ለአንድ ስራ መደብ ሊከፈል ስለሚገባ ደመወዝ (የሰበር ውሳኔ)


የሰበር መ/ቁ 40947

ህዳር 15 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡-

1. መንበረፀሃይ ታደሰ

2. ሐጎስ ወልዱ

3. ሂሩት መለሰ

4. ታፈሰ ይርጋ

5. አልማው ወሌ

አመልካች፡- አቶ መዝገቡ መድህኔ – ጠ/ሐጎስ ደበሱ ቀረቡ

ተጠሪ፡- የአ.አ ከተማ አስተዳደር – ነ/ፈጅ አትርሣው ወልዴ ቀረቡ

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የሰበር አቤቱታ የቀረበው አመልካች ተጠሪ ላወጣው ጨረታ ያስያዙት የጨረታ ማስከበሪያ ብር 20,000 ሊመለስ አይገባም ተብሎ የተሰጠውን ውሳኔ ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች በፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ ተጠሪ ባወጣው የጨረታ ብር 2,000,000 የሚያወጡ 32 አይነት እቃዎች ለማቅረብ የተወዳደሩ ቢሆንም ያሸነፉት በሁለት አይነት እቃዎች ብቻ በመሆኑ ውል እንዲሞሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው ተጠሪ ያስያዙትን የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘብ አልመልስም በማለቱ ገንዘቡን እንዲመልስላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪም ለክሱ በሰጠው መልስ አመልካች ባሸነፉባቸው ሁለት አይነት እቃዎች ውል እስካልፈረሙ ድረስ ገንዘቡ ሊመለስላቸው እንደማይገባ ተከራክሯል፡፡ ፍ/ቤቱም አመልካች በዋስትና ሰነዱ ላይ የተመለከተውን ግዴታ እስካልተወጡ ድረስ ገንዘቡ ሊመለስላቸው አይገባም በማለት ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች ይግባኝ ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው የነበረ ቢሆንም የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ፀንቶባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በመባሉም ግራ ቀኙ ቀርበው የቃል ክርክራቸው ተሰምቷል፡፡ መዝገቡም እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡

ተጠሪ ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ አመልካች 32 አይነት እቃዎች ለማቅረብ ተወዳድረው ለጨረታ ማስከበሪያም የእነዚህ እቃዎች ዋጋ አንድ በመቶ ማስያዛቸውን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል፡፡ አመልካች የተወዳደሩበት የጠቅላላ ንብረቶቹ ዋጋ ብር 2,000,000 (ሁለት ሚሊዮን) ስለሆነ የተያዘው ገንዘብ ብር 20,000 ስለመሆኑና አመልካች ከተወዳደሩበት 32 አይነት እቃዎች ውስጥ ያሸነፉት በሁለት እቃዎች ብቻ ለመሆኑ ግራ ቀኙ አልተካካዱም፡፡ አከራካሪው ጉዳይ አመልካች ላሸነፉበት ሁለት እቃዎች ውል አለመፈረማቸው ያስያዙት ብር 20,000 እንዳይመለስላቸው ይከለክላል ወይስ አይከለክልም የሚለው ነው፡፡

የጨረታ ማስከበሪያ ማለት አንድ ተጫራች ጨረታውን ቢያሸንፍ ውል የሚፈፅም ለመሆኑ ዋስትና እንዲሆን የሚያዝ ገንዘብ ነው፡፡ ለውል መፈፀም ዋስትና ሲባል የሚያዝ ገንዘብ እንደመሆኑም መጠን የጨረታው አሸናፊ ባሸነፈው መሰረት ውል ካልፈረመ የጨረታው ማስከበሪያ ይያዝበታል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ብር 2,000,000 (ሁለት ሚሊዮን) ለሚያወጡ 32 ዓይነት እቃዎች ተጫርተዋል፡፡ ለጨረታ ማስከበሪያም የተጫረቱባቸውን ጠቅላላ እቃዎች ዋጋ አንድ በመቶ ብር 20,000 (ሃያ ሺህ) አስይዘዋል፡፡ ከክርክሩ ሂደትም አመልካች ከተወዳደሩባቸው እቃዎች ውስጥ ያሸነፉት በሁለቱ እቃዎች ብቻ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ተጠይቀውም ውል ለመፈረም ፈቃደኛ ያልሆኑት እነዚህን ሁለት እቃዎች በተመለከተ ነው፡፡ አመልካች 20,000 ብር የጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ጠቅላላ ለተጫረቱበት እቃዎች በመሆኑ ጠቅላላው የጨረታ ገንዘብ ሊያዝ የሚገባው አመልካች በተወዳደሩባቸው እቃዎች በሙሉ አሸናፊ ቢሆኑና በዚሁ መሰረት ውል አልፈርምም ቢሉ ነበር፡፡ አመልካች ያሸነፉት ግን በሁለት እቃዎች በመሆኑ ለነዚህ እቃዎች ውል ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የጨረታው ማስከበሪያ ሊያዝ የሚገባው አሸናፊ በሆኑባቸው እቃዎች ዋጋ መጠን የተያዘው ገንዘብ እንጂ አመልካች ለ32 አይነት እቃዎች ላስያዙት የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘብ በጠቅላላ ሊሆን አይገባብ ባላሸነፉባቸው ዕቃዎች ቀድሞውንም ውል ለመዋዋል ስለማይችሉ ለነዚህ እቃዎች ያስያዙት የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘብ ውል አልፈፀሙም ተብሎ ሊያዝባቸው የሚገባበት ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም አመልካች ላሸነፉት ሁለት አይነት እቃዎች ውል አልፈረሙም በሚል ለ32 አይነት እቃዎች ያስያዙት ብር 20,000 በሙሉ ሊያዝ ይገባል በሚል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ው ሳ ኔ

1.   የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 01619 ጥቅምት 25 ቀን 1998 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 43929 ሐምሌ 15 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሏል፡፡

2.   አመልካች ለ32 ዓይነት እቃዎች ካስያዙት ብር 20,000 ሊያዝባቸው የሚገባው ጨረታ ያሸነፉባቸው ሁለት እቃዎች ዋጋ አንድ በመቶ ብቻ ስለሆነ ይኸው ገንዘብ ተቀንሶ ቀሪው ገንዘብ እንዲመለስላቸው ብለናል፡፡

3.   ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s