የዓመት ፍቃድ መወሰዱንና የተላለፈበትን ሁኔታ ማስረዳት ያለበት ማነው?


የሰበር መ/ቁ. 47161

የካቲት 24 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

መንበረፀሐይ ታደሰ

ሂሩት መለሠ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡– ወ/ሮ እቴነሽ ለማ ወኪል ህሩይ ጌትነት

ተጠሪ፡– አቶ ያሬድ ጥዑመልሣን – ቀረቡ

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው የስራ ክርክርን የሚመለከት ነው፡፡ አመልካች ለፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ በገዛ ፈቃዳቸው ስራ ስለለቀቁ የዓመት ዕረፍት ጨምሮ ሌሎች ክፍያዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪም አመልካች በገዛ ፍቃዳቸው ሣይሆን ከስራ ለ5 ተከታታይ ቀናት ከስራ በመቅረታቸው ከስራ የተሰናቱ በመሆኑ ክሱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም አመልካች ከስራ የተሰናበቱት በገዛ ፈቃዳቸው ነው በማለት የስንብት ክፍያ የ2 ዓመት የዓመት እረፍት በገንዘብ ተቀይሮ እንዲሁም ክፍያ ለዘገየበት እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ ተጠሪ ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው ፍ/ቤቱ አመልካች ከስራ የተሰናበቱት በራሣቸው ፈቃድ ሣይሆን አመልካች ስራቸው ላይ ለ5 ተከታታይ ቀናት ባለመገኘታቸው በተጠሪ አነሣሽነት ነው በሚል የሥር ፍ/ቤትን ውሣኔ ሽሮአል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሣኔ ላይ ነው፡፡ ችሎቱም የሥር ፍ/ቤት የዓመት እረፍትን አስመልክቶ የሰጠው ውሣኔ የመሻሩን አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ግራ ቀኙ የፅሁፍ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም ጉዳዩን ከተያዘው ጭብጥ አኳያ መርምሯል፡፡

አመልካች በስር ፍ/ቤት ከጠየቁት ክፍያዎች አንዱ የዓመት ዕረፍት በገንዘብ ተቀይሮ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ የስር ፍ/ቤት ይህ ክፍያ እንዲከፈል የወሰነው አመልካች የዓመት ዕረፍት ሰለመውሰዳቸው ተጠሪ ማስረጃ አላቀረቡም በሚል ነው፡፡ በአ/ቁ. 377/96 አንቀጽ 77/1/ መሠረት እያንዳንዱ ሰራተኛ ያለተከፋፈለ ዓመት እረፍት የማግኘት መብት እንዳለው የተቀመጠ ሲሆን ይህ የእረፍት ግዜ ሊተላለፍ የሚቻለው በተወሰነ ምክንያት ለመሆኑም የአዋጁ አንቀጽ 79 ያመለክታል፡፡ አመልካች በነዚህ ምክንያቶች የዓመት እረፍታቸው የተላለፈ ለመሆኑ አላስረዱም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከመዝገቡ እንደተገነዘብነው አመልካች አስተማሪ ናቸው፡፡ አስተማሪ በመሆናቸውም ዕረፍት የሚያኙት ት/ቤቱ በክረምት ሲዘጋ መሆኑን አመልካች ለሰበር ባቀረቡት የመልስ መልስ ላይ አምነዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የዕረፍት ግዜ ስራ ሲሰሩ የነበረ ለመሆኑ በቅድሚያ ማስረዳት ያለባቸው አመልካች እንጂ ተጠሪ አይደለም፡፡ አመልካች ይህን ለማስረዳታቸው መዝገቡ አያሣይም፡፡ በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በሰጠው ውሣኔ ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽሟል ማለት ስላልተቻለ ተከታዩ ውሣኔ ተሰጥቷል፡፡

ው ሣ ኔ

1.   የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 79213 ሰኔ 18 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡

2.   ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ተ.ወ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s