ሰራተኛው ለአሰሪው ያለበት ተጠያቂነት የህግ መሰረቱ


የሰበር መ/ቁ. 39471

ሐምሌ 29 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

ዳኞች ፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጎስ ወልዱ

ሂሩት መለሠ

በላቸው አንሺሶ

ሱልጣን አባተማም

አመልካች ፡- ኤርሚያስ ሙሉጌታ – አልቀረቡም

ተጠሪ ፡- በከልቻ ትራንስፖርት አ/ማ – ይልማ ገመቹ ቀረበ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ      ር     ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው የሰበር አቤቱታ አመልካች በተጠሪ ተቀጥሮ በሾፌርነት ሲሠራ በነበረበት ጊዜ ከጅቡቲ አስጭኖ ከመጣው የአርማታብረት ውስጥ 2ዐ ጥቅል ወይም 3ዐ5 ኩንታል አጉድሎ ተገኝቶአል በሚል ተጠሪ የመሠረተውን ክስ መነሻ በማድረግ የተደረገውን ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ ከመዝገቡ እንዳየነው ተጠሪ የብረቱን ዋጋ በማስላት እንዲከፈለው አመልካችንና ዋሱ ነች የተባለችውን ሰው አጣምሮ የከሰሰ ሲሆን፣ ተከሣሾችም የመከላከያ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ ክሱ የቀረበለት የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከመረመረ በኋላ፣ አመልካች ብር 11,250 ከወለድ እንዲሁም ከዳኝነትና ከብር 3ዐዐ.ዐዐ ኪሣራ ጋር ይከፈል፤ እሱ ባይከፍል ዋሱ ትክፈል በማለት ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ እንደአግባቡ ይግባኝ እና አቤቱታ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት እና የሰበር ችሎትም ውሣኔውን አፅንተዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚሁ ላይ ነው፡፡

አመልካች ሐምሌ 18 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በፃፈው ማመልከቻ  በሥር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ላይ ተፈፅሞአል የሚለውን የሕግ ስህተት በመግለጽ አቤቱታውን አቅርቦአል፡፡ በበኩላችንም ይህን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ ክርክሩ የተሰማው አመልካች ደረሰ ለተባለው ጉድለት ተጠያቂ ነው መባሉ አግባብ ነው ወይ? በሚለው ነጥብ ላይ በመመስረት ነው፡፡

ከሥር ጀምሮ የተደረገውን ክርክር በዝርዝር ተመልክተናል፡፡ በዚህ ሰበር ችሎት ከተደረገው ክርክር በተለይ መገንዘብ እንደቻልነው አመልካች በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሣኔ የሚቃወምበት ዋናው ምክንያት ቀደም ሲል በተደረገው ክርክር በኔ በኩል ጉድለት እንዳልተገኘ ተረጋግጦ ውሣኔ ተሰጥቶአል፡፡ ክርክሩ የተካሄደው ተጠሪ ጉድለቱን መሠረት በማድረግ የሥራ ውሌ በማቋረጡ ወደ ሥራዬ እንድመለስ በሥራ ክርክር ችሎት ክስ በመመሥረቴ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱም የስራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችል ጥፋት እንዳልተፈፀመ አረጋግጦ ውሣኔ ሰጥቶአል፡፡ በመሆኑም በተመሣሣይ ጉዳይ በድጋሚ ክርክር ሊደረግ አይችልም፡፡ በማለት ነው፡፡ ተጠሪ ደግሞ ቀደም ሲል ቀርቦ ክርክር የተደረገበት ጉዳይ የሥራ ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ክርክር ተይዞ የነበረው ጭብጥ አመልካች የሥራ ውል ሊያቋርጥ የሚችል ጥፋት ፈፅሞአል ወይስ አልፈፀመም የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ጉዳይ የተያዘው ጭብጥ ግን አመልካች በክሱ የተመለከተውን ገንዘብ ለመክፈል ይገደዳል ወይስ አይገደድም? የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩቹ ተመሣሣይ አይደሉም በማለት ተከራክሮአል፡፡

እንደምንመለከተው በዚህ ሰበር ችሎት ውሣኔ ሊሰጥበት የሚገባው ጭብጥ ተጠሪ በአመልካች ላይ የመሠርተው የገንዘብ ይከፈለኝ ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 5 ከተቀመጠው ድንጋጌ አንፃር ታይቶ ውድቅ መሆን የሚገባው ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው፡፡

በፍሬ ነገር ረገድ የቀረበው ክርክር እንደሚያመለክተው ለሁለቱም ክርክሮች መነሻ የሆነው አመልካች ያሽከረክረው በነበረው መኪና ላይ ተጭኖ የነበረው የአርማታ ብረት ጎድሎ ተገኝቶአል የሚለው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የመጀመሪያው የሥራ ክርክር በመሆኑም የታየው በስራ ክርክር ችሎት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፍታብሔር ችሎት ነው የታየው ይህ በመሆኑም ነው በአመልካች የተነሣው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 5 ላይ የተመሠረተው መቃወሚያ ተቀባይነት ያለው ነው ወይስ አይደለም የሚል አከራካሪ ጭብጥ ሊያዝ የተቻለው፡፡

ይህ የሰበር ችሎት በሰበር መ.ቁ. 3671ዐ ተመሣሣይ ክርክር ቀርቦለት በሕጉ አተገባበር ረገድ ትርጉም ሰጥቶአል፡፡ በዚህም በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚካሄደው የሥራ ክርክር የሚያዘው ጭብጥ አሠሪው የገንዘብ ይከፈለኝ ጥያቄ /ክስ/ በሠራተኛው ላይ ባቀረበ ጊዜ ከሚያዘው ጭብጥ ጋር አንድ አይነት አይደለም እሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶአል፡፡ በመጨረሻም እንደአሁኑ አመልካች በአሠሪው በጉድለት ይፈለጋል የተባለውን ገንዘብ እንዲከፍል ክስ የቀረበበት ሠራተኛ ቀደም ሲል ተካሂዶ የነበረውን የሥራ ክርክር መሠረት በማድረግ ያቀረበው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 5 ላይ የተመሠረተው መቃወሚያ ውድቅ አድርጎአል፡፡

የሰበር ችሎቱ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በተመሣሣይ ሁኔታ በተሰየመው ችሎት እስካልተለወጠ ድረስ በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍ/ቤት ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው የፌዴራል ፍ/ቤቶችን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 454/97 አንቀጽ 2/1/ ተደንግጎአል፡፡ በሰበር መ.ቁ. 3671ዐ የተሰጠው የሕግ ትርጉም አልተለወጠም፡፡ በመሆኑም በዚህ መዝገብ በቀረበው ክርክርም የተለየ የሕግ ትርጉም የሚሰጥበት አግባብ የለም፡፡ አመልካች ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የሚያገኝበት ምክንያት የለም፡፡

ው   ሣ   ኔ

  1. የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ. ዐ4ዐ76 ሚያዝያ 5 ቀን 99 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ፣ የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 53326 ህዳር 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 61371 ሚያዝያ 2ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 348/1/ መሠረት ፀንቶዋል፡፡
  2. አመልካች በዚህ ሰበር ችሎት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የሚያገኝበት የሕግ ምክንያት የለም ብለናል፡፡
  3. ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ጽ/ሽ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s