የስራ መሪ


የመዝገብ ቁጥር 47776

ጥር 27 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

ዳኞች፡– ተገኔ ጌታነህ

ሐጎስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

አመልካች፡– ናስ ፉድስ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተከራይ –

ጠበቃ ወንድዬ ግርማ ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1. አቶ ሲሣይ ገብሬ – ቀረበ፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ሊቀርብ የቻለው የአገልግሎት የስራ ስንብት ክፍያ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሣኔ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በመጽናቱ አመልካች የሰበር አቤቱታ ስላቀረበ ነው፡፡

በስር ፍርድ ቤት ከሣሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ የመሠረቱት ክስ የስራ ውሉን በገዛ ፈቃደቸው መልቀቃቸውንና ተገቢ ከፍያ ያልተፈፀመላቸው መሆኑን ገልፀው የስራ ስንብት ክፍያ ብር 767ዐ.ዐዐ ክፍያው ለዘገዬበት የሦስት ወር ደመወዝ ብር 5,31ዐ.ዐዐ ያልተጠቀሙት የዓመት እረፍት ክፍያ ብር 1,634.4ዐ መብታቸው ባለመከበሩ የስራ ውሉ ስለተቋረጠ ካሣ ብር 1ዐ,62ዐ.ዐዐ በድምሩ ብር 25,234.4ዐ/ ሃያ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሣ አራት ብር ከአርባ ሣንቲም/ ከተገቢው ወጪና ኪሣራ ጋር እንዲከፍላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኑ አመልካችም በሰጠው መልስ ተጠሪ የስራ መሪ በመሆናቸው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት በስራ ክርክር ችሎት ሊታይ እንደማይገባ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ጠቅሶ የተከራከረ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም የአመልካች የክፍያ ጥያቄዎች አግባብነት የላቸውም የሚልባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአመልካችን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነጥብ ውድቅ አድርጎ ለተጠሪ የተጠየቀው የስራ ስንብት ክፍያ እንዲከፈል እና የጡረታ ሽፋን እንዲያገኙ ወይም መዋጮውን በተመላሽ እንዲያገኙ ተገቢውን ግዴታ አመልካች እንዲወጣ በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሠረት ተሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ ሐምሌ 24 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ የሰበር አቤቱታቸውም ተመርምሮ ተጠሪ ከነበራቸው የስራ ኃላፊነት አንፃር ጉዳዩ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ሊገዛ የሚችል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ነጥብ ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎ የግራ ቀኙ የቃል ክርክር ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተሰምቷል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካች ድርጅት የበጀትና የኮስት ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን በዚሁ ክፍል ኃላፊነት ያላቸው የስራ መዘርዝር ደግሞ የዋና ክፍሉን ስራ ማደራጀት መምራት መቆጣጠር እና በስራቸው ያሉትን ሰራተኞች የስራ አፈፃፀም የሚሞሉ ግድፈት ሲፈጽሙ እርምጃ የሚወስዱ እና በስራ ኃላፊነታቸው አበል ተወስኖላቸው ሲቀበሉ የነበሩ መሆኑ መረጋገጡን የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ የስራ መሪ ሊባሉ አይችሉም ያለበት ምክንያት ቦታው “የስራ መሪ” የሚል ቢሆንም በተግባር ግን የስራ መሪ ሊፈጽም የሚገባቸውን ስራዎችን ማከናወናቸው አልተረጋገጠም በሚል ስለመሆኑ እና ተጠሪ በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ግን በስሩ በነበሩት ሰራተኞች ፈቃድ ይሰጡ የነበረ እና ይቆጣጠሩ የነበረ መሆኑን አምነው የተከራከሩ መሆኑን ነው፡፡

በመሠረቱ የአዋጁ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3/1/ አዋጁ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሠረተ የስራ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚነት እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን የስራ መሪን ማለትም በሕግ ወይም እንደ ድርጅቱ የስራ ፀባይ በአሰሪው በተሰጠ ውክልና መሠረት የስራ አመራር ፖሊሲዎችን የማውጣትና ከእነዚሁ በተጨማሪ ወይም እነዚህን ሣይጨምር ሰራተኛን የመቅጠር የማዛወር፣ የማገድ፣ የማሰናበት፣ የመመደብ ወይም የሥነ ሥርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውንና የሚወስን ግለሰብ ላይ ተፈፃሚት እንደሌለው የተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር ሁለት ፊደል “ሐ” ስር በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከዚህ የድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው የሥራ መሪ ማለት በአንድ በኩል የስራ አመራር ፖሊሲዎችን የማውጣትና የማስፈፀም ኃላፊነት ያለበት ሲሆን በሌላ በኩልም ከዚሁ ኃላፊነት በተጨማሪ ወይንም ይህን ሣይጨምር ሰራተኛን የመቅጠር የማዛወር እና ተያያዥነት ያላቸውን ስራዎች የሚያከናውን ሰው ስለመሆኑ ነው፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የስር ፍርድ ቤት ተጠሪን የስራ መሪ ለማለት አይቻልም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ተጠሪ የስራ መዘርዝሩ የስራ መሪ መሆናቸውን የሚያሣይ ቢሆንም በተግባር ሲያከናውኑ የነበረ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም በሚል ምክንያት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተጠሪ ከስራ መዘርዝራቸው በተጨማሪ በክፍሉ የነበሩትን ሰራተኞች የመቆጣጠር እንዲሁም እርምጃ የመውሰድ ስራ በተግባር ሲሰሩ የነበሩ መሆኑ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ የስራ መዘርዝራቸው ሲታይም ተጠሪ የዋና ክፍሉን ስራ ማደራጀት መምራት መቆጣጠር እና በስራቸው ያሉትን ሠራተኞች የስራ አፈፃፀም የሚሞሉ ግድፈት ሲፈጽሙ እርምጃ የሚወስዱ እና በስራ ኃላፊነታቸው አበል ተወስኖላቸው ሲቀበሉ የነበሩ መሆኑ በግልጽ ያስገነዝባል፡፡ በዚህ መሠረትም በአመልካችና በተጠሪ መካከል ያለው ግንኙነት በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ የሚገዛበት ሕጋዊ ምክንያት የለውም፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ በተግባር የስራ መሪ ስራ ሲያከናውኑ የነበሩ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም በማለት የደረሰበት ድምዳሜ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 3/ለሐ/ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ጋር ባግባቡ ያላገናዘበ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ አግኘተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1.   በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁጥር 27358 ሰኔ 17 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር ዐ4855 ሐምሌ 16 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በትእዛዝ የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/

ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡

2.   ተጠሪ በአመልካች ጋር የነበራቸው ግንኙነት የስራ መሪ በመሆኑ ጉዳዩ በአዋጁ ቁጥር 377/96 መሠረት ሊዳኝ የሚገባው አይደለም ብለናል፡፡

3.   በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ተ.ወ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s