሥለጣናት በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚወጡ ደንቦት እንደሚቋቋሙ ሲያስቀምጥ በቁጥር ሁለት ስር ደግሞ ”ተፋሰስ” ለሚለው ቃል ትርጉም ሰጥቶ የሚያጠቃልላቸውን የኢትዮጵያ ዋና ዋና ተፋሰሶችን ዝርዝር ያሣያል፡፡ አዋሽ ተፋሰስ ከእነዚህ ተፋሰሶች አንዱ ስለመሆኑ ቁጥር 2/1ሐ/ ድንጋጌ ያሣያል፡፡ ደንብ ቁጥር 156/2ዐዐዐ ደግሞ የአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት እና ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ደንብ ሲሆን በቁጥር 2/1/ ስር የአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት እና ባለሥለጣን የሕግ ሰውነት ያለው ራሱን የቻለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሁኖ መቋቋሙን ደንግጓል፡፡ ይኸው ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር ሁለት ስር መሥሪያ ቤቱ በተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤቶችና ባለሥልጣናት አዋጅ ቁጥር 534/1999 መሠረት እንደሚተዳደር የሚደነግግ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 534/1999 አንቀጽ 12/2/ለ/ ሰራተኞች የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕግን መሠረታዊ ዓላማዎች ተከትሎ መንግሥት በሚያፀድቀው መመሪያ መሠረት እንደሚቀጠሩ እና እንደሚተዳደሩ ያሣያል፡፡ የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 13 ሲታይም በጀቱ በፌዴራል መንግሥት ከሚመደብ ገንዘብና በአዋጁ መሠረት ከሚሰበሰብ ከውሃ ክፍያ የተውጣጣ እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ አዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 2/3/ ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር ሆኖ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚያወጣው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተ “የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት” መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ እንዲሁም የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 3 አዋጁ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ ተፈፃሚነት ያለው ስለመሆኑ ይገልፃል፡፡ ስለሆነም ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 534/1999 እና በደንብ ቁጥር 156/2ዐዐዐ የተቋቋመ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሆኑን ነው፡፡

በመሠረቱ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3/1/ አዋጁ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሠረተ የስራ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚነት እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን በመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች ተፈፃሚት እንደሌለው የተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር ሁለት ፊደል “ሠ” ስር በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከእነዚህ የሕግ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው አመልካች የመንግሥት አስተዳደር መሥሪያ ቤት በመሆኑ ከሰራተኞቹ ጋር የሚነሣው ክርክር በልዩ ሕግ /አዋጅ ቁጥር 515/1999/ መሠረት የሚታይ እንጂ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት የሚዳኝ አለመሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት የአመልካችን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በማለፍ ጉዳዩን በዋጅ ቁጥር 377/96 አይቶ መወሰኑ አዋጅ ቁጥር 534/99 እና ደንብ ቁጥር 156/2ዐዐዐ ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ባግባቡ ያላገናዘበ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1.                   በአሚባራ ወረዳ ፍርድ ቤት መጋቢት 3ዐ ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተሰጠው ብይንና ሚያዚያ 19 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተሰጠው ውሣኔ እንዲሁም በገቢረሱ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ/ቁጥር ዐ1ዐ79 ግንቦት 14 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የተሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡

2.                   በተጠሪዎች እና በአመልካች መካከል ያለው ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 515/1999 መሠረት የሚታይ እንጂ በአዋጁ ቁጥር 337/96 መሠረት ሊዳኝ የሚገባው አይደለም በለናል፡፡

3.                   በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ተ.ወ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s