የደመወዝ ጭማሪ ዓላማ


የሰበር መ/ቁ 47825

የካቲት 25 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- 1. ተገኔ ጌታነህ

2. መንበረፀሐይ ታደሰ

3. ሂሩት መለሰ

4. አልማው ወሌ

5. ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አ.ማ ነ/ፈጅ አስቴር በቀለ ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1. አቶ ዘርዓየሁ ስሜ

2. አቶ ሽፈራው አራጋው    ጠበቃ ክፍሌ ታደሠ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የአዋጅ ቁጥር 377/96ን መሰረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካች ላይ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ ከአመልካች ጋር የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት እንደነበራቸው፣ ይህ ግንኙነታቸው የተቋረጠው በተጠሪዎች ፈቃድ መሆኑን፣ የስራ ውሉ ሲቋረጥ ሊከፈላቸው የሚገባው ደመወዝ ሳይከፈላቸው የቀረ መሆኑን፣ ልዩነቱ መከሰቱን ያወቁት መንግስት የደመወዝ ጭማሪ ወይም ማስተካከያ ማድረጉን የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም ከጻፈው ደብዳቤ መሆኑን፣ የደመወዝ ማስተካከያው ከሕዳር 01 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን፣ በዚህም መሰረት 1ኛ ተጠሪ ሊከፈላቸው ከሚገባው ደመወዝ ብር 6338.84(ስድስት ሺህ ሶስት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር ከሰማንያ አራት ሳንቲም)፣ 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ብር 14430.93(አስራ አራት ሺህ አራት መቶ ሰላሳ ከዘጠና ሶስት ሳንቲም) መሆኑን ገልፀው ይኸው በልዩነት የመጣውን ገንዘብ አመልካች እንዲከፍላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ለከሱ በሰጠው መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መከራከሪያ ነጥቦችን በማንሳት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያቀረባቸውን የመከራከሪያ ነጠቦችን ውድቅ ከማድረጉም በላይ ለተጠሪዎች ክስ ኃላፊነት አለበት በማለት የክሱን ገንዘብ ለተጠሪዎች እንዲከፍል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረ ፈጅ ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ የሰበር ማመልከቻ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የስር ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት የቀረቡትን የአመልካችን መከራከሪያ ነጥቦችን ውድቅ ያደረገው ያላግባብ መሆኑን፣ ተጠሪዎች ከአመልካች ጋር የነበራቸው የስራ ግንኙነት በገዛ ፈቃዳቸው ከተቋረጠ በኋላ መንግስት ያደረገው የደመወዝ ማስተካከያ እንዲከፈላቸው የተወሰነው ከመመሪያው ዓላማና መንፈስ ውጪ መሆኑን ዘርዝረው ውሳኔው ሊሻር ይገባል በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታቸው ተመርምሮም ተጠሪዎች ከአመልካች ድርጅት ስራ ከለቀቁ በኋላ ተፈቀደ የተባለው የደመወዝ ስኬል ጭማሪ ተጠሪዎችን ይመለከታል ወይስ አይመለከታቸውም? የሚለውን እና ሌሎችን ነጥቦች ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጎ የተጠሪዎች ጠበቃ ሕዳር 23 ቀን 2002 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ ማመልከቻ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተገቢነት አለው የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅ በበኩላቸው ሕዳር 25 ቀን 2002 ዓ.ም በጻፉት ሁለት ገጽ ማመልከቻ የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል የነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት በተጠሪዎች ፈቃድ ከጥር 03 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ መቋረጡን፣ በዚህ ወቅት ተጠሪዎች ከአመልካች ድርጅት ሲሰናበቱ በወቅቱ ሊከፈላቸው ይገባል የተባለው የተለያየ ክፍያ መከፈሉን፣ ተጠሪዎች ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ በአመልካች ላይ ክስ ሊመሰርቱ የቻሉት የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም የደመወዝ ጭማሪ መመሪያው ተፅፎ ከህዳር 01 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ጭማሪው ተግባራዊ እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ተጠሪዎች የመብት ጥያቄው ምንጭ ነው የሚሉት የስራ ውሉ ከመቋረጡ በፊት ለሰሩበት ስራ በደመወዝ ጭማሪ መመሪያው መሰረት ሊከፈለን የሚገባው የደመወዝ ልዩነት አለ በማለት ነው፡፡

በመሰረቱ አንድ ሰራተኛ ከአሰሪው ጋር በሚፈጥረው የስራ ግንኙነት መሰረት ሕጉ የሚፈቀደው ማንኛውም መብት የሚጠበቅለት መሆኑ አከራካሪ አይሆንም፡፡ የአንድ መብት ወይም ግዴታ መሠረት ደግሞ ሕግ ወይም ውል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተያዘው ጉዳይም ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ተጠሪዎች የጠየቁትን ክፍያ የሚያገኙበት የሕግ መሰረት አለ ወይስ የለም? የሚለው ነው፡፡ አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ተጠሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ስለለቀቁ መመሪያው በስራ ላይ ያሉትን ሰራተኞች ለማበረታታት የወጣ እንደመሆኑ መጠን ሊከፈላቸው የሚገባ ቀሪ ደመወዝ የለም በማለት ነው፡፡ ለጉዳዩ አግባብነት አለው የተባለው መመሪያም የወጣበት መሰረታዊ ዓላማ ሲታይ የፋይናንስ ድርጅቶች ሰራተኞች የሆኑት በጭማሪው ተነቃቅተው ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ስለመሆኑ በመግቢያው ላይ የተገለፀ መሆኑን የስር ፍርድ ቤትም ያረጋገጠው ጉዳይ ነው፡፡ የመመሪያው መሰረታዊ ዓላማ ይህ ከሆነ መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ስራውን በገዛ ፈቃዱ የለቀቀ ሰራተኛ ወደኋላ ተመልሶ ማስተካከያውን መሰረት አድርጎ ቀሪ ደመወዝ ሊከፈለኝ ይገባል በማለት የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኝበት የሕግም ሆነ የስነ አመክንዮ(ሎጂክ) አግባብ የለም፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች የተጠሪዎችን የዳኝነት ጥያቄ ከመመሪያው ዓይነተኛ ዓላማ ጋር በማዛመድ መመልከት ሲገባቸው ይህንኑ ሳያደርጉ የአመለካችን ክርክር ውድቅ በማድረግ ለተጠሪዎች በቀሪነት የሚፈለጉት ደመወዝ ይከፈል በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 35175 መጋቢት 30 ቀን 2001 ዓ/ም ተሠጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 80204 ሐምሌ 06 ቀን 2001 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡
  2. ተጠሪዎች ከአመልካች ጋር የነበራቸውን የስራ ግንኙነት በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ በወጣው የደመወዝ ጭማሪ ማስተካከያ መመሪያ መሰረት የሚከፈላቸው ቀሪ ደመወዝ የለም ብለናል፡፡
  3. ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s