የመድን ሰጪ የተጠያቂነት መጠን (የሰበር ውሳኔ)


የሠ/መ/ቁጥር 43362

ህዳር 30 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡-

1. መንበረፀሐይ ታደሰ

2. ሐጎስ ወልዱ

3. ሂሩት መለሰ

4. ታፈሰ ይርጋ

5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንሹራንስ ኩባንያ – የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ መድን ድርጅት – የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የኢንሹራንስ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአሁኑ ተጠሪ የመድን ሽፋን በሠጠው መኪና ላይ ጉዳት አድርሷል በተባለው የመኪና ባለንብረትና አሽከርካሪ ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ተጠሪ መድን በሠጠው መኪና ጉዳት አድርሷል ለተባለው መኪና የመድን ሽፋን ሰጪ በመሆኑ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ ጣልቃ ገብቶ ተከራክሯል፡፡

አመልካች በክርክሩ ገብቶ የደንበኛው መኪና ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ያለመሆኑን፣ በወቅቱ ፕላኑን ያነሳው ትራፊክ ሁለት የአደጋ ቦታዎችን የመዘገበና ይህም አግባብ አለመሆኑን፣ ተጠሪ በደንበኛው ላይ የደረሰው ጉዳት ሙሉ ጉዳት (Total Damage) ነው በማለት በግሉ ከአደጋው በኋላ ከራሱ ደንበኛ ጋር ውል በመፈፀም የከፈለው ገንዘብ አግባብነት የሌለው መሆኑን እንዲህ ከሆነም ጉዳት የደረሰበትን የመኪና አካል ለተጠሪ ማስረከብ ሲገባው በፈለገው ዋጋ መሸጡ አግባብነት የሌለው መሆኑንና ይህ ሁሉ የሚታለፍ ቢሆን እንኳ አመልካች በሰጠው የመድን ሽፋን ልክ ብቻ ኃላፊ እንደሚሆን በመግለፅ ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የአመልካች ደንበኛ ለጉዳቱ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ ተጠሪ ብር 107,853.50 ከእነ ወለዱ ክሱ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ተጠናቆ እስኪከፈል ድረስ በባንክ ሂሳብ ወለድ መሰረት ታስቦ፣ የጠበቃ አበል አስር ፐርሰንት የዳኝነትን ጨምሮ በአመልካች እንዲከፈለው ሲል ወስኗል፡፡ ጉዳዩ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ቀርቦም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ የካቲት 03 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምከንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የአመልካች ደንበኛ ለጉዳቱ ኃላፊ ናቸው የተባሉት ያላግባበ መሆኑንና አመልካች ከመድን ሽፋን በላይ እንዲከፍል መወሰኑ ስህተት መሆኑን ዘርዝረው መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ከሠጠው የመድን ሽፋን በላይ እንዲከፍል የተሠጠው ውሳኔ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎ የተጠሪ ነገረ ፈጅ ነሐሴ 18 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ ሦስት ገፅ ማመልከቻ መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የመድን ሽፋን መጠኑን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ አዲስ ክርክር መሆኑን በመግለፅ የአመልካች ክርክር ውድቅ እንዲሆን የተከራከሩ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም የአመልካች ደንበኛ ለጉዳቱ ኃላፊ ተብሎ መወሰኑ የሚነቀፍ አለመሆኑን በመዘርዘር መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአመልካች ጠበቃም ነሐሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ የመልስ መልስ ማመልከቻ የመድን ሽፋን መጠኑን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት አንስተው የተከራከሩበት ነጥብ መሆኑን በመግለፅ የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ቀርቦ ሊተይ ይገባዋል ተብሎ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

አመልካች የደንበኛውን ለጉዳቱ ኃላፊነት በተመለከተ ያቀረበው ቅሬታ ከግራ ቀኙ ወገኖች ከቀረበው ማስረጃ አንፃር ታይቶ እና ማስረጃውም ተመዝኖ እልባት ያገኘ ሲሆን ይህ ችሎት የበታች ፍርድ ቤቶች የሠጡትን ውሳኔ ማረም የሚችለው በሕግ አተረጓጎም ረገድ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት መኖሩ ሲረጋገጥ በመሆኑ፣ የአመልካች ቅሬታ በማስረጃ አመዛዘን ረገድ የስር ፍርድ ቤት ስህተት ፈፅሟል የሚል ይዘት ያለው በመሆኑ ይህ ችሎት የሚመረምረው ነጥብ ስላልሆነ ታልፏል፡፡

በዚህ ችሎት ሊታይ የሚገባው የአመልካች የኃላፊነት መጠን ነው፡፡ ተጠሪ አመልካች የኃላፊነት መጠኑን በስር ፍርድ ቤት ያላነሳው አዲስ ክርክር በመሆኑ በዚህ ችሎት ሊታይ አይገባውም በሚል ተከራክሯል፡፡ ሆኖም አመልካች በደንበኛው ለጉዳቱ ኃላፊነት ላይ ተገቢነት አላቸው ያላቸውን መከራከሪያ ነጥቦችን በማንሳት ከተከራከረ በኋላ ደንበኛው ኃላፊነት አለው የሚባል ቢሆን እንኳ የአመልካች ኃላፊነት በመድን ውሉ ላይ በተጠቀሰው መጠን ብቻ ስለመሆኑ ገልፆ መከራከሩን በስር ፍርድ ቤት በጣልቃ ገብነት ሲከራከር በሰጠው መከላከያ መልስ ማመልከቻ መግለፁን ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም ተጠሪ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው ክርክር አዲስ ክርክር ነው በማለት ያቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት የሌለው ሆኖ አግኝተናል፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ለደንበኛው የሠጠው የመድን ሽፋን ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺህ ብር) መሆኑን ገልፆ የሚከራከር መሆኑን ተገንዝበናል፤ የመድን ሽፋን ፖሊሲውንም ተመልክተን መጠኑ በአመልካች የተገለፀው መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ በመሠረቱ በአመልካች እና በደንበኛው መካከል ያለው ግንኙነት በውል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ መድን ሠጪው የሆነው አመልካች ሊገደድ የሚችለው የካሳ መጠን በመድን ውሉ ላይ የተመለከተውን ያህል ነው፡፡ የንግድ ሕግ ቁጥር 665(2) ድንጋጌም ኢንሹራንስ ሰጪው የሚከፍለው ገንዘብ መጠን በውለታው ላይ ከተጠቀሰው አይበልጥም በማለት አስገዳጅነት ባለው ኃይለ ቃል ደንግጓል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን አመልካች ኃላፊነት አለበት የተባለው ይህንኑ ድንጋጌ ባላገናዘበ መልኩ በመድን ውሉ ላይ ከተመለከተው መጠን በላይ ሆኖ ስለአገኘነው የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1.   በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 11919 ሚያዝያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም ተሠጥቶ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 66756 ሕዳር 05 ቀን 2001 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.   አመልካች ሊገደድ የሚገባው በመድን ውሉ በገባው ሽፋን መጠን በመሆኑ ለተጠሪ ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) የስር ፍርድ ቤት ውሣኔ ከሠጠበት ቀን ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰበ 9% (ዘጠኝ በመቶ) ሕጋዊ ወለድ ጋር ይክፈል ብለናል፡፡

3.   አመልካች ኃላፊ ነው ተብሎ በዚህ ፍርድ ቤት በተወሰነው መጠን መሰረት ወጪና ኪሳራን በተመለከተ በበታች ፍርድ ቤቶች የተሠጡት ውሳኔዎች አልተነኩም፡፡

4.   በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዝግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s