በስራ ላይ ለደረሰ አደጋ የጉዳት ካሳ አከፋፈል


የሰ//. 4337

ግንቦት 12/2ዐዐ1

ዳኞች፡– 1. መንበረፀሐይ ታደሰ

2. ሐጎስ ወልዱ

3. ሒሩት መለሠ

4. በላቸው አንሺሶ

5. ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡ግብርና ምርት ማሣደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት /ፈጅ ዳንኤል ያሬድ

ተጠሪ፡አቶ ጌታቸው ገድሌ ቀረቡ፡፡

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው በሥራ ላይ ጉዳት ለደረሰበት ሠራተኛ የሚከፈልን የጉዳት ካሣ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡

ጉዳዩ የጀመረው በፌ//ደረጃ ፍ/ቤት ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በመሠረቱት ክስ በሥራ ላይ በደረሰባቸው አደጋ የጉዳት ካሣ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ አመልካችም ለክሱ በሠጠው መልስ ደመወዛቸው ሣይቋረጥ አሣክሞ መዳናቸው ሲረጋገጥ ወደ ሥራ መልሷቸው እየሠሩ በመሆኑ በተጨማሪ ካሣ ሊከፈላቸው አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ ከጉዳቱ አገግሞ ሥራ መጀመሩ በራሱ የጉዳት ካሣን የሚያስከለክለው ባለመሆኑ አመልካች ለተጠሪ በአ/. 377/96 አንቀጽ 19/3/ መሠረት የጉዳት ካሣ እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ላይ ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ መ/ሰጪን መጥራት ሣያስፈልገው ይግባኙን ሠርዞታል፡፡

የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በዚህ ውሣኔ ላይ ሲሆን አመልካች በቅሬታው ተጠሪ በደረሰባቸው አደጋ ታክመው ወደ ሥራቸው የተመለሱና የመስራት ችሎታቸው የቀነሰ ወይም ችሎታቸውን ያጡ ወይም ገቢያቸው ያልቀነሰ በመሆኑ፣ የተጠሪ ሁኔታ የተሻሻለ ወይም የተባባሠ ለመሆኑ በድጋሚ እንዲታከሙ ጠይቀን ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በድጋሚ ለማከም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፍ/ቤቱ የሕክምና ምርመራው እንዲካሄድ ትዕዛዝ መስጠት ሲገባው ይህንን አለማድረጉ አመልካች የመንግሥት ልማት ድርጅት በመሆኑና ለደሰው ጉዳት በገባው የመድን ሽፋን ባለመኖሩ ጉዳት ካሣው ሊከፈል የሚገባው በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ መሠረት ሆኖ ሣለ በአ/. 377/96 አንቀጽ 19/3/ መሠረት እንዲከፈል መወሰኑ እንዲሁም ጉዳት ካሣው መጠን ሊሠላ የሚገባው ጉዳቱ በደረሰበት ጊዜ ተጠሪ በሚያገኙት ገንዘብ እንጂ ከረጅም ዓመት በኋላ በእድገት ባገኙት የደመወዝ መጠን ባመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ሊሻር ይገባል በማለት አመልክቷል፡፡

ይህ ችሎትም ተጠሪ ከደረሰባቸው ጉዳት ታክመው ተሽሏቸው ወደ ሥራ የተመለሱና የቀድሞ ስራቸውን እያከናወኑ በመሆኑ በአ/377/96 አንቀጽ 13/3/4/ መሠረት የተጠሪ ሁኔታ መሻሻሉ ወይም መባባሱ በሕክምና ሣይረጋገጥ ጉዳት ካሣ አመልካች ሊከፍል አይገባም የሚለውንና የአመልካች ቅሬታና ሌሎች ነጥቦችን ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሠበር ችሎት እንዲቀርብ ለማድረግ ተጠሪም ቀርበው ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በቃል አሠምተዋል፡፡ ችሎቱም የሠበር አቤቱታ የቀረበበትን ውሣኔ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች አኳያ እንደሚከተለው መርምሯል፡፡

ከፍ ሲል እንደተገለፀው ተጠሪ በስራቸው ላይ እያሉ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ በግራ ቀኙ አልተካደም፡፡ ተጠሪም ለዚህ አደጋ የጉዳት ካሣ ሊከፈለኝ ይገባል ሲሉ አመልካች ሊከፈላቸው አይገባም ይከፈል ቢባል እንኳን ሊከፈላቸው የሚገባው በአ/377/96 አንቀጽ 19/3/ መሠረት ሣይሆን በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ መሠረት ሲሆን መጠኑም ሊሠላ የሚገባው ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ ያገኙ በነበረው ደመወዝ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

ስለሆነም በዚህ ችሎት መልስ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ጭብጦች

  1. አመልካች ለተጠሪ የጉዳት ካሣ ሊከፍል ይገደዳል ወይ?
  2. ይገደዳል የሚባል ከሆነ በየትኛው ሕግ መሠረት ነው ጉዳት ካሣው ሊከፈል የሚገባው?
  3. መጠኑስ የሚሠላው እንዴት ነው? የሚሉት ሆነው አግኝተነዋል፡፡

1ኛውን ጭብጥ በተመለከተ በተጠሪ ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑ አመልካችም አልተከራከረም ከክርክሩ ሂደትም በተጠሪ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን 2% ቋሚ የአካል ጉዳት መሆኑ በሃኪሞች ቦርድ መረጋገጡን ተረድተናል በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 17 መሠረት ማንኛውም በሥራ ላይ የሚመጣ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ እንደ ጉዳቱ አይነትና መጠን ክፍያ እንደሚደረግለት ይደነግጋል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ለተጠሪ ካሣ ሊከፍል አይገባም በማለት የሚከራከረው የአካል ጉዳት ማለት የመስራት ችሎታ መቀነስን ወይም ማጣትን የሚያስከትል ሁኔታ በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት መሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 99/1/ ሥር የተመለከተ በመሆኑና ተጠሪ ግን አደጋ የደረሰባቸው ቢሆንም ታክመው ስለተሻላቸው የቀድሞ ስራቸውን ያለምንም ችግር እየሠሩ በመሆኑ የመስራት ችሎታቸው ሣይቀንስ ወይም ችሎታቸውን ሳያጡ ወይም ገቢያቸው ሣይቀነስ ካሣ ሊከፈላቸው አይገባም በማለት ነው፡፡ በእርግጥ በአዋጁ አንቀጽ 99/1/ ሥር “የአካል ጉዳት” ማለት የሠራተኛውን የመስራት ችሎታ መቀነስ የሚያስከትል ወይም ጭራሹንም ችሎታውን የሚያሣጣ ጉዳት ነው ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

እዚህ ላይም መነሣት ያለበት ጉዳይ “የመስራት ችሎታ” በማለት በድንጋጌው የተመለከተው ሠራተኛው ጉዳት በደረሰበት ጊዜ ይሠራ የነበረውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን ችሎታ ብቻ ነው ወይስ ሠራተኛው ከአደጋው በኋላም ቢሆን ሊሠራ የሚችለውን ማንኛውንም ሥራ የመስራት ችሎታ ነው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህን ነጥብ ግልጽ ለማድረግ የአዋጁ አንቀጽ 99/1/ የእንግሊዝኛውን ትርጉም ማየቱ ጠቃማ ይሆናል፡፡

“Disablement” means any employment injury as a consequence of which there is a decrease or loss of capacity to work /ስርዝ የተጨማረ/

ከዚህ የእንግሊዝኛ ትርጉም በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የአካል ጉዳት ሠራተኛው ይሠራ የነበረውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን የተወሰነ ችሎታውን ብቻ የሚመለከት ሣይሆን በአጠቃላይ ወደፊትም ሠራተኛው በሌሎች የሥራ መስኮች ተሠማርቶ ሌሎች ሥራዎችንም ለመስራት የሚያስችለውን ችሎታ /capacity to work/ የሚመለከት ነው አንድ ሠራተኛ እስከመጨረሻው በመጀመሪያ የተቀጠረበትን ሥራ በመስራት ሣይገደብ ወደፊትም የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት የሚችል መሆኑ ይገመታል፡፡ ሕጉም የአካል ጉዳትን ለማያያዝ የፈለገው ሠራተኛው አደጋ በደረሰበት ጊዜ ይሠራ የነበረውን ሥራ ለመስራት የሚያስችለው ውሱን ችሎታ ጋር ብቻ ሣይሆን ይልቁንም የሠራተኛው ወደፊት በተለያየ የሥራ መስክ ተሠማርቶ ለመስራት ከሚያስችለው አጠቃላይ የመስራት ችሎት ጋር ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ በአደጋው ምክንያት 2% ቋሚ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ለመሆኑ በሀኪሞች ቦርድ ተረጋግጧል፡፡ ይህንንም አመልካች አልካደም ይህ የደረሰባቸው ጉዳት ደግሞ ምንም እንኳን አሁን የሚሠሩትን ሥራ በአግባቡ መስራት ቢያስችላቸውም ጉዳቱ ወደፊት የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ከሚያስችላቸው ችሎታ አኳያ ሊመዘን ይገባል፡፡ በመሆኑም አመልካች ተጠሪው አደጋ በደረሰባቸው ጊዜ ሲሰሩ የነበረውን ሥራ ያለችግር በመስራታቸው ብቻ ችሎታቸው አልቀነሰምና ካሣ ሊከፍል አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡

ሌላው አመልካች የሚከራከርበት ነጥብ የሠራተኛው ሁኔታ የተባባሰ ወይም የተሻሻለ ወይም ትክክል ያልሆነ ምርመራ ተደርጎለት ከሆነ ሠራተኛው በድጋሚ እንዲመረመር ሊደረግ ስለሚችል በዚሁ መሠረት በድጋሚ ተመርምረው ውጤቱ ሣይታወቅ ካሣ ልከፍል አይገባም የሚል ነው፡፡ በእርግጥ አመልካች እንዳለው የሠራተኛው ሁኔታ ተሻሽሏል ወይም ተባብሷል የሚባል ከሆነ በአዋጁ አንቀጽ 12/3/ መሠረት ሲጠየቅ ድጋሚ ሕክምና ሊደረግ እንደሚችል አዋጁ ይፈቅዳል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች የተጠሪ ሁኔታ ተሻሽሏል የሚል ከሆነ ይህንን የማስረዳት ሸክም አለበት፡፡ ይህንን የማስረዳት ሸምክ ግን በቂ ማስረጃ በማቅረብ አልተወጣም፡፡ ድጋሚ ምርመራ እንዲደረግ የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታልን ጠይቆ ሆስፒታሉ ፈቃደኛ አለመሆኑን ከመግለጽ በቀር ሌላ ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ ወይም ተጠሪን በድጋሚ እንዲመረመሩ ጠይቆ ተጠሪው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምርመራው ያልተደረገ መሆኑን አልገለፀም፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ተጠሪ ተመርምረው 2% ቋሚ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን በሐኪሞች ቦርድ የተረጋገጠው ሁኔታ ስለመሻሻሉ ያቀረበው ማስረጃ ሣይኖር ተጠሪ የቀድሞ ሥራቸውን መስራት በመቀጠላቸው ብቻ የጉዳት ካሣ ልከፍል አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ስለሌለው የሥር ፍ/ቤቶች የጉዳት ካሣ ሊከፍል ይገባል በማለት የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለውም፡፡

2ኛውን ጭብጥ በተመለከተ አመልካች የመንግሥት የልማት ድርጅት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 19/1/ ሥርም በሕ/ስምምነቱ በሌላ አኳኋን ካልተመለከተ በቀር በአዋጁ ለሚሸፈኑ የመንግሥት ድርጅቶች ሠራተኞች የሚሠጠው የጉዳት ካሣ አሠሪው በገባበት የመድኀን ዋስትና ወይም በመንግሥት የጡረታ ሕግ መሠረት ካሣው እንደሚከፈል ያመለክታል፡፡ ድርጅቱ መድን ያልገባ ከሆነ በመንግሥት የጡረታ ሕግ ለሚሸፈኑ ሠራተኞች የመንግሥት የጡረታ ሕግ ተፈፃሚ እንደሚሆን ንዑስ ቁጥር 2 አስቀምጧል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/95 ጉዳት ለደረሰበት ሠራተኛ የሚከፈለው ካሣ መጠን የመንግሥት ሠራተኛው ጉዳት ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈለው በነበረው መደበኛ የወር ደመወዙ 45% በአምስት ዓመት ተባዝቶ የሚኘው ሂሣብ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ በደረሰው ጉዳት መቶኛ ተባዝቶ እንደሆነ አንቀጽ 33 ያመለክታል፡፡

ተጠሪ አመልካች የደረሰውን የጉዳት ዓይነት አመልካች የመድን ዋስትና ገብተው በማለት ያቀረቡት ክርክር ስለሌለ ጉዳቱ መድን ያልተገባለት መሆኑን አምነው እንደተቀበሉት ያስቆጥራቸዋል፡፡ አመልካችም የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑና ለጉዳቱ መድን ሽፋን ያልገባ በመሆኑ ተፈፃሚነት የሚኖረው የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ላይ የተመለከተው የካሣ መጠን ነው፡፡ ስለሆነም አመልካች በአ/. 377/96 አንቀጽ 19/3/ መሠረት ካሣው እንዲከፈል የተሠጠው ውሣኔ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

የመጨረሻውን ጭብጥ በተመለከተ ከፍ ሲል በተገለፀው የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/95 አንቀጽ 33 የካሣው መጠን የሚሠላው ሠራተኛው ጉዳት ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈለው በነበረው መደበኛ የወር ደሞዙ መሠረት ነው፡፡ በተያዘውም ጉዳይ ለተጠሪ የሚከፈለው የካሣ መጠን ሊሠላ የሚገባው በተጠሪ ላይ ጉዳቱ ከደረሰበት ከሠኔ 2/1999 .. በፊት በነበረው ወር ይከፈላቸው በነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ መሠረት እንጂ ከጉዳቱ በኋላ በእድገት ባገኙት ደመወዝ መሠረት ሊሆን አይገባም፡፡

ው ሣ ኔ

  1. //ደረጃ ፍ/ቤት በመ/. 36135 በዐ1/5/2ዐዐ1 .. የሰጠው ውሣኔ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/. 75693 28/5/2ዐዐ1 .. የሰጠው ትዕዛዝ ተሻሽለዋል፡፡
  2. አመልካች ለተጠሪ የጉዳት ካሣ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡
  3. የጉዳት ካሣውም ሊሠላ የሚገባው በአ/. 345/95 አንቀጽ 33 መሠረት ተጠሪ ከሠኔ 2/1999 .. በፊት በነበረው ወር ይከፈላቸው በነበረው የወር ደመወዝ መሠረት ነው ብለናል፡፡
  4. ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመ/ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

/

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s