የክፍያ መዘግየት- የፍርድ ቤቶች ስልጣን


የሰበር መ/ቁ 47952

የካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

መንበረፀሐይ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- እንይ ጀነራል ቢዝነስ – የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- አቶ ዘሪሁን ገበየሁ – ቀረቡ

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው የስራ ክርክርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ተጠሪ አለአግባብ ከሥራ ተሰናብቻለሁ በማለት አመልካች የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍላቸው ለፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ክስ መስርተዋል፡፡ አመልካችም ተጠሪ ከሥራ የተሰናበቱት አዱስ መዋቅር በመዘርጋቱና የተጠሪ እድሜና የትምህርት ደረጃ ለነበሩበት ቦታ የማይመጥን በመሆኑና የስራ አፈፃፀማቸው ከሚጠበቀው በታች  በመሆኑ በሌላ ሰራተኛ መተካት ግድ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የተጠሪን የስራ ውል የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው በማለት የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡ በዚህ  ውሳኔ ላይ አመልካች ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ ፍ/ቤቱ ተጠሪ የተሰናበቱት የመዋቅሩን መስፈርት ባለማሟላታቸው በመሆኑ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት አመልካች የስንብት ክፍያ የአመት እረፍት እና ክፍያ ለዘገየበት ብቻ እንዲከፈል በማለት ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ የአመልካች ቅሬታ ተጠሪ ክፍያ ለዘገየበት እንዲከፈላቸው ሳይጠይቁ ፍ/ቤቱ እንዲከፈላቸው መወሰኑ የህግ ስህተት ነው የሚል ነው፡፡ ይህንኑ ነጥብ ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጐ ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም መዝገቡን መርምሯል፡፡

በዚህ መዝገብ ዋናው ያከራከረው ለተጠሪ እንዲከፈል የተወሰነው ክፍያ ለዘገየበት ክፍያ  ነው፡፡ ተጠሪ በስር ፍ/ቤት ክስ ሲመሰርቱ ክፍያ ለዘገየበት እንዲከፈላቸው አለመጠየቃቸው ከመዝገቡ ተረድተናል፡፡ የስር ፍ/ቤት ተጠሪ ይህንን ክፍያ ባለመጠየቃቸው ውሳኔ አልሰጠበትም፡፡ ይህም የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 182(2) የተከተለ ነው፡፡ ተጠሪም ቢሆኑ ይህ ክፍያ ሊከፈለኝ ይገባል በሚል ያቀረቡት ይግባኝ ወይም መስቀለኛ ይግባኝ የለም፡፡ ፍርድ ቤቶች ደግሞ ሊወስኑ የሚገባው በተከራካሪዎቹ ወገኖች የቀረበላቸውን የዳኝነት ጥያቄ ላይ ብቻ ነው፡፡  በእርግጥ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አስተያየት መስጠት ወይም መወሰን ይገባው ነበረ ብሎ በሚገምተው ጉዳይ ላይ ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል ይኸው ድንጋጌ ያመለክታል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን ቀድሞውኑ ተጠሪ ክፍያው እንዲከፈላቸው ጥያቄ ስላላቀረቡ የስር ፍ/ቤትም ሆነ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በዚህ ነጥብ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችልበት የህግ መሠረት የለም፡፡ በመሆኑም የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ተጠሪ ያልጠየቁትን ክፍያ ለዘገየበት እንዲከፈላቸው መወሰኑ የሥነ-ሥርዓት ህግ ስህተት ነው፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡


ው ሳ ኔ

  1. የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 79289 ሐምሌ 14 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሏል፡፡
  2. አመልካች ለተጠሪ ክፍያ ለዘገየበት እንዲከፍል የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ብቻ ተሽሯል፡፡
  3. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቻውን ይቻሉ፡፡
  4. በዚህ ውሳኔ መሠረት እንዲፈፀም ይህ ችሎት ነሐሴ 14 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው የዕግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከተው ክፍል ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ

የማይነበብ የሦስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s