የአንዲት አንቀጽ ስህተት: የወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን


‹‹በጣም ምርጥ የሆነው ህጎችን የመተርጎም ዘዴ ህጎችን እርስ በራሳቸው እንዲጣጣሙ ማድረግ ነው፡፡›› ይህ ዘመን አይሽሬ የህግ መርህ መጀመሪያ በተገለጸበት የላቲን ቋንቋ እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹Optimus interpretandi modus est sic leges interpretare ut leges legibus accordant.››

በማርቀቅ ሂደት ግድፈት ካልተፈጠረ በስተቀር አንድ ህግ ሲወጣ በውስጡ ያሉት አንቀጾችና ንዑስ አንቀፆች እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከሌሎች ህጎች ዝርዝር ድንጋጌዎች ጋር እንዲስማሙ ተደርጎ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ሃሳብ በህግ አተረጓጎም ሂደት ውስጥ ለዳኞች ትልቅ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ በማስማማት ወይም በማጣጣም መተርጎም ሲባል የአንድ ህግ አንቀጽ ከሌላ ህግ ጋር እንዲገጥም በማድረግ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ህጎች በቅርፅ ብቻ ሳይሆን በይዘትም ካልገጠሙ ተጣጣሙ አይባልም፡፡ ግጣም በጣዕም ካልታገዘ ህግን የመተርጎሙ ሂደት ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ጣዕም የሚሰጥ መድረሻ ተፈልጎ ሲገኝ ሂደቱም ያበቃል፡፡

ህዳር 9 ቀን 2001 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ አንድ ውሳኔ ከላይ ለቀረበው የማይጨበጥ የሚመስል ሐሳብ ተጨባጭ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡

በሰበር የታየው ክርክር የወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣንን የሚመለከት ሲሆን ተከራካሪዎች አመልካች ሻለቃ መሐመድ ሐሰን እና ተጠሪ ወታደራዊ ዐቃቤ ህግ (የሰበር መዝገብ ቁጥር 33369)  ነበሩ፡፡ የጉዳዩን አመጣጥ ከሰበር ውሳኔው ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው አመልካች በ1949 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 387(1)(ሀ) እና (ሐ)፣ አንቀጽ 414፣ አንቀጽ 642 እና 664 በመተላለፍ ወንጀል ፈጽሟል በሚል በቀረበበት ክስ የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው የ10(አስር) ዓመት ፅኑ እስራት እና የብር 5,000(አምስት ሺ) መቀጫ እንዲቀጣ ይወስንበታል፡፡

በመቀጠል አመልካች የተሰጠበትን ፍርድ በመቃወም ለይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 642 የቀረበበትን ክስ ብቻ በመሰረዝ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማሻሻል አጽንቶበታል፡፡

በመጨረሻም አመልካች ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርቦ ተፈጽሟል የተባለው ወንጀል በወታደራዊው ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቅ ስለመሆኑ በጭብጥነት ተይዞ ጉዳዩ በሰበር ችሎቱ ተመርምሯል፡፡

ችሎቱ ለተያዘው ጭብጥ እልባት ሲሰጥ መጀመሪያ ጭብጡ የሚያስነሳውን መሠረታዊ የህግ የበላነትይና የህጋዊነት መርህ አስረግጦ አስቀምጦታል፡፡

የሰበር ችሎቱ ‹‹በህግ የተሰጠ የዳኝነት ስልጣን ሳይኖር የተሰጠ ውሳኔ የህግ መሠረት ያለው ነው ወይም ህጋዊ ውሳኔ ነው ለማለት እንደማይቻል›› አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም አጀማመሩ ያማረው የችሎቱ ውሳኔ መጨረሻውም ያማረና የህግ የበላነትን የሚያረጋግጥ አልነበረም፡፡

በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቁ ጉዳዮች በመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 27/1988 ከአንቀጽ 26 እስከ 28 ድረስ ተዘርዝረዋል፡፡ የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የስረ ነገር የዳነት ስልጣንን በዋነኛነት የሚዘረዝረው የአዋጁ አንቀጽ 26 እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በሚከተሉት ላይ የዳኝነት ስልጣን ይኖራቸዋል፡፡

1.  በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከአንቀጽ 296 እስከ 331 በተዘረዘሩት ወንጀሎች ተጠያቂ በሚሆኑ ሰዎች

2.  በግዳጅ ላይ ያለ ወታደር በሚፈጽማቸው በማናቸውም ወንጀል

3.  በውጭ አገር በጦር ሜዳ ግዳጅ ላይ ካለ ወታደር አብረው በሚዘምቱ ሲቪሎች የሚፈጸሙ ወንጀሞች

4.  በጦር ምርኮኞች የተፈጸመ ወንጀል

የአንቀጽ 26 ድንጋጌ ይዘት ሲታይ አመልካች ላይ የቀረቡት ክሶች (የቀረቡት ክሶች ሆነ ከላይ በአንቀጽ 26/1/ ላይ ከአንቀጽ 296 እስከ አንቀጽ 331 በሚል የተጠቀሰው የድሮውን የ1949 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡) ከወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ውጭ ስለመሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ በሰበር ችሎቱም ቢሆን በመርህ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሆኖም ችሎቱ ከአንቀጽ 26 ላይ ንዑስ ቁጥር ሁለትን መዞ በማውጣት በግዳጅ ላይ ያለ ወታደር የሚፈጽማቸው ወንጀሎች ላይ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን እንደተሰጣቸው በማተት አመልካች ወንጀሉን ሲፈጽም በግዳጅ ላይ ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት መርምሯል፡፡

በዚሁ መሠረት ‹‹ግዳጅ›› ለሚለው ቃል ትርጓሜ የሰጠውንና የመጀመሪያውን የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ለማሻሻል ከሰባት ዓመት በኋላ የወጣውን የመከላከያ ሠራዊት (ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 343/1995 መሠረት በማድረግ አመልካቹ ወንጀሉን ሲፈጽም በግዳጅ ላይ እንደነበረ መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡

በተሻሻለው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 343/1995 አንቀጽ 2/1/ ቁጥር 9 መሠረት ግዳጅ ማለት ማንኛውም የሠራዊት አባል ከተቀጠረበት ጊዜ አንስቶ ከሠራዊት እስከሚሰናበት ጊዜ ድረስ በመከላከያ ውስጥ የሚያከናውነው የውትድርና ተግባር የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ አመልካች ወንጀሉን ሲፈጽም በ107ኛ ኮር በተሰየመው መምሪያ የኮሩ የፋይናንስ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ ስለመሆኑ በሰበር ውሳኔው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ወንጀሉን ሲፈጽም በግዳጅ ላይ ነበር ለማለት የሚቻል እንደመሆኑ ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስር እንደሚወድቅ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይከብድም፡፡ በዚሁ መሠረት የሰበር ችሎት አመልካች ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር እንደሚወድቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሰበር ውሳኔው ላይ ላዩን ሲታይ ከስህተት የፀዳ ቢመስልም ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የሰበር ችሎቱ ለውሳኔው መሠረት ባደረገው የተሻሻለው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 343/95 ውስጥ ያልታየች አንዲት የታለፈች አንቀጽ ለውሳኔው መሳሳት ምክንያት ሆናለች፡፡

ህግ አውጪው በማሻሻያ አዋጁ ላይ ግዳጅ ለሚለው ቃል ትርጓሜ ከመስጠት በተጨማሪ በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 27/1988 አንቀጽ 26/2/ ላይ ግልጽ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

የተሻሻለው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ አንቀጽ 12 እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹ አንቀጽ 26 ስር ንዑስ አንቀጽ (2) ተሰርዞ በሚከተለው ንዑስ አንቀጽ (2) ተተክቷል፣

26(2) የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እንደተጠበቀ ሆኖ በጦር ሜዳ ግዳጅ ላይ ያለ ወታደር በሚፈጽማቸው በማናቸውም ወንጀል፡፡›› (ስርዝ የተጨመረ)

የአንቀጹ የእንግሊዘኛ ቅጂም ተመሳሳይ ይዘት አለው፡፡ ‹‹ any offence Commited by a member of the Defence force on combat duty›› (ስርዝ የተጨመረ)

ለክርክር የማይጋብዘውና ግልጽ መልዕክት ያዘለው የማሻሻያ አዋጁ አንቀጽ 12 ተፈፃሚ ቢደረግ ኖሮ በሻለቃ መሐመድ ሐሰን እና በወታደራዊ ዐቃቤ ህግ መካከል በሰበር ችሎት የቀረበውን ክርክር በቀላሉ ይፈታው ነበር፡፡ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣን የመከላከያ ሠራዊት አባል ከተቀጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከሚሰናበት ጊዜ ድረስ በሚፈጽማቸው በማናቸውም ወንጀሎች ላይ ሳይሆን በጦር ሜዳ ግዳጅ ላይ እያለ በሚፈጽማቸው ማናቸውም ወንጀሎች ላይ ብቻ የተገደበ ስለመሆኑ ህግ አውጪው ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ በጦርነት ውስጥ ለጦርነት ዝግጅት በሚደረግበት እና ወዲያውኑ ከጦርነት መልስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የወታደራዊ ፍርድ ቤት የተሰጠው የዳኝነት ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 27/1988 አንቀጽ 26/1/,/3/ እና 4 እንዲሁም አንቀጽ 28 ስር በሚወድቁ ወንጀሎች ላይ ብቻ ነው፡፡

አመልካች ፈጸመ የተባለ ወንጀል በጦር ሜዳ ግዳጅ ውስጥ ሆኖ የፈጸመው አይደለም፡፡ ይህ ስለመሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር የለም፡፡

በሰበር ውሳኔው ላይ የታየው ስህተት ያቺን የተሸሸገች አንቀጽ ካለማስተዋል የመነጨ ቢሆንም መሠረቱ ግን በጽሁፉ መግቢያ ላይ ስለህጎች ግጣም እና ጣዕም ጋር በተያያዘ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ከአዋጅ ቁ. 343/1995 ላይ የግዳጅ ትርጉም ተወስዶ ከአዋጅ ቁ 27/1988 ጋር ተጣምሮ ሲነበብ አንዳች የገጠመ ነገር ይታያል፡፡ ሆኖም ያ የገጠመው ነገር ጣዕም እንደማይሰጥ በግልጽ ያስታውቅ ነበር፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ከተቀጠረበት  ጀምሮ እስከሚሰናበት ጊዜ ድረስ የሚፈጽማቸው ወንጀሎች በሙሉ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቁ ከሆነ ከስም ማጥፋት እስከ ግርዛት ሁሉም ወንጀሎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት ሊታዩ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ ስሜትም ትርጉምም የሚሰጥ አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግዳጅን ትርጉም ብቻ ወስደን አንቀጽ 26(2) ላይ ስንገጥመው የአንቀጽ 26 ሌሎች ንዑስ አንቀፆች በሙሉ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በሁሉም በመከላከያ ሠራዊት አባላት በሚፈጽሙ ማናቸውም ወንጀሎች ላይ የወታደራዊ ፍርድ ቤት ስልጣን የሚኖረወ ከሆነ ስለ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ስልጣን የሚያወራ ሌላ የህግ ድንጋጌ አስፈላጊ አይሆንም፡፡

ከአንቀጽ 26(3) በስተቀር የተቀሩት በአዲሱ የአንቀጽ 26(2) ትርጓሜ ውስጥ ይዋጣሉ፡፡ ስለሆነም ከአንቀጽ 296 እስከ 331 በተዘረዘሩት ወንጀሎች በሚል ለወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ዳኝነት የሚሰጥ የህግ ድንጋጌ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የግዳጅን ትርጓሜ ብቻ በመውሰድ የምንደርስበት ድምዳሜ የሚጥም እንደማይሆን ያሳዩናል፡፡

ስህተቱ የተፈጠረውም ሁለቱ ህጎች ገና ሳይጣጣሙ ሂደቱ ማብቃቱ ነው፡፡ ማሳረጊያው በመግቢያው ሲቋጭ አሁንም ‹‹ በጣም ምርጥ የሆነው ህጎችን የመተርጎም ዘዴ ህጎችን እርስ በራሳቸው እንዲጣጣሙ ማድረግ ነው፡፡

 

 

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s