ክስ የማቅረብ መብትና የማስረዳት ጫና


የሰበር መዝገብ ቀጥር 44008

መጋቢት 28 ቀን 2002ዓ.ም

ዳኞች፡-

ተገኔ ጌታነህ

ሒሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የገንዘብ ኢኮኖሚ ልማት ሚ/ር

ተጠሪ፡- 1. ወ/ሮ ፍቅሬ አድርሴ

2. ወ/ሮ ሙሉእመቤት አፈወርቅ

3. አቶ ዮሴፍ ጃባ

ፍ ር ድ

አመልካች በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የመ/ቤቱ ካፍቴሪያ ገንዘብ ያዥ ሆነው ሲሰሩ ብር 4,994.74 በማጉደላቸውና 3ኛ ተጠሪ የ2ኛ ተጠሪ ዋስ በመሆናቸው ገንዘቡን እንዲከፍሉ ክስ ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቱ አመልካች ክስ በቀረበበት ንብረት ላይ መብት ወይም ጥቅም የለውም በማለት ክሱን ውድቅ በማድረጉና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ውሳኔውን በማጽናቱ የቀረበ የሰበር አቤቱታ ነው፡፡

አመልካች 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች በአመልካች መ/ቤት ካፍቴሪያ ገንዘብ ያዥ ሆነው ሲሰሩ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን ገንዘብ በማጉደላቸውና 3ኛ ተጠሪም የ2ኛ ተጠሪ ዋስ በመሆናቸው ሁሉም በአንድነትና በነጠላ ገንዘቡን እንዲከፍሉ በመጠየቅ በማስረጃነትም የሒሳብ ምርመራ አያይዟል፡፡ ተጠሪዎች ቀርበው ሒሳቡ የተሰራው እነሱ በሌሉበት መሆኑን ገልፀው ገንዘቡንም አላጎደልንም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ካፍቴሪያው የሰራተኞች መረዳጃ እድር በቅርብ አገልግሎት ለማግኘት ሲሉ ፈቃደኛ የሆኑ ሰራተኞች በግል ሐሳባቸውና በግል ገንዘባቸው የሚያቋቁሙት የራሱ መተዳደሪያ ደንብ የሚኖረው እንጂ የአመልካች ንብረት ስላልሆነ አመልካች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ መሠረት ክሱ ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ ፍ/ቤቱ ውሳኔውን አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ የአመልካች ቅሬታም ካፍቴሪያው የአመልካች አይደለም በሚል ተጠሪዎች ያቀረቡት ክርክር አልነበረም፣ የሰራተኞች እድር ካፍቴሪያውን በውክልና እንዲያስተዳድር በውል የተረከበው በመሆኑ በንብረቱ ላይ መብት የላችሁም ልንባል አይገባም የሚል ነው፡፡ ችሎቱም አመልካች በንብረቱ ላይ መብት የለውም በሚል የተጠሰውን ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት ተጠሪዎች መልሳቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም መዝገቡን ከተያዘው ጭብጥ አኳያ መርምሯል፡፡

በዚህ መዝገብ አከራካሪ የሆነው አመልካች ገንዘብ ጎደለበት በተባለው ካፍቴሪያ ላይ መብት አለው የለውም የሚለው ነው፡፡ ተጠሪዎች በስር ፍ/ቤት ለቀረበባቸው ክስ ገንዘቡን አላጎደልንም ከማለት ባለፈ አመልካች በካፍቴሪያው ላይ መብት ወይም ጥቅም የለውም በማለት አልተከራከሩም፡፡ ፍ/ቤቱም አመልካች በንብረቱ ላይ መብት የለውም ያለው የሒሳብ ምርመራ ውጤቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚ/ር ሰራተኞች መረዳጃ እድር ካፍቴሪያ ስለሚልና የሰራተኞች መረዳጃ እድር ደግሞ በቅርብ አገልግሎት ለማስገኘት ሲሉ ፈቃደኛ የሆኑ ሰራተኞች በግል ሐሳባቸውና በግል ገንዘባቸው የሚያቋቁሙት የራሱ መተዳደሪያ ደንብ የሚኖረው ነው የሚለውን ግምት በመውሰድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በእርግጥም ካፍቴሪያው የሰራተኞች መረዳጃ እድር እንጂ የአመልካች ስላለመሆኑ የቀረበለት ማስረጃ  የለም፡፡ ፍ/ቤቱ ተጠሪዎች ያላነሱት የፍሬ ነገር ክርክር እራሱ አንስቶ መወሰኑ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 182/2/ን የሚቃርን ነው፡፡ ምናልባት ፍ/ቤቱ በክርክሩ ሒደት አመልካች በንብረቱ ላይ መብት ያለው መሆን አለመሆኑ አጠራጣሪ ሆኖ ቢያገኘው እንኳን ከግራ ቀኙ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ወይም ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የሚረዳው ከሆነም አስፈላጊው ማስረጃ እንዲቀርብ በማድረግ ጉዳዩን አረጋግጦ መወሰን ይገባው ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ ግን ንብረቱ አመልካች አይደለም ያለው የቀረበለት ተጨባጭ ማስረጃ ኖሮ ሳይሆን ካፍቴሪያው የራሱ መተዳደሪያ ደንብ ስላለውና በሒሳብ ምርመራ ውጤቱ ላይ የሰራተኞች መረዳጃ እድር ካፍቴሪያ ተብሎ የተገለፀው መጠቀሱ በመመልከት መረዳጃ እድር ምን እንደሆነ የራሱን ትርጉም በመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ፍሬ ነገር የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሳይቀርብ ወይም እንዲቀርብ ሳይደረግ ካፍቴሪያው የመረዳጃ እድሩ እንጂ የአመልካች አይደለም በሚል ፍ/ቤቱ የደረሰበት መደምደሚያ የሙግት ሥርዓትን ያልተከተለ አካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ው ሳ ኔ

1.       የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 17498 ህዳር 4 ቀን 2000ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 61879 ጥር 22 ቀን 2001ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

2.       አመልካች ክርክር ባስነሳው ሐብት ላይ ጥቅም ወይም መብት አለው? የለውም? በሚለው ነጥብና በፍሬ ጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙ የሚያቀርቡትን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 341/1/ መሠረት ጉዳዩን ለፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መልሰናል፡፡

3.       ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ሶ/በ

1 Comment

  1. mulugeta yalew says:

    በመጀመሪያ የከበረ ሰላምታ እያቀረብኩ ፕሮግራማችሁ እጅግ በጣም ድንቅ የሆነ website እና ከ2 ዓመት በፊት በFm ፕሮግራም እከታተላችሁ ነበር እናም በጣም የሚገርም እና በጣም አከራካሪ ፕሮግራማችሁ ሳላደንቅላላችሁ አላልፍም እውነቴነው ትለቅ ተቋም መስራት ከሚችለው በላይ አዘጋጅታችሁ ስላቀረባችሁለን ደግሜ ምስጋናዬን አቅርብላችኋለው…
    ሙሉጌታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s