ለማነው የተወሰነው?


የሰበር መ/ቁ 38506

ግንቦት 10 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- ሂሩት መለሰ

ተሻገር ገ/ሥላሴ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- 1. አቶ አማኑኤል ነጋሪ

2. ወ/ሮ ማርታ ነጋሪ      ጠ/ጌታቸው ዲኪ

3. አቶ ዳንኤል ነጋሪ

ተጠሪ፡- 1. የአ/አበባ ከተማ አስተዳደር ነ/ፈጅ ማህለት ዳዊት ቀረቡ

2. ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ቀበሌ 14 መስተዳድር የቀረበ የለም

3. አቶ ዘላለም ገዛኸኝ

4. ወ/ሮ ምስራቅ ገዛኸኝ

5. አቶ አንዱአለም ገዛኸኝ           ወኪል ዳንኤል ገዛኸኝ

6. አቶ ዳንኤል ገዛኸኝ

7. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  – ነ/ፈጅ ትዕግስት ገ/እግዚአብሔር

ፍ ር ድ

አመልካቾች ለአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ቀበሌ 14 ክልል የሚገኘውን የቤት  ቁጥር 259 አካል የሆነውን ቁጥር 260 ሰርቪስ ቤት ተጠሪዎች አላግባብ ስለያዙት ይመልሱልን በማለት ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪዎችም በሰጡት መልስ ክስ የቀረበበትን ቤት መንግሥት በአ/ቁ 47/67 መሠረት ወርሶት ሲያስተዳድረው የቆየ በመሆኑ ሊመለስ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ለረጅም አመታት በመንግሥት እጅ ይተዳደር የነበረን ቤት እንዲመለስ ለመጠየቅ በአ/ቁ 47/67 መሠረት የተፈቀደላቸውና ባለንብረት መሆናቸው ወይም ከአዋጅ ውጪ ተወስዶብናል የሚሉ ከሆነ ለሚመለከተው አካል ጥያቄአቸውን አቅርበውና ውሳኔ አግኝተው ባለመብት መሆናቸውን ማስረዳት እንዳለባቸውና ይህን ካላደረጉ ደግሞ ክስ በቀረበበት ንብረት ላይ መብት ወይም ጥቅም እንደሌላቸው በሰበር መ/ቁ 14094 የህግ ትርጉም ስለሰጠበትና አመልካቾች በዚህ መሠረት ስላላስረዱ በቤቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም የላቸውም በማለት ክሱን ውደቅ አድርጐታል፡፡ አመልካቾች በዚህ ውሳኔ ላይ ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ይግባኛቸው የተሰረዘባቸው ሲሆን የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎትም ውሳኔው መሠረታዊ የህግ ስህተት የለውም በማለት የአመልካቾችን አቤቱታ ውድቅ አድርጐታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው  በዚህ ውሳኔ ላይ ሲሆን አመልካቾች በቅሬታቸው በቤቱ ላይ መብት ያላቸው ስለመሆኑ የተለያዩ ማስረጃዎች ያቀረቡና ቤቱም ያልተወረሰ በመሆኑ መብት ወይም ጥቅም የላችሁም መባሉ መሠረታዊ የህግ ስህተት ነው በማለት ውሳኔው እንዲሻርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህ ችሎትም አመልካቾች ክስ ባቀረቡበት ንብረት ላይ ካቀረቡዋቸው ማስረጃዎች አኳያ ሲታይ መብት ወይም ጥቅም የላቸውም የመባሉን አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ያደረገ ሲሆን ተጠሪዎችም ክርክራቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡  በሌላ በኩል ግን ምንም እንኳን ችሎቱ የሰበር አቤቱታው በሰበር ችሎት እንዲታይ ያደረገበት ጭብጥ ዋናውን ጉዳይ የሚመለከት ቢሆንም በቅድሚያ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ክስ የቀረበበትን ጉዳይ ለማየት የዳኝነት ስልጣን ያላቸው መሆን አለመሆኑን ተመልክቷል፡፡ በእርግጥ ይህ ጭብጥ በግራ ቀኙ ያልተነሳ ሲሆን ችሎቱ ጥያቄውን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 9(2) መሠረት ጥያቄው ማስተናገዱ ተገቢ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

አመልካቾች ክስ የመሰረቱት ከወራሾች  በውርስ የተላለፈላቸውን ቤት ተጠሪዎች ስለያዙባቸው እንዲለቁላቸው ስለመሆኑ የክሱ ይዘት ያመለክታል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ክሱ የባለቤት መፋለም ጥያቄ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ያላቸው የዳኝነት ስልጣን በአ/ቁ 361/95 አንቀጽ 41 ስር ተዘርዝሮ ተቀምጧል፡፡ በተለይ የዚህ አንቀጽ ንዑስ ድንጋጌ ‹‹ረ›› የከተማው አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው የመንግሥት ቤቶች ጋር በተያያዙ የሚነሱ ጉዳዮችን የመዳኘት ስልጣን ያላቸው ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ ክርክር የተነሳበት ቤት ባለቤት መንግሥት መሆኑ ክርክር ባልተነሳበት ግዜ ከባለቤትነት በመልስ ያሉ ጉዳዮችን ለመዳኘት ስልጣን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ይህ የሰበር ችሎት በመ/ቁ 34428፣ 29761 እና በሌሎችም መዝገባች ላይ የህግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ክስ የቀረበበትን ጉዳይ ለማየት የስረ-ነገር ስልጣን ስለሌላቸው ክሱን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 231(1)(ለ) መሠረት ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው ክሱን ተቀብለው መወሰናቸው መሠረታዊ የህግ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

 

ው ሳ ኔ

1.   የአዲስ አበባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የመ/ቁ00466 ሐምሌ 20 ቀን 1999 የሰጠው ውሳኔ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በመ/ቁ 05155 ታህሳስ 8 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ ተሽሯል፡፡

2.   የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ክስ የቀረበበትን ጉዳይ ለመዳኘት የስረ-ነገር ስልጣን የላቸውም ብለናል፡፡

3.   ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s