የደመወዝ ማስተካካያ ጥያቄ (የሰበር ውሳኔ)


የሰበር መ/ቁ 42923

ህዳር 22 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡-

1. መንበረፀሐይ ታደሰ

2. ሐጎስ ወልዱ

3. ሂሩት መለሰ

4. ታፈሰ ይርጋ

5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን – የቀረበ የለም

ተጠሪ፡– ወ/ሮ ነጃት አባስ – ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996ን መሰረት ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ናቸው፡፡ የተጠሪ ክስ ይዘት፤ የሁለት ዓመት የሥራ ልምድ የሚጠይቅ በሙሉ ስታትስቲሺያን የሥራ መደብ ተቀጥረው በወር ብር 1971.00 (አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ አንድ ብር) ደመወዝ እየተከፈላቸው በመስራት ላይ የሚገኙ መሆኑን፣ አነስተኛ የሥራ ልምድ ያላቸው እና ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ሌሎች ሠራተኞች ከፍ ያለ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ገልፀው ድርጊቱ ለአንድ ሥራ እኩል ክፍያ የሚለውን መርህ የሚጥስ በመሆኑ አመልካች የወር ደመወዙን ብር 2366.00(ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ ስድስት ብር) እንዲያደርግላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

አመልካችም በተከሳሽነቱ ቀርቦ በሠጠው መልስ ተጠሪ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብት ወይም ጥቅም የሌላቸው መሆኑንና ጥያቄአቸውም በይርጋ የታገደ መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት፣ በፍሬ ነገር ረገድ ደግሞ የደመወዝ ልዩነት የተደረገው መመሪያውን መሰረት በማድረግ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 14(1/ረ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በዋቢነት በመጥቀስ የአመልካች አሰራር ህገ ወጥ ነው በማለት ለተጠሪ የደመወዝ ማስተካከያ በማድረግ በፔሮል ላይ ሊተክል ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ይግባኙን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ሠርዞታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረ ፈጅ ጥር 19 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሦስት ገፅ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የስር ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የአዋጅ ቁጥር 337/96 አንቀፅ 14(1/ረ) አሰሪው መመሪያውን መሰረት በማድረግ ለፈፀመው ተግባር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የስር ፍርድ ቤት አመልካች መስሪያ ቤት ከዘረጋው የእድገት አሰጣጥ ሥርዓት አልፎ ለተጠሪ የወሰነው የደመወዝ መጠን መነሻን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ ጉዳዩ እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪ ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ ማመልከቻ መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በተመሳሳይ ደረጃ በሚገኙ ሠራተኞች መካከል የሚፈጠር የደመወዝ ልዩነት (Equal Pay Discrimination) የተከለከለ ነው የሚለውንና ኢትዮጵያ ያፀደቀችውን ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንን መሰረት ያደረገ ስለሆነ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለውም በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅ በበኩላቸው ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገፅ ማመልከቻ የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ ቀርቦ ሊመረመር ይገባዋል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አኳያ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካች ድርጅት በስታትስቲሽያንነት ተቀጥረው የሚሰሩ መሆኑን፣ ቅጥሩም በሙሉ ስታትስቲሽያን የስራ የማዕረግ መፈፀሙን በተጠሪና በሌሎች ሠራተኛች መካከል የደመወዝ ልዩነት የተፈጠረው እነዚህ ሠራተኞች ምንም የስራ ልምድ በማይጠይቅ በመለስተኛ ስታትሺያን የስራ መደብ ተቀጥረው ከቆዩ በኋላ በዚህ የስራ መደብ የተቀጠሩ የዲግሪ ምሩቃን ሰራተኞች ወደሚቀጥለው የስራ መደብ የሚያድጉበትን ሁኔታ አመልካች በመመሪያ መወሰኑንና በዚህ መመሪያ መሰረትም ከተጠሪ ጋር ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ የዲግሪ ምሩቃን ከተጠሪ የተለየ ደመወዝ የሚከፈላቸው መሆኑን ነው፡፡

በመሰረቱ ሴቶች ሠራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀፅ 42(1/መ) ድንጋጌ የሚያሳይ ሲሆን ኢትዮጵያ የተቀበለችው አለም አቀፍ ኮንቬንሽንም ይህንኑ ያስገነዝባል፡፡

የስር ፍርድ ቤት የአመልካችን ክርክር ውድቅ ሲያደርግ መሰረት ያደረገው የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14(1/ረ) ሲሆን የዚህ ድንጋጌ ይዘት ሲታይ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በሐይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት እና በሌሎችም ሁኔታ በሠራተኞች መካከል ልዩነት ማድረግ ለማንኛውም አሠሪ ሕገወጥ ድርጊት ነው የሚል ነው፡፡ የድንጋጌው እንግሊዘኛ ትርጉሙም “discriminate between workers on the basis of nationality, sex, religion, political outlook, or any other conditions shall be unlawful for an employer.” በሚል ተቀምጧል፡፡

ከድንጋጌው ውስጥ “…በሌሎችም ሁኔታ…” ወይም “…. Any other conditions….” የሚለው ሐረግ ጠቅላላ ቃል መሆኑ ግልጽ ሲሆን እንዲህ በሆነ ጊዜ ቃሉን ህግ አውጪው የተጠቀመው ምንን ለማመላከት ነው የሚለው ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ሲሆን የህግ አተረጓጎም መርሆዎችን መሰረት በማድረግም ምላሹን ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት ከጠቅላላው ቃል በፊት የተዘረዘሩት የቃልት ዝርያ የሚያሳዩትን ሁኔታ በመመልከት ጠቅላላ ቃል ሌሎች ያልተዘረዘሩትን ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸውን ቃላት ለመጠቀም ታስቦ የተቀመጠ ነው በሚል እንደሚተረጎም ተቀባይነት ያላቸው የህግ አተረጓጎም መርሆዎች ያስገነዝባሉ፡፡ በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14(1/ረ) ድንጋጌ ስር “በሌሎች ሁኔታም” የሚለው ቃል ከቃሉ በፊት የተቀመጡትን የልዩነት ማድረጊያ ድርጊቶችን ዓይነት የሚመለከት እንጂ አሰሪው የእድገት አሠጣጥ ሥርዓቱን በመመሪያ ዘርግቶ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ሠራተኞች መስፈርቱን ካላሟሉ ሰራተኞች የተለየ ክፍያ እንዲከፈል የሚያደርግበትን አሰራር የሚመለከት አይደለም፡፡ መመሪያው በሕገ መንግስቱ፣ በዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14(1/ረ) ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በተጠሪና በሌሎች ሰራተኞች መካከል የደመወዝ ልዩነት ያደረገ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡ መመሪያው መድሎን ለመከላከል የማያስችል ነው ሊባል የሚችልበትን ሕጋዊ ምክንያትም አላገኘንም፡፡ ሲጠቃለልም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ከላይ በተመለከቱት ህጋዊ ምክንያቶች መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም መሰረት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሳ ኔ

1.   በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 23005 ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም ተሠጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 70763 ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2.   አመልካች በተጠሪና በሌሎች ሠራተኞች መካከል ለተመሳሳይ ሥራ የደመወዝ ልዩነት ያደረገው በሕግ የተከለከሉ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ባለመሆኑ ለተጠሪ ብር 2366.00 በፔሮል እንዲተክል የሚገደድበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ብለናል፡፡

3.   ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s