የዘመን ባንክ ውዝግብ አቶ ኤርሚያስን በመምረጥ ተቋጨ.
ባአክሲዮኖችን ለሁለት ከፍሎ ሲያወዛግብ የሰነበተው የዘመን ባንክ የምርጫ ሽኩቻ ተጠናቆ ባለፈው ቅዳሜ ሌላ ምርጫ ተካሂዶ መሥራቹን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን በድጋሚ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት በመምረጥ ተቋጭቷል፡፡ በእርግጥ ውዝግቡ የመጨረሻውን ዕልባት የሚያገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የምርጫውን ውጤት ሲያፀድቀው በመሆኑ፣ የባንኩ ባለአሲዮኖች የባንኩን ውሳኔ እየተጠባበቁ ነው፡፡
ስድስት ኪሎ የስብሰባ ማዕከል በተካሄደው የባንኩ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው ለቦርድ አባልነት የተመረጡት፡፡ ከተመረጡት ውስጥ አቶ ኤርሚያስን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተጠቁመው የነበሩ ሲሆን፣ እነሱም አቶ ታምሩ ወንድም አገኘሁ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሠራተኞች ቁጠባ ማኅበር፣ ዶ/ር ፀጋዬ ሀብቴና ወይዘሮ እመቤት ደጀኔ ናቸው፡፡ አራቱ ተጠቋሚዎች ሲመረጡ ዶ/ር ፀጋዬ ሀብቴ ግን ሳይመረጡ ቀርተዋል፡፡