ሰራተኞች ስላላቸው የቅድሚያ ክፍያ መብት


የሰ/መ/ቁ. 40921

የካቲት 26 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

ታፈሰ ይርጋ

ፀጋዬ አስማማው

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- አቢሲኒያ ባንክ (አ.ማ) ነ/ፈጅ ዱላ መራራ

ተጠሪ፡– እነ አብዱ አህመድ (266 ሰዎች) ጠበቃ ምትኩ

በዚህ መዝገብ የቀረበው አቤቱታ በመ/ቁጥር 42132 ከቀረበው አቤቱታ ጋር በስረ ነገርም ሆነ በጭብጥ ረገድ ተመሳሳይ በመሆኑ ሁለቱም መዛግብት ጐን ለጐን ተመርምረው ቀጥሎ የተመለከተው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበውም ሆነ በመዝገብ ቁጥር 42132 የቀረበው የሰበር አቤቱታ ከፍርድ አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ሲሆን በዚህ መዝገብ የፍርድ ባለመብቶች የሆኑት የአሁን ተሰጠሪዎች በፍርድ ባለእዳ ጣና ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ በፌደራል መ/ደ/ፍ/ቤት የፍርድ አፈፃፀም ማመልከቻ አቅርበው የፍርድ ባለእዳው ንብረት ተሸጦ በአመልካች ባንክ በዝግ ሂሳብ እንዲቀመጥ የተደረገው ገንዘብ ወጭ ሆኖ እንዲከፈለን ይታዘዝልን በማለት ጠይቀው የአሁን አመልካችም ቀርቦ በፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ የተሰጠባቸው የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ለብድር አከፋፈል በዋስትና የያዛችው ስለሆነ በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2857 መሰረት ከማናቸውም ገንዘብ ጠያቂ በፊት በተሽከርካሪዎቹ ላይ የቅድሚያ መብት ስላለኝ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍርድ አፈፃፀሙ ሊቀጥል አይገባም በማለት መቃወሚያ ማቅረቡን  ተገንዝበናል፡፡ በተመሳሳይም በመ/ቁ. 42832 ተጠሪዎች የሆኑት እነ አቶ አበራ መለሰ በፍርድ ባለእዳው አበባው ደስታ የግል ትራንስፖርት ላይ የፍርድ አፈፃፀም ማመልከቻ አቅረበው የባለእዳው ተሽከርካሪዎች ተሽጠው በአመልካች ባንክ በዝግ ሂሳብ እንዲቀመጥ የተደረገው ገንዘብ ወጭ ሆኖ እንዲከፈለን ይታዘዝልን በማለት አምልክተው በዚህ መዝገብም አመልካች በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2857 መሰረት ከማናቸውም ገንዘብ ጥያቄ በፊት የቅድሚያ መብት እንዳለው መቃወሚያውን አቅርቦ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 167 መሰረት በቅጥር ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት የሚመነጭ ማንኛውም የሰራተኛ ክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የእዳ ጥያቄ ቅድሚያ እንደሚኖረው ስለተመለከተ የአመልካች አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ በአመልካች ባንክ በዝግ ሂሳብ እንዲቀመጥ የተደረገው ገንዘብ ወጭ ሆኖ ለፍርድ ባለመብቶች እንዲከፈል በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

አመልካች በዚሁ ትእዛዝ ቅሬታ አድሮበት የይግባኝ ቅሬታውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበው ቢሆንም የስር ፍ/ቤት ትእዛዝ ጉድለት የሌለው ነው በማለት ፍ/ቤቱ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 337 መሰረት ይግባኙን ሰርዟል፡፡

የሰበር አቤቱታውም የቀረበው ይህንኑ በመቃወም ሲሆን ይህም ችሎት አቤቱታውን መርምሮ አመልካች በዋስትና በያዛቸው ንብረቶች ላይ የቅድሚያ መብት ሳያገኝ መቅረቱ ከአዋጅ ቁጥር 97/90 እና ከፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 2857 እንደዚሁም ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አኳያ አግባብነቱ ለሰበር ቀርቦ ሊመረመር እንደሚገባው በማመኑ በሁለቱም መዛግብት ተጠሪዎችን በመጥራት ግራ ቀኙን በጽሁፍና በቃል አከራክሯል፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከፍ ብሎ የተሰጠው ሲሆን በበኩላችንም የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ መርምረነዋል፡፡ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የፍርድ አፈፃፀሙ ሲቀጥል ለፍርድ ባለመብቶች የአሁን ተጠሪዎች ፍርድ ማስፈጸሚያነት እንዲሸጡ ትእዛዝ የተሰጠባቸው የተለያዩ ተሽከርካሪዎች አመልካች በአዋጅ ቁጥር 97/90 መሰረት ለብድር በዋስትና የያዛቸው ተሽከርካሪዎች እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ባንክ መያዣ የያዛቸውን ንብረቶች እዳው ሳይከፈለው በቀረ ጊዜ የ30 ቀን ማስጠንቀቂያ ለተበዳሪው በመስጠት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በመዣ የያዘውን ንብረት በመሸጥ ገንዘቡን ገቢ ማድረግ እንደሚችል በአዋጅ ቁጥር 97/90 አንቀጽ 3 ላይ ተመልክቷል፡፡ ከዚህም ሌላ መያዣ የተቀበለ ባለገንዘብ ከመያዣው ሽያጭ ዋጋ ከሌሎች ባለገንዘቦች ቀድሞ የመቀበል መብት እንዳለውም በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2857/1/ ላይ ተደንግጓል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች አንጻር አመልካች ከብድር አከፋፈል በመያዣነት በያዛቸው ንብረቶች ላይ የቀደምትነት መብት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩልም የአሰሪና ሰራተኛን ጉዳዩ በሚመለከተው በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት በቅጥር ላይ ከተመሰረተ የስራ ግንኙነት የሚመነጭ ማንኛውም የሰራተኛ የክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የእዳ ክፍያ ጥያቄ ቅድሚያ እንደሚኖረው በአንቀጽ 167 ላይ ተመልክቷል፡፡ አመልካች የዚህ ድንጋጌ ተፈፃሚነት በአሰሪው ላይ ሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች ክስ አቅርበው ያሰፈረዱ ባለ ገንዘቦች በሚኖሩበት ጊዜ በፍርዱ መሰረት ለነዚህ ባለገንዘቦች ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት ሰራተኖች በአሰሪያቸው ላይ ክስ መስርተው ካስፈረዱ ለሰራተኞቹ ቅድሚያ ክፍያ እንደሚፈጽም የሚያመለክት እንጂ ከዚህ አልፎ ባንኩ ለሰጠው ብድር በመያዣ የያዘውን ንብረት ሕጉ በሰጠው ስልጣን መሰረተ ሸጦ ለብድሩ እዳ እንዲውል ከሚያደርግ በስተቀር ከተቀበለው የመያዣ ንብረት ሽያጭ ላይ ለባለእዳው ሰራተኞች በቅድሚያ እንዲከፈል ተደርጐ ሊተረጐም የሚገባው አይደለም በማለት ተከራክሯል፡፡

ይሁንና በሕጉ ላይ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው በቅጥር  ላይ ከተመሰረተ የስራ ግንኙነት የሚመነጭ ማንኛውንም የሰራተኛ የክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የእዳ ጥያቄ ቅድሚያ እንደሚሰጠው የተደነገገ እንደመሆኑ መጠን የሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች አቋም ተራ ገንዘብ ጠያቂዎች/ordinary creditors/ ወይንም እንደ አመልካች በመያዣ ብድር የሰጠ ባለገንዘብ /secured creditors/ ሆኑም አልሆኑ የሰራተኛው የክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ጥያቄ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ስለተደነገገ ይህ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሊገባ እንደማይችል መገንዘብ እያዳግትም ሕጉ አውጭው የባንክ የክፍያ ጥያቄ ከሰራተኛም የክፍያ ጥያቄ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሐሳብ ቢኖረው በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 80 ላይ እንደተመለተው ዋስትና የተሰጣቸው የሌሎች አበዳሪዎች የቅድሚያ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ የግብር ሰብሳቢው መብት ግብር የመክፈል ግዴታ ባለበት ሰው ሐብት ላይ ከማናቸውም ሌሎች እዳዎች የቀደምትነት መብት ይኖረዋል በማለት እንደተደነገገው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅም ላይ ይህንኑ ያንጸባረቀው እንደበር ይታመናል፡፡

ሲጠቃለልም ለሰራተኞች የሚፈል የክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይንም የእዳ ጥያቄ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የተደነገገው በመያዣ በተያዘም ንብረት ላይ ተፈፃሚነት እንዳለው መገንዘብ ስሚቻል አመልካች በመያዣ በተያዙ ንብረቶች ላይ የቅድሚያ መብት ስላለኝ በእነዚህ ንብረቶች ላይ አፈፃፀሙ ሊቀጥል አይገባም በማለት ያቀረበውን አቤቱታ የስር ፍ/ቤቶች ሳይቀበሉት መቅረታቸው በአግባቡ ስለሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡

ው ሳ ኔ

1.  የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 33588 በ20/10/2000 እንደዚሁም በመ/ቁ. 33941 በ26/3/2001 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም በመ/ቁ. 69727 በ3/2/2001 እና በመ/ቁ. 74069 በ16/4/2000 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ በአግባቡ ስለሆነ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት አጽንተነዋል፡፡

2.  በዚህ መዝገብ የተሰጠው ፍርድ በመ/ቁ. 42132 ላይ ተፈፃሚነት ስላለው የፍርዱ ግልባጭ ከመ/ቁጥር 42132 ጋር እንዲያያዝ ብለናል፡፡

3.  ግራ ቀኙ ወጭና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡

4.  መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡

የማይንበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃLeave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s