አንቀጽ ጥቀስ ብሎ ነገር!


ጉዳያችሁን በቅጡ ለማስረዳት በፍርድ ቤት ቆማችሁ ስተከራከሩ ሆነ የአቤቱታችሁንና መከላከያችሁን ዝርዝር መከራከሪያ  በፅሁፍ ስታቀርቡ አልፎ አልፎ ከችሎት የሚገጥማችሁ ፈተና አለ ዳኞች ላቀረባችሁት ክርክር ደጋፊ ህግና አንቀጽ እንድትጠቅሱ ካልጠቀሳችሁም እንደተሸነፋችሁ በመቁጠር ወዲያው ውሳኔ ይሰጣሉ

“የትኛው ህግ ነው እንዲህ የሚለው? እስቲ አንቀጽ ጥቀስ!” ከዳኞች እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲመጣ እኔም “አንቀፅ ጥቀስ የሚል አንቀፅ የተከበረው ፍርድ ቤት ሊጠቅስልኝ ይችላል?” (ማለት ይዳዳኛል) ሆኖም የያዝኩት የሰው ጉዳይ ነውና ፍርድ ቤት እንኳንስ አንቀጽ ሌላም ነገር ጥቀስ ቢለኝ ትዕዛዙን ተግባራዊ ማድረግን እምርጣለሁ

አንቀጽ ከመጥቀስ ባለፈ አንዳንዴ የተገለጸው ፍሬ ነገርና የተጠቀሰው አንቀጽ ዱባና ቅል የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በእርግጥ ለዳኞችም የሚከብዳቸው ነገር ሊፈጥር ይችላል ለምሳሌ ተከሳሽ ለቀረበበት ክስ የሚከተለውን ምላሽ ቢሰጥ እንዴት ይስተናገዳል?

“ክሱ በፍትሃ ብሄር ህግ አንቀጽ 1000(1) መሰረት ከአስር አመት በኋላ የቀረበ ስለሆነ በይርጋ ቀሪ ነው” ምንም እንኳን ከክሱ ይዘትና አመላካች ከሆኑ ፍሬ ነገሮች ተከሳሽ ለክርክሩ መሰረት ያደረገው የይርጋ ህግ የትኛው እንደሆነ መገመት ቢቻልም የቀረበው ክስ የተጠቀሰውን ህግና ፍሬ ነገሩን በአንድ ጊዜ የሚነካ ሲሆን አንዱን መምረጥ አዳጋች ይሆናል ለምሳሌ ከላይ የቀረበው መቃወሚያ “ሟች ያደረገው የስጦታ ውል ይፍረስ እንዲሁም ተከሳሽ አለአግባብ የያዘውን የወራሽ ንብረት ይልቀቅ” የሚል በሚሆንበት ጊዜ ከህጉና ከፍሬ ነገሩ አንዱን መምረጥ አስቸጋሪ ይሆናል

ሆኖም በእኔ እምነት ለማናቸውም ክርክር መሰረት ሊሆን የሚገባው በባለጉዳዩ የሚጠቀሰው ህግ ሳይሆነ ፈሬ ነገሮቹ ናቸው

“ፍሬ ነገሩን ንገረኝና ህጉን እነግርሃለው!” የሚል የህግ አባባል አለ  ከአባባልነት ባለፈ የፍትሃ ብህር ስነ ስርዓትና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጎቻችን በዋነኛነት ትኩረት የሚሰጡት ፈሬ ነገርን መሰረት ላደረገ ሙግት ነው በይግባኝና በሰበር ከሚካሄዩ ክርክሮች በስተቀር በመጀመሪያ ደረጃ በሚካሄድ ክርክር ላይ ‘አንቀጽ ከአንቀጽ በማጋጨት’ የሚካሄድ ሙግት ብዙም ቦታ የለውም ስለሆነም አንቀጽ ተጠቀሰም አልተጠቀሰም ከፍሬ ነገሩ ተነስተው ተገቢነት ያለውን ህግ ተፈጻሚ ማድረግ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት የዳኞች ግዴታ ነው

አሁን ባለው ሁኔታ አንቀጽ ጥቀስ የሚል ህግ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን አንቀጽ መጥቀስ የተከራካሪ ወገን ግዴታ ስላለመሆኑ ራሱን የቻለ ህግ ሆኗል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  በአመልካች አቶ ውብሸት ካሳዬ  እና ተጠሪ የኢትዮጵያ ማዕድን ሃብት ኮርፖሬሽን መካከል በነበረው የሰበር ክርክር ጥር 25 ቀን 2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ (የሰበር መ/ቁ 39581) የተሳሳተ አንቀጽ መጥቀስ ሆነ እስከነጭራሹ አንቀጽ አለመጥቀስ መብትን የማስቀረት ውጤት የለውም  ችሎቱ ይህን ነጥብ የገለጸው በእንዲህ መልኩ ነበር

“…አንድ ተከራካሪ ወገን ፍሬ ነገሩን ከገለፀ ትክክለኛውን የህግ ድንጋጌ አለመጥቀሱ መብቱን ሊያስቀርበት አይችልም፡፡ ይልቁንም ፍ/ቤቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ አግባብነት ያለውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ተገቢ ነው ያሉትን ውሳኔ የመስጠት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ “

የውሳኔው ሙሉ ይዘት የሚከተለው ነው

የሰበር መ/ቁ 39581

ጥር 25 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- 1. መንበረፀሐይ ታደሰ

          2. ሐጎስ ወልዱ

          3. ሒሩት መለሰ

          4. ብርሃኑ አመነው

          5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- አቶ ውብሸት ካሳዬ – ጠበቃ ኃይሉ ገ/ሥላሴ

ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ማዕድን ሃብት ኮርፖሬሽን – ነ/ፈጅ ግርማ አለሙ ቀረቡ

 

ፍ ር ድ

        ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ጉዳይ የጀመረው ከፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ነው፡፡ አመልካች በስር ፍ/ቤት ከሳሽ ነበሩ፡፡ የክርክሩም አመጣጥ የሚከተለው ነው፡፡ ተጠሪ ያለአግባብ ከስራ አሰናብቶኛል በሚል ክፍያ እንዲከፈላቸውና ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ክስ አቅርበው ተጠሪ አመልካች የአሰሪ ወገን ሳይሆኑ የሰራተኛ ወገን ናቸው በሚል መቃወሚያ በማቀረቡ ፍ/ቤት ተጠሪ የአሰሪ ወይም የሰራተኛ ወገን ስለመሆናቸው በስራ ክርክር ችሎት አስወስነው ሲቀርቡ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብታቸውን ጠብቆ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ አመልካችም በዚሁ መሰረት በስራ ክርክር ችሎት የአሰሪ ወገን መሆናቸውን አስወስነው መዝገቡን እንዲንቀሳቀስላቸው ሲያመለከቱ መዝገቡ በመጥፋቱ የቀድሞ ክስና የተጠሪ መልስ ተያይዞ ክሱ በአዲስ መዝገብ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ፍ/ቤቱም የአመልካች አቤቱታ ከነአባሪው ለተጠሪ ደርሶ ተጠሪ አስተያየት እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ከዚህ በኋላ አመልካች በተከታታይ ቀጠሮዎች ባለመቅረባቸው ፍ/ቤቱ መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መሰረት ዘግቷል፡፡ አመልካችም የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 71(2)ን መሰረት አድርገው መዝገቡ እንዲከፈትላቸው ሲያመለክቱ ፍ/ቤቱ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 የተዘጋ መዝገብ አመልካች በጠቀሱት የሥነ-ሥርዓት ህግ መሰረት ሊከፈት አይችልም በማለት ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች ለፌ/ኬፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረቡት ይግባኝ ተቀባይነት አጥቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ አመልካችም በቅሬታቸው በስር ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ለተጠሪ ደርሶ መልስ እና የመልስ መልስ የተቀባበልን ስለሆነ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መወሰን ሲገባው መዝገቡን መዝጋቱ ስህተት ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ችሎትም የአመልካች አቤቱታ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በማለቱ ግራ ቀኙ ቀርበው የቃል ክርክራቸው ተሰምቷል፡፡ ችሎቱም አቤቱታ የቀረበበትን ትዕዛዝ ከተገቢው ህግ ጋር በማገናዘብ ተመልክቷል፡፡

        ከፍ ሲል የተገለፀው የግራ ቀኙ ክርክርና የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ምላሽ ማግኘት የሚያስፈልገው ጭብጥ የስር ፍ/ቤት መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መሠረት መዝጋቱ እንዲሁም አመልካች መዝገቡ እንዲከፈት ሲጠይቁ ጥይቄአቸው ውድቅ መደረጉ ተገቢ መሆን አለመሆኑ ነው፡፡ ከፍ ሲል እንደተመለከትነው አመልካች ክስ አቅርበው ግራ ቀኙ መልስና የመልስ መልስ ተቀባብለው ጨርሰዋል፡፡ ተጠሪ ቀድሞ የቀረበው ክስ፣ መልስ፣ የመልስ መልስ እንደሁም ሌሎች ማስረጃዎች ደርሶት አስተያየት እንዲሰጥ የታዘዘው የቀድመውን ተከሳሽ ተክቶ በክሱ ውስጥ በመግባቱ ብቻ ነው፡፡ ፍ/ቤቱም መዝገቡን በዘጋበት እለት ለመዝገቡ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበረው አመልካች አቤቱታቸውን ከነአባሪዎቹ ለተጠሪ አድርሰው ተጠሪ የሚያቀርበውን አስተያየት ለመቀበል እንጂ ክስ ለመስማት አልነበረም፡፡ አመልካች በቀጠሮው እለት ባለመቅረባቸውም ፍ/ቤቱ መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መሰረት መዝገቡን ዘግቷል ይህ የሥነ-ሥርዓቱ ድንጋጌ የሚገኘው ክረክርን ስለማቋረጥ በሚናገረው ሥነ-ሥርዓት ህጉ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የተጠቀሰው ድንጋጌም ለክሱ ምክንያት የሆነው ነገር ተቋርጦ በሚቀርብበት ጊዜ ፍ/ቤቱ ስለሚወስደው እርምጃ የሚናገር ሲሆን የድንጋጌው ይዘትም፤ “ክሱ በሚቀጥልበት በማንኛውም ጊዜ ለክሱ ምክንያት የሆነው ነገር መቋረጡን ወይም ጨርሶ መቅረቱን ፍ/ቤቱ በቂ በሆነ ማስረጃ የተገነዘበ እንደሆነ ስለ ኪሳራና ስለ ካሳ ተገቢ የሆነውን ትእዛዝ በመስጠት ክሱን ይዘጋዋል፡፡ ምክንያቱንም ዘርዝሮ በመዝገቡ ላይ ያሰፍራል፡፡” በሚል ይነበባል፡፡ ድንጋጌው ከሚገኝበት ክፍልና ከድንጋጌው ዝርዝር ይዘት በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው ፍ/ቤቱ ክሱን የሚዘጋው የክሱ ምክንያት ሲቋረጥ ወይም ጨርሶ ሲቀር ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግን ፍ/ቤቱ መዝገቡን የዘጋው የክሱ ምክንያት በመቋረጡ ሳይሆን አመልካች በተከታታይ ቀጠሮ በመቅረታቸው በመሆኑ ፍ/ቤቱ የተጠቀሰውን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌ መሰረት አድርጎ መዝገቡን መዝጋቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

        በሌላ በኩል አመልካች መዝገቡ እንዲከፈትላቸው የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 71(2)ን መሰረት በማድረግ ለፍ/ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ሥነ-ሥርዓት መሰረት መዝገብ እንደከፈት ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለው በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69(2) ክስ በሚሰማበት ቀነ-ቀጠሮ ከሳሽና ተከሳሽ በመቅረታቸው ወይም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 70(መ) መሰረት ከሳሽ ለተከሳሽ መጥሪያ ሳያደርስ በመቅረቱ መዝገቡ ተዘግቶ ከነበረና ከሳሹ የቀረው ወይም ለተከሳሽ መጥሪያ ያልደረሰው በቂ ሆኖ በሚገመት ምክንያት መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የአመልካች የክስ መዝገብ የተዘጋው ክስ በሚሰማበት ቀነ-ቀጠሮ በመቅረታቸው ስላልሆነ መዝገቡ እንዲከፈት ይህን ሥነ-ሥርዓት መጥቀሳቸው ተገቢ አልነበረም፡፡ ነገር ግን አንድ ተከራካሪ ወገን ፍሬ ነገሩን ከገለፀ ትክክለኛውን የህግ ድንጋጌ አለመጥቀሱ መብቱን ሊያስቀርበት አይችልም፡፡ ይልቁንም ፍ/ቤቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ አግባብነት ያለውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ተገቢ ነው ያሉትን ውሳኔ የመስጠት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍ ሲል እንደተመለከትነው ፍ/ቤቱ አመልካች ባለመቅረባቸው መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መሰረት መዝጋቱ ሥነ-ሥርዓታዊ ባለመሆኑ ምንም እንኳን አመልካች የጠቀሱት አንቀፅ ለጉዳዩ አግባብነት ባይኖረውም ተገቢውን ድንጋጌ በመጠቀም ስህተቱን ሊያርም ይገባው ነበር፡፡ በክርክሩ ውስጥ ከሥነ-ሥርዓት ውጪ የሆነው ጉዳይ ሲያጋጥም ማንኛውም ተከራካሪ ወገን በሚያቀርበው ጥያቄ ፍ/ቤቱ ከሥነ-ሥርዓት ውጪ የሆነው ነገር በሙሉ ወይም በከፊል እንዲሰረዝ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 209 ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አመልካች ለስር ፍ/ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ ከተጠሪ ጋር መልስና የመልስ መልስ ተሰጥቶበት ለውሳኔ ያደረ ጉዳይ መሆኑን በመግለፅ መዝገቡ እንዲከፈትላቸው በ21/4/2000 ዓ.ም ስለመጠየቃቸው የስር ፍ/ቤት መዝገብ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቱ የአመልካች ክስ የክስ ምክንያቱ ሳይቋረጥ መዝገቡን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መዝጋቱ ከሥነ-ሥርዓት ውጪ በመሆኑ አመልካች ባቀረቡት ጥያቄ መነሻነት ይህንን ስህተቱን በማረም መዝገቡን መክፈት ሲገባው አመልካች የጠቀሱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌ አግባብ አለመሆኑን ብቻ መሰረት በማድረግ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 280 መሰረት የተዘጋ መዝገብ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 71(2) መሰረት አይከፈትም በሚል ምክንያት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎቹን በአግባብ ያላገናዘበና መሰረታዊ የሥነ-ሥርዓት ህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 92294 ጥር 13 ቀን 2000 ዓ.ም የተሰጠው ትዕዛዝ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 64486 ሚያዚያ 28 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል፡፡
  2. አመልካች ክስ ያቀረቡበት መዝገብ ተከፍቶ ክርክሩ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
  3. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s