የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍ/ቤት ስልጣን


የፍ/ይ/መ/ቁጥር 57621

ሐምሌ 30 ቀን 2002ዓ.ም

ዳኞች፡-  አስግድ ጋሻው

ደስታ ገብሩ

በላቸው አንሺሶ

አመልካቾች፡- 1ኛ አቶ እምሩ አበጋዝ

2ኛ አቶ አለማየሁ ባይሴ

3ኛ ባሻ መሐመድ

4ኛ ጌታቸው ቶላ

ተጠሪ፡- የለም

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

ው ሳ ኔ

አመልካቾች ቀደም ሲል ለፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ የአስተዳደር ፍ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ የመድሀኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ በተባለ የፌዴራል መንግስት መ/ቤት ሰራተኞች የነበረን ሲሆን መ/ቤቱ የካቲት 1 ቀን 2002ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ እንድንገለል አድርጎናል፡፡

ይሁንና በጡረታ እንድንገለል ሲያደርግ በአዋጅ ቁጥር 515/99 አንቀጽ 85/2/ መሠረት የ3 ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን በድንገት በመሆኑ በማስጠንቀቂያ ጊዜው ሊከፈለን ይገባ የነበረውን የ3 ወር ደመወዝ ሊከፈለን ይገባል የሚል ነበረ፡፡

የአስተዳደር ፍ/ቤቱንም የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ በይ/መ/ቁጥር 00958/2002/ በ22/8/2002ዓ.ም የአመልካቾች የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ክፍያ ይሰጠን ጥያቄ በአስተዳደር ፍ/ቤቱ የሚታይ አይደለም በማለት አቤቱታቸውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

አመልካቾችም በፌ/መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ይህንኑ ጥያቄያቸውን ይዘው በመ/ቤታቸው ላይ ክስ የመሰረቱ ሲሆን ጉዳዩ የቀረበለት የነበረው ችሎት በኮ/መ/ቁ 29275 በ14/ዐ8/2002ዓ.ም በዋለው ችሎት ጉዳዩ መስተናገድ ያለበት በስራ ክርክር ችሎት ነው፡፡ በማለት ስለመለሰው ክሱ ለፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ስራ ክርክር ችሎት ቀርቧል፡፡

የስራ ክርክር ችሎቱም በኮ/መ/ቁ 17073 በ28/08/2002ዓ.ም በዋለው ችሎት ከሳሾች ያቀረቡት ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት የሚታይ አይደለም በማለት ክሱን አልቀበልም ብሎ መዝገቡን መዝጋቱን ተረድተናል፡፡

አመልካቾች በተጠቀሰው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 92525 በ22/10/2002ዓ.ም በዋለው ችሎት የአመልካቾችን የይግባኝ ቅሬታ ባለመቀበል በፍ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 337ን መሠረት ቅሬታቸውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

አመልካቾች በ24-10-2002ዓ.ም ለዚህ ፍ/ቤት ጽፈው ያቀረቡት አቤቱታ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 35/2/ መሠረት ጉዳያችንን ተቀብሎ የማስተናገድ ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት /አባል/ እንደሆነ ተለይቶ ይወሰንልን በማለት አመልክተዋል፡፡

በኛ በኩል የአመልካቾችን ክስ ተቀብሎ የማስተናገድ ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው? የሚለውን ነጥብ አግባብነት ካላቸው ህጎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡

አመልካቾቹ የመንግስት ሰራተኞች መሆናቸው እና በእድሜ ምክንያት አገልግሎታቸው የተቋረጠ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡

አመልካቾቹ የመንግስት ሰራተኞች መሆናቸው እስከተረጋገጠ ድረስ አቤቱታቸው የሚስተናገድው በአዋጅ ቁጥር 515/1999 ነው፡፡

በተጠቃሹ አዋጅ አንቀጽ 74 መሠረት የመንግስት ሰራተኞች በአዋጅ አንቀጽ 75 መሠረት የሚያቀረቡትን የስራ ክርክር አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው ደግሞ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ አስተዳደር ፍ/ቤት አመልካቾች በአዋጅ አንቀጽ 85/2/ መሠረት በጡረታ እንድንገለል ሲደረግ በቅድሚያ የ3 ወር ማስጠንቀቂያ አልተሰጠንምና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያው ይከፈለን በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ የማየት ስልጣን የለኝም ያለው ይህ አይነቱ የዳኝነት ጥያቄ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ እንዲያያቸው በአዋጅ አንቀጽ 75 ውስጥ ከተዘረዘሩት የሥራ ክርክሮች ውስጥ አልተካተተም በሚል ነው፡፡

በእርግጥ በአዋጅ አንቀጽ 75 የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ክፍያ ይገባኛል የሚለው ጥያቄ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ እንዲያስተናግድ በግልጽ ሰፍሮ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዋጅ አንቀጽ 85/2/ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ጡረታ እንዲወጣ ከመደረጉ ከ3 ወር በፊት በጽሑፍ እንዲያውቀው መደረግ አለበት በማለት በአስገዳጅነት የተደነገገ ቢሆንም ሰራተኛው ጡረታ ከመውጣቱ ከ3 ወር በፊት በጽሑፍ እንዲያውቀው ባይደረግ ውጤቱ ምን ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ አዋጁ በግልጽ የሚሰጠው ምላሽ የለም፡፡

ሆኖም ይህን ነጥብ መርምሮ የሚመለሰው አቤቱታውን ተቀብሎ የማስተናገድ ስልጣን ያለው ፍ/ቤት በመሆኑ በኛ በኩል በቅድሚያ የስልጣንን ጥያቄ አስመልክቶ ለቀረበው አቤቱታ አዋጁ በጥልቀት እንደመረመርነው እና ከላይ በዝርዝር እንደሰፈረው በአመልካቾች እና በመ/ቤታቸው በኩል የሚነሱ የሥራ ክርክሮች የሚዳኙት በአዋጅ ቁጥር 515/99 እንደመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 75 ከተዘረዘሩት የስራ ክርክሮች በቀር ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን የአስተዳደር ፍ/ቤቱ እንዳያይ አዋጁ በግልጽ የከለከለው ነገር የሌለ ከመሆኑም በላይ የአመልካቾች ጥያቄም በአዋጁ አንቀጽ 75 ውስጥ ሊካተት የሚችል ተመሳሳይ የስራ ክርክር በመሆኑ የአመልካቾችን አቤቱታ ተቀብሎ የማስተናገድ ስልጣን ያለው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ አስተዳደር ፍ/ቤት ነው ብለን በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 35/2/ መሠረት ውሳኔ ሰጥተናል፡፡ ይፃፍ መዝገቡ ተዘግቷል ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የሶስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ሶ/በ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s