የአሰሪ ትርጉም


የሰ/መ/ቁጥር 48648

የካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- 1. ተገኔ ጌታነህ

2. መንበረፀሐይ ታደሰ

3. ሂሩት መለሰ

4. አልማው ወሌ

5. ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የፃልቄ የትምህርትና የተቀናጀ የልማት ማህበር – የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- 1. አቶ ታጠቅ ደጀኔ

2. አቶ ተፈሪ በርቤ      ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት የቀረበውን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ ሚያዚያ 29 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ የክስ ማመልከቻ በመሰረቱት ክስ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ 1ኛ ተጠሪ ከአመልካች ድርጅት ታህሳስ 13 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በፕሮግራም ማናጀርነት፣ 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ከጥቅምት 03 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በኮሚኒቲ ወርከር የስራ መደብ ተቀጥረው እንደሰሩና የስራ ውሉ ያላግባብ ሚያዚያ ዐ8 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም መቋረጡን ገልፀው ካሳ፣ የስራ ስንብት፣ ክፍያ ለዘገየበት ክፍያ፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ የሚያዚያ ወር ደመወዝ እና የዓመት እረፍት ክፍያ ከወጪና ኪሳራ ጋር ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚይሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ድርጅትም ለክሱ በሠጠው መልስ፣ ተጠሪዎች ለተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩ ሰራተኞች ሁነው የስራ ቅጥር ውላቸውም ለማህበሩ በለጋሽ ድርጅቶች የሚሠጠው እርዳታ በመቆሙ ፕሮጀክቱ የተዘጋ ስለሆነ መቋረጡን ገልፆ የስራ ውል የተቋረጠው በሕጉ አግባብ በመሆኑ የተጠየቁት ክፍያዎች ሊከፈሉ አይገባም ሲል በማለት ተከራክሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤትም ክርክሩንና ማስረጃዎችን መርምሮ የስራ ውሉ ለአንድ ፕሮጀክት ተጠሪዎች የተቀጠሩ ስለመሆኑ የማያሳይ፣ ተጠሪዎች ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩ ሰራተኞች ናቸው ስለማይባሉ፣ በአንድ ፕሮጀክት መዘጋት ምክንያት ተጠሪዎችን ማሰናበቱ ህጋዊ አይደለም የሚል ምክንያት በመያዝ የአመልካችን ክርክር ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎ ተጠሪዎች ካሳ፣ የስራ ስንብት ክፍያ፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ የሚያዚያ ወር ደመወዝ እና የዓመት ፈቃድ ክፍያ አመልካች ሊከፍላቸው ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ስንብቱ ሕገወጥ ተብሎ ውጤቶቹን በተመለከተም የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሰረት ተሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረ ፈጅ ነሐሴ 01 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሦስት ገፅ የሰበር አቤቱታ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪዎች ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩና የተቀጠሩበት ፕሮጀክት የተዘጋ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ተጠሪዎች የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ መወሰኑ ያላግባብ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የተጠሪዎች የስራ ውል ለተለየ ፕሮጀክት የተቀጠሩ መሆኑን የሚያስረዳ ባለመሆኑ ተጠሪዎች ይሰሩበት የነበረው ፕሮጀክት ተቋርጧል በሚል የስራ ስንብቱ ሕገወጥ ነው መባሉ እና የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉ መወሰኑ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪዎች ቀርበው ታህሳስ 13 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገፅ ማመልከቻ ተጠሪዎች የተቀጠሩት ለጠቅላላ ፕሮጀክት በመሆኑ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ቅሬታ ነጥቦች ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን፣ በአንፃሩ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተገቢነት ያለው መሆኑን በመዘርዘር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አልተፈፀመም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅም ታህሳስ 19 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገፅ የመልስ መልስ ሠጥተዋል፡፡ ይህ ችሎትም ጉዳዩን መርምሮ ግራ ቀኙን ጥር 12 ቀን 2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት ያነጋገረ ሲሆን ግራ ቀኙ የስራ ውል ለጠቅላላ ፕሮጀክት የተደረገ መሆኑንና አመልካች ድርጅትም በአሁኑ ወቅት ስራውን እየሰራ እንደሚገኝ ተማምነዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር ማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ተብሎ ተጠሪዎች የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ የተወሰነው ባግባቡ ነው ወይም አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ተጠሪዎችን አሰናበትኩ የሚለው ተጠሪዎች የተቀጠሩበት ፕሮጀክት በመዘጋቱ ነው የሚል ምክንያት ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ ቅጥሩ ለተዘጋው ፕሮጀክት ሳይሆን ለጠቅላላ ፕሮጀክት ሁኖ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ይገኛል በማለት የሚከራከሩ ሆኖ ቅጥሩ ለጠቅላላ ፕሮጀክት ስለመሆኑ በዚህ ችሎት በተደረገው ማጣራት መረጋገጡን ነው፡፡ ይህ ፍሬ ነገር ከተረጋገጠ ደግሞ በተጠሪዎች እና በአመልካች መካከል ያለው ግንኙነት መገዛት ያለበት በመካከላቸው በተቋቋመው ውል በመሆኑ ተጠሪዎች በአዋጁ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 10(1ሀ) መሰረት ለአንድ ለተለየ ፕሮጀክት የተቀጠሩ ሰራተኞች አለመሆናቸውን መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የተሠጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሳ ኔ

1.    በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 30005 ሰኔ 03 ቀን 2001 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 52383 ሐምሌ 30 ቀን 2001 ዓ.ም በከፊል የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

2.    በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

ት ዕ ዛ ዝ

በዚህ ችሎት ነሐሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም ተሠጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ይጻፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s