እውነተኛነቱ ያልተረጋገጠ አንድ የችሎት ገጠመኝ እንዲህ ይነበባል፡፡ ተከሳሽ ሆና የቀረበችው ሴት መልኳ የሚማርክ ሰውነቷ የሚያማልል ዓይነት ነበረች፡፡ በዛ ላይ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ተደማምሮ የዳኛውን ቀልብ ሳትስብ አልቀረችም፡፡ በችሎት የሚከናወነው አጭር የቃል ክርክር እንዳበቃ ከሳሽና ተከሻስ ከችሎት /ጉዳዩ የሚታው በዳኛው ቢሮ ውስጥ ነበር/ ሊወጡ ሲያመሩ ዳኛው ተከሳሽ ወደኋላ እንድትቀር ምልክት ይሰጧታል፡፡ ድንጋጤ የተሰማት ተከሳሽ የዳኛውን ትዕዛዝ ሳታቅማማ በመቀበል አቋቋሟን አሳምራ ተገትራ ቀረች፡፡ በዚህ ጊዜ ውበቷን ለማድነቅ ዕድል አጥተው የነበሩት ዳኛ ‘ችሎቱ በጣም ይወድሻል!’ በማለት አድናቆታቸውን በጨዋ ደንብ ገልፀዋል፡፡