በጠበቆች ምዝገባ ፍትሕ ሚኒስቴርና ንግድ ሚኒስቴር እየተከራከሩ ነው


በጠበቆች ምዝገባ ፍትሕ ሚኒስቴርና ንግድ ሚኒስቴር እየተከራከሩ ነው.

ጠበቆች በአዲሱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ተመዝግበው የንግድ ፈቃድ ማውጣት እንዳለባቸው ከንግድ ሚኒስቴር በየወረዳው የተላለፈው መመርያ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከጠበቆች ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ወረዳዎች ከንግድ ሚኒስቴር የተላለፈላቸውን መመርያ መሠረት በማድረግ ማንኛቸውም ጠበቆች እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም. እንዲመዘገቡ አስጠንቅቀው፣ የማይመዘገቡ ከሆነ ግን የሚሠሩበትን የሥራ ቦታ እንደሚያሽጉት ያስተላለፉትን መግለጫ በሚመለከት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ከንግድ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረበት መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ እንደገለጹት፤ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠበቆችን የሚያውቃቸው እንደነጋዴ ሳይሆን፣ ለፍትሕ ሥርዓቱ ደጋፊና አጋዢ በመሆን አብረው መሥራታቸውን ነው፡፡ የጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ራሱን የቻለ ሕግና ሥርዓት አለው፡፡ ከንግድ ሥርዓቱ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም ብለዋል፡፡

በ1952 ዓ.ም. ስለነጋዴዎችና ስለንግድ መደብሮች የወጣው አዋጅ ከ21 በላይ የንግድ ሥራ ዝርዝሮችን ሲያስቀምጥ ጠበቆችን ያላካተተ ከመሆኑም በላይ፣ ባለፈው ዓመት የወጣው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002  የሚጠቅሰውም የ1952ን በመሆኑ ይህንን አለማካተቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የጥብቅና ሥራ ከሙያው ትርፍ የሚገኝበት ሥራ በመሆኑ ጥብቅናን ሙያው አድርጐ የሚሠራ ማንኛውም ጠበቃ ተመዝግቦ የንግድ ፈቃድ የማውጣት ግዴታ እንዳለበት የሚገልጹት ደግሞ፣ የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን መሐመድ ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ጥብቅና በውል የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ በሥራው ትርፍ ይገኛል፡፡ ትርፍ የሚያስገኝ ሥራ ከሆነ ደግሞ በምዝገባ ፈቃድ መውጣት አለበት፡፡ “ለምሳሌ አርክቴክት የሚሠራው ዲዛይን ነው፡፡ በሚሠራው ዲዛይን ገንዘብ ስለሚያገኝ ነጋዴ ነው፡፡ ጠበቃንም የምንረዳው በዚህ መንገድ ነው ይላሉ፤”

በ1952ና በ686/2002 አዋጆች አልተካተተም ስለሚባለው አቶ ኑረዲን ሲመልሱ፤ “686/2002 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ የሚለው የንግድ ፈቃድ የሚወጣባቸው የንግድ ሥራዎች /መስኮች/ በሸቀጣ ሸቀጦች ወይም በዓለም አቀፍ የንግድ ስያሜዎች መሠረት ይከናወናሉ ነው፡፡ የአወሳሰን ሥርዓቱን ንግድ ሚኒስቴር ያወጣል ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ንግድ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ንግድ ፈቃድ መስጫ መደቦች ብሎ 982 መደቦችን አውጥቷል፡፡ ከእነዚህ መደቦች ውስጥ አንዱ የጥብቅናና የነገረ ፈጅ አገልግሎት መሆኑን በመመርያው ተጽፎ ገብቷል፤” ብለዋል፡፡

ሙ ዜናውን ለማንበብ

 

2 Comments

 1. Belaynew says:

  የንግድ ሚኒስቴር ፈቃድ የሚሰጣቸው የንግድ ዘርፎች በ1952 የንግድ ሕግ ቁጥር 5 ሥር ተዘርዝረዋል፡፡ በንግድ ሕጉ ቅጥር 5 የተዘረዘሩትም የንግድ ሥራዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን የንግድ ሥራዎች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ የንግድ ሥራዎች በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለነዚህም የንግድ ፈቃድ የሚሰጠው በነዚሁ አዋጆች የሚቋቀቋሙ የተለያዩ የመንግስት አስተዳደራዊ አካላት ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ2002 ዓ.ም የወጣው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 በአንቀጽ 30 ንኡስ ቁጥር 1 ከ (ሀ) – (ቸ) ድረስ የተዘረዘሩት የንግድ ሥራዎች ላይ የንግድ ሚኒስቴር ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ያልተካተቱ የንግድ ሥራዎች፣ ፍትሕ ሚኒስቴርም ፈቃድ የማይሰጥባቸው ሌሎች የንግድ ሥራዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ብንወስድም የጥብቅና ሥራ አንዱ ነው፡፡ የጥብቅና ሥራ በ1952 ዓ.ም የወጣው የንግድ ሕግ በአንቀጽ 5 ሥር የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟላ ነው፡፡ በርግጥ ጥብቅና ለትርፍ ተብሎ የማይሰራ ነው ለማለት የሚቻል ቢሆንም ትርፍ የሚያስገኝ ሥራ ነው፡፡ ከሌሎች የንግድ ሥራዎች የሚለየው ጉዳይም ከሥራው የሚገኘው ትርፍ አገልግሎቱ በሚሰጥበት ጊዜ እግረ-መንገዱን /Incidental/ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ሥራው ሲጀመርም በዋናነት የሕግ አገልግሎት ለመሰጠት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሰጠበቅ በሚል እሳቤ ነው፡፡ የንግድ ሥራ መሆኑ ግን የሚያጠያይቅ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይም አይደለም፡፡

  የጥብቅና ሥራ ፈቃድን በተመለከተም ፈቃዱን የሚሰጠው ንግድ ሚኒስቴር ሳይሆን የፍትሕ ሚኒስቴር ነው፡፡ ይኸውም በአዋጅ ቁጥር 691/2002 አንቀጽ 16(12) ሥር በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ግን የንግድ ሚኒስቴር ምንም የሚመለከተው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ ፈቃዱን የሚሰጠው የፍትሕ ሚኒስቴር ቢሆንም ሌሎች ከንግድ ጋር ተያያዥነት የላቸውን ጉዳዮች ግን ንግድ ሚኒሰቴር የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን አለው፡፡ ተያያዥነት የላቸውን ጉዳዮች ግን ንግድ ሚኒሰቴር የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን አለው፡፡

  1. “ከንግድ ጋር ተያያዥነት የላቸውን ጉዳዮች ግን ንግድ ሚኒሰቴር የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን አለው፡፡ ተያያዥነት የላቸውን ጉዳዮች ግን ንግድ ሚኒሰቴር የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን አለው”
   ለኔ ግልጽ ያልሆነልኝ ጉዳይ ይሄ ነው
   “ተያያዥነት የላቸውን ጉዳዮች” ምንድናቸው?
   ማለቴ! ምን አርጉ ነው?
   ዛሬ ነጋደየ ናችሁ ከተባለ እኔ የምፈራው ነገ ደግሞ እንደ ኪሎ ስጋ ዋጋ ካልተመንን እንዳይሉ ነው

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s