የአንድ እሳት የላሰ ጠበቃ ታሪክ


የሚቀጥለውን ትረካ አንዳንድ ከሳሾችና ተከሳሾች ነገሩ እውነት ሲሉ ቢደመጥም እውነተኛነቱ በገለልተኛ ጠበቃ አልተረጋገጠም፡፡

አሜሪካ ውስጥ አንድ ጠበቃ በዓለም ገበያ ላይ ብዙም የማይገኝ ውድ ሲጋራ ከገዛ በኋላ ለንብረቱ በጣም በመሳሳት የእሳት አደጋ ኢንሹራንስ ይገባለታል፡፡ የኢንሹራንስ ፖሊሲ በገዛ አንድ ወር በማይላ ጊዜ ውስጥ ጠበቃው የመጀመሪያ ዙር አረቦን /ፕሪሚየም/ እንኳን ሳይከፍል ኢንሹራንስ የተገባላቸውን 24ቱንም ሲጋራዎች ሁሉ በየቀኑ እያጨሰ ጨረሳቸው፡፡ የመጨረሻዋን ሲጋራ እንደማገ በቀጥታ ወደ መድን ድርጅቱ በማምራት በፖሊሲው መሠረት ካሳ እንዲከፈለው ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ጠበቃው ለድርጅቱ በፃፈው የክፍያ መጠየቂያ ደብዳቤ ላይ ሲጋራዎቹ “ባለማቋረጥ በተከታታይ   ለሃያ አራት ቀናት የተነሳ ግዝፉነት የሌለው እሳት ምክንያት እንደወደሙና ከጥቅም ውጭ እንደሆኑ”  በመግለጽ ክፍያ ቢጠይቅም የመድን ድርጅቱ ግን ጠበቃው መድን የገባለትን ሲጋራ ራሱ በማጨስ መደበኛ ለሆነው አገልግሎት ያዋለው በመሆኑ ተጠያቂ አይደለሁም በማለት ለመክፈል ፍቃደኛ ሳይሆን ይቀራል፡፡ መቼም ቀጥሎ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጠበቃው መድን ድርጅቱን ፍርድ ቤት ገተረው፡፡ ገትሮትም አልቀረ ረታው፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛው መጀመሪያ የመድን ድርጅቱ ያቀረበውን ክርክር በመደገፍ ክሱ “ተልካሻና የማይረባ!” መሆኑን በሐተታቸው ላይ ካሰፈሩ በኋላ እንዳሉት “ይሁን እንጂ ከሳሹ ጠበቃ ከተከሳሹ የመድን ድርጅት ፖሊሲ ገዝቷል፡፡ ተከሳሹም ለሲጋራዎቹ መድን መግባት እንደሚቻል በማረጋገጥ በእሳት ከወደሙ ክፍያ ሊፈጽም ዋስትና ሰጥቷል፡፡ በኢንሹራንስ ፖሊሲው ላይ ተቀባይነት የሌለው እሳት ወይም ሽፋን የማይሰጠው የእሳት አደጋ የትኛው እንደሆነ በግልፅ አልሰፈረም፡፡ ስለሆነም በውላቸው መሠረት ተከሳሽ ክፍያ ሊፈጸም ይገደዳል፡፡” በነገሩ የበገነው ተከሳሽ ድርጅት እንደገና ይግባኝ ጠይቆ ለተጨማሪ ክርክርና ወጪ ከሚዳረግ ይልቅ ውሳኔውን እንዳለ መቀበል ስለመረጠ 15,000 ዶላር ለጠበቃው ከፍሏል፡፡

ታሪኩ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ ጠበቃው ልክ ገንዘቡን ሲቀበል ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የኢንሹራንስ ክፍያ ለማግኘት ሲል ኢንሹራንስ የተገባለትን ዕቃ ራሱ በማውደሙ በማጭበርበር የኢንሹንስ ክፍያ በመቀበል ለፈጸመው ወንጀል በተከሳሽ ድርጅቱ ክስ ቀርቦበት ነው፡፡ በመቀጠል ጠበቃው ላጨሳቸው 24 ሲጋራዎች ለእያንዳንዱ 24 የወንጀል ክስ ቀርቦበት ራሱ ያቀረበው አቤቱና በመድን ክርክሩ ላይ የተሰሙትን ምስክሮች ቃል እንደ ማስረጃ በመጠቀም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው የ24 ወራት እስራት እና የ24,000 ዶላር የገንዘብ መቀጣ ቅጣት ወስኖበታል፡፡

ዘዴኛነቱ ሲታይ በእርግጥም ይህ ጠበቃ እሳት የላሰ ጠበቃ ነበር፡፡  እሳቱን በዛ አድርጎት እሳት ውስጥ ገባ እንጂ!

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s