በአዋጅ ወይም በህብረት ስምምነት ያልተጠቀሰ ጥፋት መፈጸም በስንብት እርምጃ ህጋዊነት ላይ ያለው ውጤት


የሰበር መዝገብ ቁጥር 51971

ሐምሌ 09/ቀን 2002

ዳኞች፡-

1. ሓጐስ ወልዱ

2. ኂሩት መለሰ

3. ብርሃኑ አመነው

4. አልማው ወሌ

5. ዓሊ መሐመድ

 

አመልካች፡- ኤስ ኤንቪ ኢትዬጰያ – ጠበቃ ደበበ ኃ/ገብርኤል ቀረቡ

ተጠሪ አቶ አብዱራህማን ቁብሣ – ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ አዋጅ ቁጥር 377/96 “ን” መሰረት ያደረገ የአሰሪና ሰራተኛን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ በመሰረትት ክስ መነሻ ነው፡፡ የተጠሪ ክስ ይዘትም ባጭሩ፡- ከአመልካች ጋር ነሐሴ 16 ቀን 1997 ዓ/ም የመሰረቱት የስራ ውል ያለአግባብ ሐምሌ 14 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም የተቋረጠባቸው መሆኑን በመግለፅ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደ ምድብ ስራቸው እንዲመለሱ፤ ይህ የማይሆን ከሆነም የተለያዩ ሕጋዊ ክፍያዎች እንዲከፍሏቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም፤ ተጠሪ ጋር የነበረው የስራ ውል መቋረጡን ሳይክድ እርምጃው ሕጋዊ ነው የሚልባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ ተከራክሯል፡፡ አመልካች ለስንብቱ ህጋዊነት እንደምክንያት የጠቀሰው ተጠሪ ሁለተኛ ቅጥር ለመፈፀም ሞክረዋል፡፡ ለበላይ አካል አልታዘዝም ብለዋል፤ በማጭበርበር ተግባር ውስጥ ገብተው ተገኝተዋል የሚሉ ሲሆኑ እነዚህ ጥፋቶች በድርጅቱ የህብረት ስምምነት /የስራ ደንብ/ መሰረት ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል እንዲቋረጥ የሚያደርጉ ናቸው በሚል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቅጥሩ ለተወሰነ ጊዜ በመሆኑ ስንብቱ ህገወጥ ነው ሊባል የሚችል ከሆነ ለቀሪው ጊዜ ብቻ ተገቢው ክፍያ እንዲከፈላቸው፣ የተለያየ ክፍያዎችን በተመለከተ ደግሞ ተጠሪው ፈርመው የወሰዱ በመሆኑ የሚጠይቁበት አግባብ እንደሌለ እንዲወሰን በመግለፅ ተከራክሯል፡፡ ስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የአመልካችን መከራከሪያ ነጥቦችን ውድቅ አድርጎ እርምጃውን ሕገ ወጥ ነው በማለት አመልካች ካሳ፣ የስራ ስንብት እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያዎች ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ ጥር ዐ6 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- የስራ ደንቡ የስራ ውሉ አካል የሆነ እና እጥፍ ቅጥር፣ ለበላይ አካል አልታዘዘም ማለት እና የማጭበርበር ተግባር የሚከለክል ሁኖ እያለ ይኸው ታልፎ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው መባሉ ያለአግባብ ነው፣የስራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገና ቀጣይነት የሌለው ነው በሚል የቀረበ ክርክር ታልፎ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍሉ መወሰኑ ያለአግባብ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎች ለተጠሪ እንዲከፈሉ መወሰኑ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪ ቀርበው ሚያዚያ 19 ቀን 2ዐዐ2 ዓ/ም በተፃፈ ሦስት ገፅ ማመልከቻ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአመልካች ጠበቃ በበኩላቸው ሚያዚያ 22 ቀን 2ዐዐ2 ዓ/ም በተፃፈ ማመልከቻ የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ከበታች ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ግልባጭ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና ተጠሪ ነሐሴ 16 ቀን 1997 ዓ/ም የሥራ ውል ያደረጉ መሆኑን፣ በዚህ የስራ ውል በግልፅ አመልካች ድርጅት አላማዎችና ተግባራት ለትርፍ የተነሳሱ ሳይሆኑ ለልማት እና ለተዛማጅ እንቅስቃሴዎች ብቻ መሆኑ፣ ተዋዋይ ወገኖች ስራው ቋሚ አለመሆኑና በወቅቱም ከውጭ በሚገኝ ገንዘብ ላይ በከፍተኛ የሚመሰረት መሆኑን በግልፅ በማወቅ ውልን ማድረጋቸው መገልፁን እንዲሁም በውሉ ላይም የስራ ጊዜው ከነሐሴ 16 ቀን 1997 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት አመት ፀንቶ እንደሚቆይ መገለጹን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጠሪ የተቀጠሩበት የሥራው አይነትም መለስተኛ የቱሪዝም አማካሪነት መሆኑን ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ ችለናል፡፡

አመልካች ድርጅት ተጠሪ ሁለተኛ ቅጥር ለመፈፀም ሞክረዋል፤ ለበላይ አካል አልታዘዝም ብለዋል፤ በማጭበርበር ተግባር ውስጥ ገብተው ተገኝተዋል በሚል ያቀረባቸውን የመከራከሪያ ነጥቦችን የስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ያደረጉት ድርጊቶቹ ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውልን ለማቋረጥ የሚያስችሉ ጥፋቶች ተብለው የተዘረዘሩት በህብረት ስምምነት ሳይሆን በስራ ውሉ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1/ተ// ስር የሚሸፈኑ አይደለም በሚል ነው፡፡ ይህ ችሎትም የተጠቀሰውን ድንጋጌ መንፈስና ይዘት ከአላማው ጋር አገናዝቦ ሲመለከተው በአዋጁ አንቀጽ 27 ስር ከተመለከቱት ሁኔታዎች ውጪ አንድ ጥፋት የስራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው በሕብረት ስምምነቱ በግልፅ ተቀምጦ በተገኘ ጊዜ ነው፡፡ የህብረት ስምምነት ሰፊ ውይይት ድርድር ተደርጎበት የሚደረስ በመሆኑ ከስራ ውሉ የተሻለ ድርድር የሚያደርግበት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ በዚሁ ሰነድ ውስጥ የሚካተቱ ድርጊቶች ሕጋዊ ተቀባይነት አላቸው፡፡ በመሆኑም አመልካች ድርጊቶቹ የስራ ውል አካል ስለሆኑ እንደ ሕጋዊ ምክንያቶች ሊወሰዱ ይገባል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት ያለው ሁኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም አመልካች ተጠሪን ያስናበትኩት በጥፋት ነው የሚለው ክርክር ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ እርምጃው ሕገ ወጥ ነው ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡

ሌላው በዚህ ችሎት መታየት ያለበትና ምላሽ ማግኘት ያለበት ነጥብ ሁኖ የተገኘው አመልካች የስራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ ነው በማለት ያቀረበውን ክርክር በተመለከተ ነው፡፡ ይህ ክርክር በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ ስለሆነ በዚህ ችሎት ሊነሳ አይገባም በማለት ተጠሪ የሚከራከሩ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ይሁን እንጂ ክርክሩ በስር ፍርድ ቤት መነሳቱን የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የመረመረው ሲሆን ይህ ችሎትም ክርክሩ በስር ፍርድ ቤት መነሳቱን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም ክርክሩ ስርዓቱን ጠብቆ የቀረበ በመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠሪ ያቀረቡት ተቃውሞ ተቀባይነት የሌለ ሁኖ አግኝተናል፡፡

የስራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ ነው የሚለውን የአመልካችን ክርክር ህጋዊነት ስንመለከተው አመልካች ድርጅት አላማዎችና ተግባራት ለትርፍ የተነሳሱ ሳይሆኑ ለልማት እና ለተዛማጅ እንቅስቃሴዎች ብቻ መሆኑ፣ ተዋዋይ ወገኖች ስራው ቋሚ አለመሆኑንና በወቅቱ ከውጭ በሚገኝ ገንዘብ ላይ በከፍተኛ የሚሰረት መሆኑን በግልፅ በማወቅ ውልን ማድረጋቸው መገልፁን እንዲሁም በውሉ ላይ የስራ ጊዜው ከነሐሴ 16 ቀን 1997 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት አመት ፀንቶ እንደሚቆይ በስር ፍርድ ቤት አመልካች ባቀረበው ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጠሪ የተቀጠሩበት የሥራው አይነትም መለስተኛ የቱሪዝም አማካሪነት መሆኑ ክርክር የተነሳበት ነጥብ አይደለም፡፡

በመሰረቱ የስራ ውል በመርህ ደረጃ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተደረገ ሕጉ ግምት የሚወስድ መሆኑን አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 9 በግልጽ የሚደነግገው ጉዳይ ሲሆን ይህ በሕጉ ግምት የተሰጠው ጉዳይ ሊስተባበል የሚችለው በአዋጁ አንቀጽ 1ዐ ስር በተመለከቱት መንገዶች ቅጥሩ መፈፀሙን አሰሪው ካስረዳ ብቻ ነው፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ተጠሪን በጊዜ በተገደበ የስራ ውልና የስራ ውሉም ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ መሆኑን አውቀው ተጠሪ መቀጠራቸውን መሠረት በማድረግ የስራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ ነው በማለት ይከራከራል፡፡ ሆኖም ቅጥሩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 1ዐ ስር በተመለከቱት ሁኔታዎች የተፈጸመ ስለመሆኑ አያሳይም፡፡ ምንም እንኳ ተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ የመስጠት ነፃነት ያላቸው ቢሆንም በሕጉ የተመለከቱትን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የስራ ውል ሊዋዋሉ ይገባል፡፡ የስራ ውል ሕጋዊ ጥበቃ የሚያገኘው ይዘቱ ሕጋዊ ሁኖ ሲገኝ ስለመሆኑ ከአዋጁ አንቀጽ4 ድንጋጌ መንፈስ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመሆኑም አመልካች ድርጅት የመለስተኛ ቱሪዝም አማካሪነት ስራ በባሕሪው ቀጣይነት የሌለው መሆኑን ባለስረዳበት ሁኔታ እና ውሉ በጊዜ መገደብን ብቻ በምክንያትነት በመጥቀስ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ የስራ ውል ነው በማለት የሚቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ አመልካች ድርጅት ከሌሎች ድርጅቶች በሚያስገኘው የእርዳታ ገንዘብ የሚተዳደር መሆኑም የእርዳታ ገንዘቡ ያልተቋረጠ መሆኑ ያልተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ቢቋረጥ እንኳ አመልካች ተጠሪን ማሰናበት የሚገባው ራሱን በቻለ ሥርአት እንጂ ያለማስጠንቀቂያ የሚያሰናብትበት ምክንያት አይደለም፡፡ በመሆኑም በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

ው ሳ ኔ

1.   በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 36ዐ78 ግንቦት 12 ቀን 2ዐዐ1 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 81326 ታህሳስ ዐ7 ቀን 2ዐዐ2 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ጸንቷል፡፡

2.   በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

ት ዕ ዛ ዝ

ይህ ችሎት የካቲት 18 ቀን 2ዐዐ2 ዓ/ም ሰጥቶት የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ፍ/ዘ

 

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s