የህግ ግምት ማስረጃ በባንክ ወለድ ላይ ያለው ተፈፃሚነት


የሰበር መ/ቁ 48110

ሰኔ 16 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

ታፈሰ ይርጋ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

አመልካች፡- የኢት/ልማት ባንክ ነ/ፈጅ ትእግስት አሰፋ ቀረቡ

ተጠሪዎች፡- 1) አቶ ፋሪስ ሲራጅ ቀረቡ

2) ወ/ሮ አለሚቱ ዳዳ ቀረቡ

መዝገቡን መረምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍርድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር የብድር ገንዘብ ወለድ አከፋፈል የሚመለከት ነው፡፡ አመልካች የሥር ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ ለንግድ ሥራ ተጠሪዎች ብር 410‚000.0 /አራት መቶ አሥር ሺህ ብር/ ተበድረው ብድር ከተወሰደበት ጥር 12 ቀን 1992 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 21 ቀን 1993 ዓ.ም ከፍሎ ለማጠናቀቅ ግዴታ ገብተው ሆኖም አላጠናቀቁም በሚል  ቀሪ ብር 257‚095.11 እና ወለዱ ብር 255‚010.80 በአጠቃላይ ብር 621‚453.71 እንዲከፍሉ እንዲወሰን ዳኝነት ጠይቋል፡፡ ተጠሪዎች ሥር ፍ/ቤት ቀርበው የብድር ገንዘብ ስለመክፈላቸው እና በመያዣ የተያዘውን ንብረት አመልካች የተረከበና የሸጠ መሆኑን ተከራክሯል፡፡ የሥር ፍ/ቤት የወለዱን ገንዘብ በተመለከተ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ካልተጠየቀ እንደተከፈለ ይቆጠራል በማለት የፍ/ብ/ሕግ/ቁጥር 2024(ረ) በመጠቀስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤትም ይህንኑ አጽንቷል፡፡ ለዚህ ሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ነው፡፡

በዚህ ሰበር ችሎት ውሳኔ እንዲሰጥበት የተያዘው ጭብጥ የወለድ ክፍያ ጥያቄን አስመልክቶ በፍ/ብ/ሕግ 2024(ረ) መሠረት ውድቅ መደረጉ በአግባቡ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ ለመመርመር ነው፡፡ ባንኮች ለደንበኞች በሚሰጡት የብድር ገንዘብ አከፋፈል ላይ የወለድ ክፍያ አፈጻጸም አስመልክቶ የፍ/ብ/ሕግ ድንጋጌ ቁጥር 2024(1) አፈጻጸም ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2473(2) አንፃር ውጤት ባለው መልኩ ሊተረጐም እና ተግባራዊ እንዲሆን ሊደረግ እንደሚገባ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ቁ 29181 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በሌላ አስካልተለወጠ ጊዜ ድረስ በፌዴራልም ሆነ በክልል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት እንዳለው በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) ተደንግጓል፡፡ በዚህ መዝገብ የቀረበው የወለድ ክፍያ ጉዳይም በተመሳሳይ መልክ መታየት ያለበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም የወለድ ክፍያን አስመልክቶ የሥር ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2024(ረ) መሠረት በሁለት አመት ጊዜ እንደተከፈለ ይቆጠራል ሲል የሰጠው ውሳኔ የዚህን ሰበር ችሎት ውሳኔ ያላገናዘበ ሆኖ ስላገኘነው ሊታረም ይገባል ብለናል፡፡

የክፍያውን ሁኔታና መጠን በተመለከተ በተጠሪዎች በኩል የቀረበው ክርክር ወለድ ቀደም ሲል የተከፈለ ስለመሆኑ ሳይሆን በፍ/ብ/ሕግ/ ቁጥር 2024(ረ) መሠረት እንደተከፈለ ይቆጠራል የሚል ሲሆን አመልካች ይህ የወለድ ገንዘብ ያልተከፈለው ስለመሆኑ በሥር ፍ/ቤት ባቀረበው ክርክር ማረጋገጡን ተረድተናል፡፡

ስለሆነም ተጠሪች ክስ የቀረበበትን የወለድ ገንዘብ ጭምር የማይከፍሉበት ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡

በዚህ መሠረት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

ውሳኔ

  1. የኢሊባቡር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 08818 የሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ 78584 በግንቦት 13 ቀን 2001 የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሻሽሎ ተከታዩ ተወስኗል፡፡
  2. በሥር ፍ/ቤት የተወሰነው ቀሪ የብድር ገንዘብና  የኢንሹራንስ ክፍያ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጠሪዎች ወለዱን በአመልካች ተመልክቶ በቀረበው መጠን ሊከፍሉ ይገባል ብለናል፡፡
  3. በዚህ ፍ/ቤት በተሻሻለው ውሳኔ መሠረት የኢሊባቡር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲያስፈጽም ታዟል፡፡ ይጻፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s