ተገማችነትና ሰበር ሰሚ ችሎት: የስራ ክርክር የዳኝነት አካላት ስልጣን በተመለከተ ከ1997-2001 ዓም ድረስ በሰበር ችሎት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ ዳሰሳ


ተገማችነትና ሰበር ሰሚ ችሎት: የስራ ክርክር የዳኝነት አካላት ስልጣን በተመለከተ ከ1997-2001 ዓም ድረስ በሰበር ችሎት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ ዳሰሳ

ክፍል አንድ

አብረሃም ዮሐንስ

”ማወቅ የምፈልገው ሕጉ ምን እንደሆነ ሳይሆን ዳኛው ማን እንደሆነ ነው። ‘

(ሮይ ኮህን–አሜሪካዊ ጠበቃ)

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጥ የህግ ትርጓሜ በኢትዮጽያ ውስጥ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት ተሰጥቶታል። [አዋጁ ቁጥር 4541/97 አንቀጽ 2(1)] ሆኖም ችሎቱ በራሱ ውሳኔ ሳይታሰር ”በሌላ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል”

 

የችሎቱ ውሳኔዎች በስር ፍርድ ቤቶችና በዜጋው ዘንድ ተገማችነት እንዲኖራቸው በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ለሆነ ጊዜ ፀንተው ሊቆዩ ይገባል። ፀንተው መቆየታቸው ከተገማችነት ባሻገር የሰበር ውሳኔ ከስር ፍርድ ቤቶች በተለየ መልኩ የተነሳውን የህግ ጭብጥና የህግ ትርጉም ጥልቅ ፍተሻ እና ምርመራ ተደርጎበት እልባት የተሰጠው መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።  ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በተለይ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ጋር ተያይዞ ለአንድ የህግ ድንጋጌ የተሰጠው ትርጓሜ ሊቀየር ሊሻሻል ወይም በተለየ መንገድ ሊቃኝ ይችላል ስለሆነም የዳኛ ግዴታ ህግና ማስረጃውን ብቻ ሳይሆን ጊዜውም ጭምር መመርመር ነውና የአቋም ለውጥ ማድረግ የግድ ይላል።

 

ሆኖም በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጓሜ ሲሰጥ የመጀመሪያው የህግ አተረጓጎም ትክክል እንዳልነበር በማመን መግለጽ ያስፈልጋል በመቀጠልም ከዱሮው የተለየው አዲሱ ትርጓሜ በምን ረገድ የተሻለ እንደሆነና ተቀባይነት እንዳገኘ አሳማኝ ምክንያቶችን መስጠት ያስፈልጋል።

 

ይህ ሳይሟላ የአቋም ለውጥ በዝምታ የሚከናወን ከሆነ በስር ፋርድ ቤቶች ላይ ውዥንብር በመፍጠር በዜጋውም ላይ ትልቅ የፍትሕ ኪሳራ ያደርሳል። የዝምታ ለውጡ በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ በአጠቃላይ በፍትሕ አስተዳደር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

በሰበር ችሎት የህግ ትርጓሜ ተሰጥቶባቸው በቀጣይነት በችሎቱ በራሱ በተለያዩ ጊዜያት ወጥነት የሌለው ውሳኔ ከተሰጠባቸው የተዘበራረቀ አቋም ከተያዘባቸው ጉዳዮች መካከል የግል የስራ ክርክር እና የወል የስራ ክርክር ምንነትና ልዩነት ከዚህ ጋር ተያያዞም የፍርድ ቤት እና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን በዋነኛነት ሊጠቀስ ይችላል። በዚህ ነጥብ ላይ ከ1997 ዓ.ም እሰከ 2001 ዓ.ም ድረስ እርስ በእርስ የሚጣረሱ የተለያዩ ውሳኔዎች በሰበር ችሎት ተሰጥተዋል ከዚህ በታች ተመርጠው የተዳሰሱት የሰበር ውሳኔዎች ይህንኑ እውነታ በገሃድ የሚያሳዩ ናቸው።

 

1997 ዓ.ም “የኬኬ መለኪያ”

በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት የክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአዋጁ አንቀጽ 138 ንዑስ አንቀጽ1 ላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎች ተመሳሳይ የግል የስራ ክርክር ጉዳዮች” የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ደግሞ በአንቀጽ 142 (1) (ሀ) የተዘረዘሩትንና ”ሌሎች ተመሳሳይ የወልየስራ ክርክር ጉዳዮች” አስመልክቶ በየፊናቸው የዳኝነት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። ቦርዱ ቋሚና ጊዜያዊ ተብሎ የተከፈለ ሲሆን የጊዜያዊ ቦርዱ ስልጣን ደመወዝና ሌሎት ጥቅሞች አወሳሰን የሚመለከቱ የወል የስራ ክርክር ጉዳዮች ላይ የተገደበ ነው ።

ከዚህ በተጨማሪ በቋሚና በጊዜያዊ ቦርዱ ስልጣን ስር በሚያርፍ የወል የስራ ክርክር ላይ በአንደኛው ወገን አቤቱታ ሲቀርብ ክርክሩ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር ከሚመደብ ወይም ተከራካሪዎች በሚመርጡት አስማሚ አማካይነት እልባት ሊሰጥ ይችላል። ሆኖም የአስማሚው ስልጣን ተከራካሪ ወገኖችን ለማስማማት በመጣር ክርክሩ እልባት እንዲያገኝ የተቻለውን ያህል ማድረግ ነው። አስማሚው ተከራካሪዎችን ማስማማት ካልቻለ የውሳኔ ሓሳቡን ለሚኒስቴሩና ለተከራካሪው ወገኖች ሪፖርት ያቀርባል።

ለብዙ ጊዜያት የፍርድ ቤትና የቦርድ ስልጣን ብዙዎችን ሲያወዛግብ ቆጥቷል።  ዋነኛ የችግሩ ምንጭም ለግል እና ለወል የስራ ክርክር የሚሰጠው የተለያየ የህግ አተረጓጎም እንደሆነ በፍርድ ቤት ሆነ በቦርድ ከሚሰጡት ወጥነት የሌላቸው የተለያዩ ውሳኔዎች ለመረዳት ይቻላል።

ይህን አወዛጋቢ የስልጣን ክርክር የሰበር ሰሚ ችሎት ሐምሌ 27 ቀን 1997  ዓ.ም በሰበር መዝገብ ቁጥር ከአሁን በኋላ (ሰ/መ/ቁ በሚል የሚገለጽ) 18180 በሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ ምላሽ ሰጥቶበታል። በሰ/መ/ቁ 18180 ተከራካሪዎቹ አመልካች የኬ.ኬ ብርድልብስ ፋብራካ መ/ሰ/ማ (56 ሰዎች) (መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር) እና ተጠሪ የኬ.ኬ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትራ ነበሩ።

የጉዳዩን አመጣጥ ከሰበር ውሳኔው ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው አመልካቾች የተወሰደባቸውን የቅነሳ እርምጃ በመቃወም ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው ቦርዱም ቅነሳው ህገ ወጥ ስለሆነ ወደስራ ይመለሱ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን በመቃወም በተጠሪ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት (ከአሁን በኋላ ፌ/ከ/ፍ/ቤት በሚል የሚገለጽ) ቦርዱን በጉዳዩ ላይ የዳኝነት ስልጣን የለውም በማለት የቦርዱን ውሳኔ ሽሮታል።

በመቀጠልም አመልካቾች የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል የሰበር አቤቱታ አቅርበው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮ የቦርዱን ውሳኔ አጽንቶታል በዚሁ መሰረት ክርክሩን አይቶ መዳኘት የቦርዱን ስልጣን እንደሆነ በችሎቱ አቋም ተወስዶበታል ችሎቱ እዚህ አቋምና መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ሰፊ ትንተና በመስጠት የወል የስራ ክርክር ከግል የስራ ክርክር የሚለይባቸውን ሁለት ነጥቦች አስቀምጧል።

በዚሁ መሰረት የግል የስራ ክርክርን ከለል የስራ ክርክር ለመለየት

  1. ቁጥር እንደመስፈርት ሊወሰድ አይገባም
  2. የወል የስራ ክርክር ማለት ውጤቱ ከግል አልፎ የሰራተኞችን የጋራ መብትና ጥቅም የሚነካ ሲሆን የግል የስራ ክርክር ደግሞ በተከራካሪው ሰራተኛ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲቀር ነው።

ችሎቱ ያስቀመጠው መለኪያ ተቀባይነት በተለይም ቅነሳን በተመለከተ ለሚቀርብ ክርክር ተፈፃሚ ለመሆን የመቻሉ ጥያቄ በተመለከተ ራሱን የቻለ ትንተና የሚያስፈልገው በመሆኑ አሁን ወደዛ መግባት አያስፈልግም  ነው።

ችሎቱ ያስቀመጠው መለኪያ ምናልባት በሌሎች ቅነሳን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆናል። ሆኖም ከቅነሳ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስላለመኖሩ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ቅነሳን በተመለከተ የሚነሳው መሰረታዊ ነጥብ “በህግ በተቀመጠው አነጋገር ቅነሳ አለ ወይስ የለም?” የሚል እንጂ የመላውን የሰራተኞችን የጋራ መብትና ጥቅም መንካቱና አለመንካቱ አይደለም በህጉ ላይ የተቀመጠው የቅነሳ መስፈርት እስከተሟላ ድረስ የመላውን ሰራተኛ የጋራ መብትና ጥቅም ተነካም አልተነካም ስልጣኑ ሁል ጊዜ የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ነው። ስለሆነም መሰረታዊው ጭብጥ በአንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በተቀመጠው አነጋገር ለቅነሳ የተሰጠው ፍቺ ተሟልቶ የመገኘቱና አለመገኘቱ ላይ ነው።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በሰ/መ/ቁ 18180 የተቀመጠው መለኪያ ትክክለኛነት መመዘን ሳይሆን በቀጣይ ጊዜያት ይኸው መለኪያ እስከመኖሩ ተረስቶ ተቃራኒ ውሳኔዎች በራሱ በሰበር ችሎት መሰጠታቸውን ማሳየት እንደመሆኑ ለወል የስራ ክርክርና ለግል የስራ ክርክር የተሰጠው ፍቺ ይዘት ላይ የሚደረግ ጠለቅ ያለ ፍተሻ አይኖርም።

ከተገማችነት አንጻር በሰ/መ/ቁ 18180 የተሰጠው ውሳኔ በቦርዱ እና በፍርድ ቤት ይስተዋሉ የነበሩትን የተለያዩ ውዥንብሮች በማጥራት ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። መለኪያው ማንም ሰው በሚረዳው መልኩ የተቀመጠ እንደመሆኑ ሰራተኛውም ክሱን በየትኛው የዳኝነት አካል ማቅረብ እንደሚኖርበት አስቀድሞ በእርግጠኝነት እንዲያውቅ ያስችለዋል።

ከዚህ አንፃር በስ/መ/ቁ 18180 የተሰጠው ውሳኔ የፍርድ ቤትና የቦርድ ስልጣን በተመለከተ ወጥነትና ተገማችነት እንዲፈጠር የመሰረት ድንጋይ የጣለ ውሳኔ ተበሎ ሊወደስ ይችላል።

1998 ዓ.ም እስከ 1999 ዓ.ም የችግሩ ፍንጭ መታየት ጀመረ

በሰ/መ/ቁ 18180 ”የኬኬ መለኪያ‘ በግልጽ ተለይቶ ከተቀመጠ ወዲህ ባሉት ዓመታት ውስጥ በሰበር ችሎት ከሞላጎደል በሁሉም ተመሳሳይ ጉዳዮች ወጥነትን የተከተለ አካሄድ ሰፍኖ ነበር።  የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ስልጣንን አስመልክቶ በ1998 ዓ.ም እና 1999 ዓ.ም  የተሰጡ ውሳኔዎች ”የኬኬ መለኪያ”ን መሰረት ያደረጉ ናቸው።  ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ እንችላለን

  • የኮተቤ ብረታብረት መሣሪያዎች ፋብሪካ እና አቶ ስንታየሁ ዋለ (ሰ/መ/ቁ 23439-ግንቦት 28-1998 ዓ.ም)
  • የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኀይል ኮርኮሬሽን እና አቶ ገነነ ታደሰ (ሰ/መ/ቁ 21913-ግንቦት 25 ቀን 1998 ዓ.ም)
  • የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት እና 1. አቶ ስንታየሁ ታደሰ 2. አቶ ደገፋው ዳምጠው (ስ/መ/ቁ 21008-ግንቦት 25 ቀን 1998 ዓ.ም)
  • የኢት/ብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ እና አቶ በቀለ ነጋሽ (ስ/መ/ቁ 22094-የካቲት 22-1998 ዓ.ም)
  • የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሐይል ኮርኮሬሽን እና አዱኛ ገመዳ (ስ/መ/ቁ 15531-የካቲት 6-1999 ዓ.ም)
  • ግዮን ሆቴሎች ድርጅት እና ወ/ሮ ስለእናት ወርቅነህ (ስ/መ/ቁ 6653 መጋቢት 27-1919 ዓ.ም)

ከላይ በተጠቀሱት በሰበር የታዩ መዝገቦች መነሻቸው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ሲሆን በአብዛኛዎቹ ቦርዱ ስልጣን አለኝ በሚል ብይን የሰጠባቸው ሲሆኑ በቀሪዎቹ ደግሞ ስልጣኑን ሳይመረምር በፍሬ ነገር ላይ ውሳኔ የሰጠባቸው ናቸው። በሁሉም መዝገቦች ከቦርዱ ይግባኝ የቀረበለት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቦርዱን ውሳኔ አፅንቶታል።  በሁሉም መዝገቦች የሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤትና የቦርዱን ውሳኔ በመሻር ቦርዱ ስልጣን የለውም የሚል ውሳኔ ሰጥቷል።

ከላይ በተጠቀሱት መዝገቦች ላይ ለአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ የቀረቡት ጥያቄዎች የደረጃ እና የደመሞዝ ጭማሪ& በተመሳሳይ ደረጃ ላሉት ሠራተኞች የተሰጠው ደረጃ ይሰጠኝ& ቋሚ እንድንሆን ይወሰንልንልን እና ጥቅማጥቅም ስለተከለከልን ይሰጠን& የምሰራበት የስራ መደብ ከደመወዙ ጋር ይሰጠኝ& ከደረጃዬ ዝቅ ተደርጌአለሁ& የሰራ መደቡ እና ለቦታው የተመደበው ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ይስጠኝ& የሚሉ ነበሩ።

በኬ.ኬ መለኪያ መሰረት እነዚህ ጉዳዮች የተከራካሪዎችን የግል መብትና ጥቅም ለማስከበር የቀረቡ እንጂ ከውጤት አንፃር የሌሎች ሰራተኞችን የጋራ መብትና ጥቅም የማይነኩ ስለመሆናቸው በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል። በዚሁ መሰሪት የሰበር ችሎት ከላይ በተጠቀሱት መዝገቦች ላይ የአሰራና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን አልተሰጠውም በማለት የሰ/በ/ቁ 18180 መሰረት አድርጉ መወሰኑ አግባብነት ነበረው። በተለይም የችሎቱ ውሳኔዎች ወጥነትን የተከተሉ መሆኑ ከተገማችነት አንፃር በጎ ጅምር ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

ሆኖም ይህ የወጥነት በጎ ጅምር በሰ/በ/ቁ 18180 መሰረት ላይ ቀጥ ብሎ ለመተከል የቻለ አልነበረም። በ1998 እና በ1999 ዓ.ም የተወሰኑ መተጣጠፎች ተስተውለዋል።

የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 18180 ካስቀመጣቸው ነጥቦች አንዱ የስራ ክርክርን የግል ወይም የወል ብሎ ለመፈረጅ የሰራተኞች ቁጥር እንደመስፈርት ሊያገለግል አለመቻሉ ነው። ስለሆነም ክሱ የቀረበው  በአስር ሆነ በአንድ ሰራተኛ የጋራ መብትና ጥቅም ላይ ውጤት የማያስከትል እስከሆነ ድረስ የግል የስራ ክርክር ነው።

ይህንኑ ሓሳብ በሚቃረን መልኩ በኢት/ንግድ ባንክ እና አቶ ግርማ ታከለ (8 ሰዎች) (ሰ/መ/ቁ 22038) ሰኔ ቀን 1998 ዓ.ም በሰበር ችሎት ውሳኔ ተሰጥቷልበአንድ ተጠሪዎች በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ የስራ ደሪጃችን ከደረጃ 4 ወደ ደረጃ 3 ዝቅ ተደርጎ በተመሳሳይ ደረጃ 4 የነበሩት ባልደረቦቻችን ወደ ደረጃ 5 ያደጉ በመሆኑ ደረጃ 5 የስራ ደረጃ እንድናድግ ይወሰንልን የሚል ነው። ጥያቄው በሰ/በ/ቁ 18180 መለኪያ የግል የስራ ክርክር ቢሆንም ጥየቄው በነጀመሪያ የቀረበለት ቦርድ በጉዳዩ ላይ ስልጣን እንዳለው ግምት በመውሰድ በፍሬ ነገሩ ላይ የተጠሪዎችን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል።  ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከ/ፍ/ቤትም ቦርዱ ስልጣን እንደሌለው በውሳኔው ላይ ሳያመለክት የስልጣን ጥያቄውን በዝምታ በማለፍ ተጠሪዎች የጠየቁት የደረጃ 5 እንዲሰጣቸው ውሳኔ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ መልኩ በሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎትም የቦርዱን ውሳኔ ሽሮ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በማሻሻል ተጠሪዎች ደረጃ 4 እንዲሰጣቸው የወሰነ ሲሆን ከመስረቱ ቦርዱ ጥያቄውን የተቀበለው የዳኝነት ስልጣን ኖሮት ነው? የሚለውን ጥያቄ ግን በዝምታ አልፎታል። ይህም በሌላ አነጋገር ቁጥር እንደመስፈርት መወሰድ የለበትም የሚለውን የሰ/መ/ቁ 18180 የሚያሻሽል ነው።

እዚህ ላይ አንድ ነገር አጥብቀን ልብ ልንል ይገባል። የሰበር ችሎት የዳኝነት ስልጣን በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጠው ስልጣንን አስመልክቶ በተከራካሪ ወገኖች ክርክር ቢቀርብለትም ባይቀርብለትም ነው ክርክር ቀረቦም አልቀረበም ሰበር ችሎት ቦርዱ ወይም ፍርድ ቤት ስልጣን የለውም ለማለት አያግዳውም ይህንንም በችሎቱ ከሚሰጡ ውሳኔዎች ለመረዳት የሚቻል ሲሆን በ2000 ዓ.ም በተሰጠ አንድ ውሳኔ ላይም ይኸው ነጥብ ግልጽ ተደርጎ ተቀምጧል። በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል እና እን አቶ ገዛኸኝ                    (3 ሰዎች) በሰ/መ/ቁ 35073 ጥቅምት 20 ቀን 2000 ዓ.ም በተሰጠው የሰበር ውሳኔ ”ስልጣንን በተመለከተ ከተከራካሪ ወገኖች ባይቀርብም “ፍርድ ቤት በራሱ አስተያየት ሊመለከተው እንደሚገባ” ተጠቅሷል።

ከዚህ አንቀጽ በሰ/መ/ቁ 22038 ላይ የስልጣን ጥያቄ በዝምታ መታለፉ በ8 ሰዎች የቀረበ የደረጃ እድገት ጥያቄ የወል የስራ ክርክር ተደርጎ ስለመቆጠሩ ማየት ይቻላል።

ታህሳስ 20 ቀን 1998 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሐይል ኮርኮሬሽን እና አቶ አንለይ ያየህ (27 ሰዎች) (ሰ/መ/ቁ 16648) በሰበር ችሎት የተሰጠው ውሳኔም በድጋሚ ተመሳሳይ ስህተት የተሰራበት እና ከሰ/መ/ቁ 18180 መለኪያ ጋር ያልተጣጣመ ነበር። በዚህ መዝገብ ላይ ተጠሪዎች በጌዶ ነቀምት ጊምቢ የትራንስሚሽን ዝርጋታ ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞች በመንግስት ትእዛዝ የሁለት እርክን ጭማሪ ተደርጎ ሆኖም እኛም በዚህ ውስጥ ብንሳተፍም ጭማሪ የተከለከለን በመሆኑ ጭማሪው ይሰጠን በማለት ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው ቦርዱም በኮርኮሬሽኑ የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ በፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።  ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የቦርዱን ውሳኔ ጉድለት የለበትም በማለት አጽንቶታል።

በመጨረሻም በሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ሰሚ ችሎት ክሱ በይርጋ ይታገዳል በማለት የቦርዱንና የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ የሻረው ሲሆን ከመሠረቱ ቦርዱ ጥያቄውን የተቀበለው ስልጣን ኖሮት ስላለመሆኑ ግን በዝምታ አልፎታል በመሆኑም በይዘቱ የግል የሆነው የስራ ክርክር እንድ የወል የስራ ክርክር ተቆጥሯል።

ሰበር ችሎት የይርጋ መቃወሚያው በቦርዱ ውድቀት የተደረገው በአግባቡ ስለመሆኑ ከመመረመሩ በፊት መጀመሪያውኑ ስልጣን እንደነበረው ሊመርመር ይገባ ነበር ከይርጋ ጥያቄ በፊት የዳኝነት ጥያቄ እልባት ማግኘት ይኖርበታል ይህም ሐሳብ በቸሎቱ ዘንድ ሳይቀር ተቀባይነትን አግኝቷል በመሪጌታ ልሣነ ወርቅ በዛብህ እና ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መካከል በነበረው የሰበር ክርክር (ስ/መ/ቁ 32279) ሰበር ችሎት ሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም በተሰጠው ውሳኔ ላይ ሰበር እንዲህ ብሎ ነበር።

”በመሰረቱ አንድ ፍ/ቤት የቀረበለትን ጉዳይ የመዳኘት ስልጣን ያለው መሆኑን ካላረጋገጠ የግራ ቀኙን ክርክር መመርመር አይጀምርም።”

ስለሆነም ቦርዱ የቀረበለትን የስራ ክርክር ምንም እንኳን በ27 ሰዎች የቀረበ ቢሆንም በይዘቱ የግል የስራ ክርክር ስለሆነ ዳኝነት ባልተሰጠው ጉዳይ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በሰበር ችሎቱ ተሽሮ ክርክሩ ስልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት ሊታይ ይገባው ነበር።

ዋናው ችግር የሰበር ችሉት በሰ/መ/ቁ 22038 እና ስ/መ/ቁ 16648 የግል የስራ ክርክር በአሰሪና ሰራተኛ ቦርድ ቀርቦ እያለ የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ በዝምታ ያለፈው መሆኑ አይደለም። እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ ሰበር  ችሎቱ ትክክል ሆነም አልሆነም ቢያንስ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሰበር አቋም በሌሎች መዝገቦች ላይ የታወቀ ይሆናል ነገር ግን ተመሳሳይ አቋም በሌሎች መዝገቦች ላይ አናገኝም።

በኦ/ብ/ክ/መ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን የጎጃ ገ/መ/ጥ/ ጽ/ቤት እና እነብረሃኑ አንቴ (33 ሰዎች) (ሰ/መ/ቁ 21956) መካከል በነበረው ክርክር በሰበር ችሎት በተሰጠው ውሳኔ ላልተወሰነ ጊዜ እንደተቀጠርኩኝ ይወሰንልኝ የሚል ጥያቄ የክስ ምክንያት እንደሌለው በተጨማሪም ጥያቄው (በ33 ሰዎች) ቢቀርብም የጋራ በሆነ የሠራተኞች መብትና ጥቅም ላይ አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ውጤት እንደማያስከትል በመግለጽ የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ጥያቄውን ተቀብሎ የመዳኘት ስልጣን እንደሌለው ተገልጿል።

በተጨማሪም በኪራይ ቤቶች አስተዳደር እና 1. አቶ ስንታየሁ ታደሰ 2. አቶ ደገፋው ዳምጠው (ሰ/መ/ቁ 21008) ግንቦት 25 ቀን 1998 ዓ.ም በሰበር ችሎት በተሰጠ ውሳኔ ቋሚ እንሁን ከሚል ጥያቄ ጋር ጥቅም ይሰጠን የሚል ክስ ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ የቀረበ ክስ በቦርዱ ስልጣን ስር እንደማይወድቅ በሰበር ችሎቱ ተመልክቷል።

በሰ/መ/ቁ 21956 እና ሰ/መ/ቁ 21008 ቦርዱ ስልጣን የለውም የተባለው ጉዳዩ ሰበር ላይ በደረሰ ጊዜ ሲሆን ስልጣንን አስመልክቶ ከታች ጀምሮ የተነሳ ክርክር የለም

ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀርባል

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s