ሰራተኛ በአደጋ ሲሞት ለጥገኞች ስለሚከፈል ክፍያ


የሰ/መ/ቁ. 40529

የካቲት 10 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

አመልካች፡- የሕፃን ዮናታን ነጋ ተሻገር ጠ/ጥጋቡ ጌጤ ቀረቡ

ተጠሪ፡– አቶ ለገሰ አበራ ጠ/ወርቁ መንገሻ ቀረቡ

መዝገቡን መርመረን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ በሞት ምክንያት የሥራ ውል ሲቋረጥ ለሰራተኛው ጥገኞች ስለሚከፈል ካሣ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110 አተረጓጐም የሚመለከት ነው፡፡

የአመልካች አባት አቶ ነጋ ተሻገር በተጠሪ ተቀጥረው ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ሕይወታቸው በማለፉ ያልተከፈለ ደመወዝ ብር 6,500፣ያልተከፈለ አበል ብር 9,750፣የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪ ብር 2000 እና ሟች ሌላ ጥገኛ ስላልነበራቸው የሞት ካሣ ክፍያ ብር 60,000 እንዲከፈል አመልካች በሞግዚቱ አማካይነት ክስ መሰረተ፡፡ የሥር ፍ/ቤት ተጠሪ ያቀረቡትን የመጠን ክርክር በማስረጃ አጣርቶ ከካሣ ገንዘብ በተቀረ ሌሎቹን እንደ ክሱ አቀራረብ ወስኗል የሞት ካሣ አከፋፈል አስመልክቶ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110/3/ ለ እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች የእያንዳንዳቸው ድርሻ 10% ብቻ ነው በሚል ከተጠየቀው ብር 60,000 ውስጥ 10,000(አስር ሺህ) ብቻ እንዲከፈል ወስኗል፡፡

በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር ተሰኝቶ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረበ ሲሆን ከፍተኛው ፍ/ቤትም ተጠቃሹ ድንጋጌ የአንዱን ጥገኛ ድርሻ ለሌላኛው እንዲከፈል ሕጉ በግልጽ አልደነገገም የሚል ምክንያት ሰጥቶ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቷል፡፡

የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህ የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የአዋጁን አንቀጽ 110/3/ በአግባቡ አልተረጐመም፣የሟች ብቸኛ ወራሽ እና ጥገኛ አመልካች ነው፤እንዲሁም ሟች ሚስት አልነበረውም፤የሚስትም ድርሻ ጭምር ታስቦ ለአመልካች ሊከፈል ይገባል አመልካችም የተወለደው ከጋብቻ ውጪ ነው የአመልካች ሞግዚት አክስቱ ናቸው በሚሉ ፍሬ ነገሮች መነሻ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲታረም አመልክተዋል፡፡

ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት የሥር ፍ/ቤት የአዋጁን አንቀጽ 110 አተረጓጐም አግባብነት ለመመርመር ተጠሪን አስቀርቧል፡፡ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩ ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

በተያዘው ጉዳይ የአመልካች ወላጅ አባት በተጠሪ ተቀጥረው ሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ አላከራከረም፡፡ የአመልካች አባት በሥራ ላይ በሞት የተለዩ ስለመሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የሞት ካሣ ለጥገኞች ስለሚከፍልበት ሁኔታ በዝርዝር የተደነገገው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 110 እንመለከታለን፡፡

በተጠቀሰው አንቀጽ 110/1/ የተመለከተው ሊከፈል የሚገባው የክፍያ ዓይነት ነው፡፡ ይህም አንዱ ለጥገኞች የሚከፈል ካሣ ነው፡፡ ለጥገኞች የሚከፈል ካሣ መጠን እና ጥገኞች የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ድንጋጌው በቀጣይ ንኡስ አንቀጾች አመልክቷል፡፡ የሟች ጥገኞች ብሎ ሕጉ የዘረዘራቸው የሟች ልጆች ሆነው 18 ዓመት በታች የሆኑ፣የሟች ሕጋዊ ባል ወይም ሚስት እና በሟች ሰራተኛ ድጋፍ ይረዱ የነበሩ የሟች ወላጆች መሆናቸውን አንቀጽ 110/2/ ዝርዝር ያመለክታል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ከአመልካች ሌላ የቀረበ የሟች ጥገኛ ነኝ ባይ የሌለ መሆኑ ከመዝገቡ ተረድተናል፡፡

ቀጥሎ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ የካሳ ስሌት እና የአከፋፈሉ ሁኔታ ነው፡፡ ሊከፈል የሚገባው ካሳ መጠን አስመልክቶ የአዋጅ አንቀጽ 110/3/ የመጀመሪያው አረፍተ ነገር ይገልፃል፡፡ ይኸውም “የሰራተኛው የዐመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው” የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ስለሆነም የክፍያው መጠን ጣሪያ በሕጉ በግልጽ ተወስኗል፡፡ ከዚህ ተከትሎ የሚታየው ይህንን ገንዘብ በጥገኞች መካከል የሚከፋፈልበት ሥርአት የሚያመለክት ድንጋጌ ነው፡፡ ለዚህም የሟች ጥገኞች ናቸው ተብለው ከላይ የተዘረዘሩት የእያንዳንዳቸው ድርሻ መጠን በመቶኛ በአንቀጽ 110/3/ ሀ-ሐ ተዘርዝሯል፡፡ ከፍ ሲል የተመለከትነው የጥገኞች ማንነት፣ሊከፈል የሚገባው ካሣ መጠን ጣሪያው እና የስሌቱ አወሳሰን እንዲሁም የጥገኞች ድርሻ መጠን አስመልክቶ በሕጉ የተዘረዘሩትን መሰረተ ሐሳቦች ነው፡፡

ከተያዘው ጉዳይ አንፃር አከራካሪው ሟች አንድ ጥገኛ ብቻ ያለው መሆኑ በታወቀ ጊዜ ሊከፈል የሚገባው የካሳ መጠን ጣሪያው የተወሰነው (100%) ወይንስ ከላይ በዝርዝር በተመለከተው መሰረት የጥገኛው ማንነት ተከትሎ የተቀመጠው መቶኛ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አከራካሪ ጭብጥ መልስ ለማግኘት የአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌ አንቀጽ 110/4/ በዝርዝር መመርመር ተገቢ ነው፡፡ የዚህ ድንጋጌ ይዘት እንዲህ የነባባል፡፡

“በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 የክፍፍል መጠን መሰረት ተሰልቶ የክፍፍሉ መጠን በድምር (100%) (መቶ በመቶ) የሚበልጥ እንደሆነ የክፍፍሉ ድምር መጠን 100%(መቶ በመቶ) እስኪሆን ከእያንዳንዱ ጥገኛ ላይ ጥገኛ በየመጠኑ ይቀነሳል፡፡ እንዲሁም የክፍፍሉ መጠን መከፈል ከሚገባው አጠቃላይ መጠን የሚያንስ የሆነ እንደሆነ የክፍፍሉ መጠን መቶ በመቶ እስከሚሆን ለእያንዳንዱ ጥገኛ ድርሻ እንደመጠኑ የጨመራል” ይላል፡፡ አንቀጽ 110/4/ ይመለከታል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር መገንዘብ የሚቻለው የእየንዳንዱ ጥገኛ ድርሻ ተዳምሮ ሊከፈል ከሚገባው ጣሪያ (ወሰን) በላይ የሚሆን ከሆነ የእያንዳንዱ ጥገኛ ድርሻ በመቶኛ በሕጉ ከተሰጠው ሊቀነስ እንደሚገባ ነው፡፡

የዚህ ድንጋጌ መንፈስ ሟች ሰራተኛ በርካታ ጥገኞች ቢኖሩት በአዋጁ አንቀጽ 110/3/ ሀ-ሐ በተቀመጠው መጠን ለእያንዳንዱ እየተሰላ የአሰሪውን ሃላፊነት መጠን ከጣሪው(ወሰን) እንዳያልፍ ወይም የአሰሪው ሃለፊነት በአንቀጽ 110/3/ የመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር ከተቀመጠው የሥሌት መጠን እንዳያልፍ ለመከላከል ነው፡፡ ይህ የሕጉ ሐሳብ ተፈፃሚነት የሚኖገው ሟች ሰራተኛ በርካታ ጥገኞች ኖሮት የእያንዳንዳቸው ድርሻ በመቶኛ ድምር ከጠቅላላው መቶኛ ድምር በላይ ሆኖ ሲገኝ ነው ማለት ነው፡፡ አንቀጽ 110/4/ ሁለተኛው ዐረፍተነገር ይዘት ደግሞ ሲታይ ሟች ሰራተኛ ያለው ጥገኛ ቁጥር አነስተኛ ሆኖ የእያንዳንዳቸው ድርሻ ስሌት ተደምሮ አሰሪው ሊከፈል ከሚገባው በታች ሆኖ ሲገኝ ቀሪውን መቶኛ ገንዘብ ሌሎቹ ጥገኞች እንዲያገኙት ለማድረግ እንደሚቻል የታሰበ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ማለት ሟች ሁለት ልጆች ብቻ ቢኖሩት እና ሚስት ባይኖረው በአንቀጽ 110/3/ ለ መሰረት የልጆቹ ድርሻ 20% ሲሆን ቀሪው 80% ተጠቃሚ (ባለመብት ጥገኛ) የለውም ተብሎ የሚቀር ሳይሆን ለእነዚሁ ልጆች እንደየድርሻው በመቶኛ ሊጨመርላቸው እንደሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡ የዚህ ድንጋጌ መንፈስ የጥገኞች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ የአሰሪ ሃላፊነት ጣሪያ ወሰን ድረስ ያሉት ጥገኞች ተጠቃሚ እንዲሁኑ ለማድረግ ያሰበ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በተያዘው ጉዳይ ሟች አቶ ነጋ ተሻገር ከአመልካች ሌላ ጥገኛ ስለመኖሩ የቀረበ የለም፡፡ በሥር ፍ/ቤት የተወሰደው አቋም አመልካች ድርሻ 10% ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የአንቀጽ 110/4/ ድንጋጌ ሁለተኛው ዐረፍተ ነገር እንደሚያስገነዝበው አመልካች ብቸኛ የሟች ጥገኛ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የተጠሪ የሃላፊነት መጠን ጣሪያ ድረስ ካሳው ሊከፈለው ይገባል፡፡ ይህም ማለት የአመልካች ድርሻ 10%(አስር በመቶ) ሳይሆን መቶ በመቶ(100%) ነው፡፡

ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች ይህንን በአግባቡ ሳይገናዝቡ የአመልካች ድርሻ 10% ብቻ ነው በማለት የአዋጁን አንቀጽ 110/3/ለ በመጥቀስ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ሆኖ አግኝተናል፡፡

የአመልካች ድርሻ መቶ በመቶ ነው ከተባለ ስሌቱ ምን ያህል ነው ለሚለው የሥር ፍ/ቤት የአመልካች አባት ደመወዝ በወር 1000 መሆኑን መሰረት አድርጐ የሰጠው ፍርድ ተጠሪ ስላልተቃወሙ በአንቀጽ 110/3/ መሰረት በሞት ምክንያት ሊከፈል የሚገባው የካሣ መጠን አመልካች በሥር ፍ/ቤት ያቀረቡት ብር 60,000 (ስልሳ ሺህ ብር) መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በዚሁ መሰረት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

ው ሳ ኔ

1.   የፌ/መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 22962 የሰጠው ፍርድ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 66031 የሰጠው ውሳኔ የአመልካች የካሣ ድርሻ አስመልክቶ የሰጡት የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕቁ. 348/1/ መሰረት ተሻሽሎ ተከታዩ ተወስኗል፡፡

2.   አመልካች የሟች አቶ ነጋ ተሻገር ብቸኛ ጥገኛ መሆኑ ስለተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110/4/ መሰረት ካሣ ሙሉ ለሙሉ ሊከፈለው ይገባል ብለናል፡፡ ስለሆነም በሟች ደመወዝ ተሰልቶ የቀረበው ብር 60,000 (ሥልሳ ሺህ ብር) ይከፈለው ብለናል፡፡ የሥር ፍ/ቤት በዚሁ መሰረት እንዲያስፈጽም ታዟል፡፡

የዚህን ፍ/ቤት ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s