ማታለል ለስንብት ምክንያት የሚሆነው መቼ ነው?


የሰበር መ/ቁ 41840

ሐምሌ 28 ቀን 2001 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

በላቸው አንሺሶ

ሱልጣን አባተማም

 

አመልካች፡– የናዝሬት ምግብ ዘይት ፋብሪካ – ለሜሳ ያደታ ቀረበ

ተጠሪ፡- በቀለ ጭፍራ ቀረበ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

ለአቤቱታው መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ 377/96 መሠረት የተደረገውን የሥራ ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት ሲጀመር ከሣሽ የነበረው ተጠሪ በአመልካች ላይ ክስ የመሠረተው የሥራ ውሌ ከሕግ ውጪ ስላቋረጠብኝ ወደ ሥራዬ ይመልሰኝ ዘንድ ይወሰንልኝ በማለት ነው፡፡ አመልካች ደግሞ ለክሱ በሰጠው መልስ የንብረት ክፍል ረዳት ሃላፊ ሆኖ ሲሠራ ለአንድ ድርጅት (የአመልካች ደንበኛ) ከተሸጠው 500.50 ኩንታል ፋጉሎ ውስጥ 50.40 ኩንታሉን ምንም ግንኙነት ለሌለው ሰው አሳልፎ በመስጠቱ የሥራ ውሉ በሕጉ መሠረት እንዲቋረጥ ተደርጎአል፡፡ በመሆኑም ወደሥራው የሚመለስበት ምክንያት የለም በማለት የተከራከረ ሲሆን ክሱን የሰማው ፍ/ቤትም የግራ ቀኝ ወገኖችን ማስረጃ ከሰማ በኋላ ከሣሽ (የአሁኑ ተጠሪ) ከሥራ ሊያስወጣ የሚችል ጥፋት ፈጽሞአል፡፡ ስለዚህ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በሕጉ መሠረት ነው በማለት ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትም በበኩሉ ክርክሩን የሰማ ሲሆን በመጨረሻም በወረዳው ፍ/ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አፅንቶአል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠሪ ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ በማቅረቡ በዚህ ደረጃም ክርክሩ ተሰምቶአል፡፡ ችሎቱ ክርክሩን ከመረመረ በኋላ የስር ከሣሽ ፋጉሎውን ለማን መስጠት እንደነበረበት ማጣራት ቢኖርበትም 50.40 ኩንታል ፋጉሎ ለሌላ ሰው ሰጥቶ በመገኘቱ ከባድ የሆነ የማጭበርበር ወይም ማታለል በአሠሪው ላይ ለመፈጸም አስቦ መሆኑን በማሰረጃ አልተረጋገጠም፡፡ የሚል ምክንያት በመስጠት የሥራ ውሉ የተቋረጠው በሕገ ወጥ መንገድ ነው ወደሚለው መደምደሚያ ደርሶአል፡፡ በዚህ መሠረትም በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ በመሻር ተጠሪ የአንድ ዓመት ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራው ይመለስ ሲል ወሰኖአል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ነው፡፡

አመልካች ታሕሣሥ 6 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈው ማመልከቻ የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ ተፈጸመ የሚለውን የሕግ ስህተት በመግለጽ ስህተቱ ይታረምለት ዘንድ አቤቱታ አቅርቦአል፡፡ በበኩላችንም ይህን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ ክርክሩ የተሰማው ተጠሪ የማታለል ተግባር ፈጽሞአል እየተባለ ድርጊቱ ቀላል ማታለል ነው በሚል ምክንያት የወረዳው እና የከፍተኛው ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ መሻሩ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጭብጥ ላይ ነው፡፡ ስለዚህም ይህን ነጥብ ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡

ከስር ጀምሮ የተደረገውን የግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር በዝርዝር ተመልክተናል፡፡ ተጠሪ በአመልካች ፋብሪካ የመጋዘን ሠራተኛ ነው፡፡ ከዚህ የሥራ ድርሻ በተያያዘ ሁኔታም ነው ጥፋት ፈጽመሃል የተባለው፡፡ ክሱ በቀረበለት የአዳማ ወረዳ ፍ/ቤትም ሆነ ይግባኙን በሰማው የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በማስረጃ እንደተረጋገጠው ተጠሪ ፋብሪካው ለአንድ ድርጅት ከሸጠው 500.50 ኩንታል ፋጉሎ ውስጥ 50.40 ኩንታሉን ለሌላ ሰው ማለት ከፋብሪካው ላልገዛ አሳልፎ መስጠቱ እርግጠኛ ሆኖአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፋጉሎውን የገዛው ድርጅት 500.50 ኩንታል እንደወሰደ አድርጎ መዝግቦ እንደነበረም ተረጋግጦአል፡፡ ይህ እንግዲህ በፍሬ ነገር ረገድ የተረጋገጠ ሲሆን ቀጥሎ የሚታየው የተረጋገጠው ፍሬ ነገር ከሕጉ ጋር ሲገናዘብ የሥራ ውል ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ይሆናል ወይስ አይሆንም? የሚለው ነው፡፡

ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ በቂ ምክንያቶች ተደርገው የሚወሰዱት ሁኔታዎች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ 377/96 አንቀጽ 27 በዝርዝር ተመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በንኡስ አንቀጽ 1(ሐ) የተደነገገው ሠራተኛው በሥራው ላይ የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር ፈጽሞ መገኘት ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ ተጠሪ የማጭበርበር ተግባር ስለመፈጸሙ በማስረጃ ተረጋግጦአል፡፡ የተረጋገጠውም ክሱን በሰማው ፍ/ቤት እና ይግባኙን ባየው ፍ/ቤት ነው፡፡ በመጨረሻ ጉዳዩን ያየው የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት መሠረታዊ የሕግ ስህተት ስለመፈጸም አለመፈጸሙን ከመመርመር አልፎ በማስረጃ ምዘና ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ሥልጣን የለውም፡፡ በመሆኑም በሥር ፍ/ቤቶች የተረጋገጠው ፍሬ ነገር እውነት አይደለም ወይም አልነበረውም፡፡ ያለሕጋዊ ምክንያት በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጡትን ውሳኔዎች በመሻሩም ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ችለናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ 62891 ህዳር 1 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሠረት ተሽሮአል፡፡
  2. አመልካች ከተጠሪ ጋር አድርጎት የነበረው የሥራ ውል ያቋረጠው በሕጉ መሠረት ነው ብለናል፡፡ ስለዚህም የአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ 16625 ጥቅምት 21 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 05807 መጋቢት 5 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ፀንተዋል፡፡
  3. ወጪና ኪሣራ በሚመለከት ግራ ቀኝ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s