አነጋጋሪው የአዲሱ የሊዝ አዋጅ ይዘትና አንድምታው


አነጋጋሪው የአዲሱ የሊዝ አዋጅ ይዘትና አንድምታው

የዚህ ጽሁፍ እንግሊዝኛ ቅጂ  The New Land Lease Proclamation: Changes, Implications

ሪፖርተር ጋዜጣ

በዳንኤል ወልደ ገብርኤል

መግቢያ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር የከተማ መሬትን አስመልክቶ አዲስ አዋጅ አውጥቷል።

አዋጁ አዋጅ ቁጥር 721/2004 የሚባል መጠርያ የተሰጠው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ ቁጥር 272/1994ን ሙሉ በሙሉ ሽሯል። አዲሱ አዋጅ በአምስት ክፍሎችና 38 አንቀጾች የተዋቀረ ሲሆን፣ ሕዝቡን ያነጋገሩ አዳዲስ ሐሳቦችና አሠራሮችንም አካትቷል። በዚህ አጭር ጽሑፍ ይህ አዋጅ ያስተዋወቃቸውን ዋና ዋና አሠራሮችንና አንድምታቸውን ለመተንተን ይሞከራል። አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ አዋጁ ካለፈው አዋጅ ያስቀረውንና የቀየረውን አሠራር በንፅፅር እንመለከታለን። አዋጁ ጥቅል የሆኑ ሐሳቦች ብቻ የያዘ ስለሆነ ማብራሪያ ሲያስፈልግ (ዝርዝር ድንብ እስኪወጣ ድረስ) ባለሥልጣናቱ የሚሰጡትን ማብራሪያ እንጠቀማለን።

የሊዝ ሥርዓት አስፈላጊነትና የአዋጁ ዓላማ
በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ የከተማ መሬት ምንም እንኳን ጥቂት ፊውዳሎች ቢቆጣጠሩትም ሥሪቱ ግን በግል የተያዘ ነበር። ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ግን በአዋጅ ቁጥር 47/67 አማካይነት ሁሉም የከተማ መሬቶችንና ትርፍ ቤቶችን ወደ መንግሥት ይዞታ አዛወራቸው። የመሬት ባለቤቶች ንብረታቸውን ያለምንም ካሳ አጡ። መሬትም እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ፣ በዕዳ እንዳይያዝና ለሌላ ሰው በማንኛውም መንገድ እንዳይተላለፍ እገዳ ተጣለበት። የከተማ ነዋሪዎች አንድ መኖርያ ቤትና አስፈላጊ ከሆነም ሌላ ድርጅት ቤት ብቻ እንዲይዙ ተፈቀደላቸው። ቤቱን ግን ያለምንም ማዕቀብ በነፃ ማዘዋወር ተቻለ። ቤት ያልነበራቸው ደግሞ ከ500 ካሬ ሜትር የማይበልጥ መሬት እየተሰጣቸው ቤት እንዲሠሩ ተደረገ። ቤት መሥራት የማይችሉት ደግሞ የተወረሱትን የቀበሌ ቤቶች እየተሰጣቸው በኪራይ ቤቶች መኖር ጀመሩ። የመሬት ይዞታ ሥሪቱ ዕድሜ ልክ የሚቆይ (በጊዜ ያልተገደበ) እና ኪራይ የማይከፈልበት ነበር። ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የከተማ መሬት ይዞታ በሊዝ ሥርዓት እንዲተዳደር አዋጅ ቁጥር 80/1986 አወጣ። ይህ አዋጅም በሌላ አዋጅ ቁጥር 272/1994 ተሻረ። እስከ ጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. ይህ አዋጅ ለአሥር ዓመታት በሥራ ላይ ቆየ። ጥቅምት 2004 ዓ.ም. ግን የኢፌዲሪ ፓርላማ አዋጅ ቁጥር 721/2004 የተባለ ሌላ የሊዝ አዋጅ አፀደቀ።

መሬት ከመንግሥት እጅ ወደ ግለሰቦች በሊዝ ኪራይ ማስተላለፍ በሁሉም አገሮች ዘንድ የተለመደ አሠራር ነው። ዋና ዓላማውም መንግሥት ልክ እንደ ግብር ሁሉ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝበት ታስቦ የተቀረፀ ነው። መሬት የግል በሆነባቸው አገሮች ጨምሮ መንግሥት በእጁ ያለውን ሰፋፊ መሬት ለገቢ ማስገኛ ሲል በሊዝ ለግለሰቦችና ለሪል ስቴት አልሚዎች ያከራያል። ከሊዝ ሥርዓቱ የሚሰበሰው ሀብትም ተመልሶ ለከተሞቹ መሠረተ ልማት ግንባታ ይውላል። ከዚሁ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ባለሀብትነት ሥር በዋለባቸው እንደ ቻይና፣ ኢትዮጵያና ሌሎች ሶሻሊስት አገሮችን ስንመለከት ደግሞ ሊዝ ከላይ ከተመለከተው በተጨማሪ ሌላ ዓላማ አለው፡፡ መሬት የመጠቀም መብትን ከመንግሥት ወደ ዜጎች ማስተላለፍያ መንገድ ሆኖ ያገለግላል። ይህም ማለት መሬቱ በአንዴ ወደግል ባለሀብትነት (Private Ownership) ማስተላለፍ ስለማይቻል ወይም ስለማይፈለግ ዜጎች በመሬቱ ሊጠቀሙበት የሚቻለው ሊዝ ብቻ ሆኖ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ቀደም ብሎ የነበረው አዋጅ ቁጥር 272/1994 ሁለት ዋና ዓላማዎች  ነበሩት። እነዚህም በቂ የሆነ ገቢ ከሊዝ ኪራይ መሰብሰብና በከተማ የተያዘውን መሬት ሁሉ ወደ ሊዝ ይዞታ መቀየር የሚሉ ናቸው። ላለፉት አሥር ዓመታትም መንግሥት እነዚህ ሁለት ዓላማዎችን ለመተግበር ሲጥር ኖሯል። ይሁን እንጂ በከተሞች ያለው የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመሬት አቅርቦት ሒደት ወቅት ቅልጥፍናና ግልጽነት የሌለው በመሆኑ የመሬት ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ሲነፃፀር የማይገናኝ ሆነ። ከዚህም በተጨማሪ የመሬት አሰጣጡ ሥርዓት በፈጠረው ክፍተት ምክንያት በሒደት ሙስና ተንሰራፋ። ይህም ለከተማ ብልጦችና ደላሎች መጠቀሚያ ሆነ። የመሬት ደላሎችና  ነጋዴዎች ባዶ ቦታ በሕጋዊና ሕገወጥ መንገድ በመግዛት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ በከፍተኛ ትርፍ መሸጥ ቻሉ። በብዙ ከተሞች መሬቱ ለአንድ ዓመት ይዞ በመቆየት ብቻ መቶ ፐርሰንት ትርፍ ማጋበስ ተቻለ። ሽያጮቹ በተጭበረበረ ውል ስለሚካሄዱም መንግሥት የትርፉ ተካፋይ መሆን አልቻለም። ሌላው ይቅርና የቤቶችን እጥረት ይቀርፋሉ የተባሉትን የሪል ስቴት አልሚዎች እንኳን በነፃ ከመንግሥት የወሰዱትን መሬት ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይሠሩ ባዶ ቦታ መሸጥ ጀመሩ። በዚህም የተነሳ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የአሁኑ አዲስ አዋጅ ሊወጣ ችሏል። የዚህ አዋጅ ዓላማዎችም ሁለት ሆነው እናገኛቸዋለን። ሐሳባቸው ሲጨመቅም ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመጣው የመሬት ፍላጎት ተገቢ የሆነ የመሬት አቅርቦት ለመፍጠርና እንደዚሁም  በመልካም አስተዳደር የተደገፈ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለበት የመሬት አስተዳደር ሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉ የሚሉ ናቸው።

ሁሉም የከተማ መሬት ይዞታ ወደ ሊዝ ስለመዛወሩ

አዋጁ ‹‹ማንኛውም ሰው የከተማ መሬትን በዚህ አዋጅ ከተደነገገው የሊዝ ሥርዓት ውጪ መያዝ›› እንደማይችል ይደነግጋል። ይህም ማለት ለወደፊት ለተጠቃሚዎች የሚተላለፍም ሆነ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ በግለሰቦች የተያዘ ቦታ ሁሉ ወደ ሊዝ ይዞታ ይቀየራል ማለት ነው። ምንም እንኳን የይዞታው ዓይነት (Tenure Type) የተለያየ ስም ቢሰጠውም መሬት ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በግለሰቦች እጅ ይገኛል። በወቅቱ የከተማ ርስት ይባል ነበር። በደርግ የተሰጠው ስያሜ ብንጠቀም ‹‹የይዞታ መሬት›› ይባላል። አዲሱ አዋጅ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ከዚያ በኋላ ከሊዝ ውጪ የተገኙ ይዞታዎች ‹‹ነባር ይዞታዎች›› ይላቸዋል። ‹‹ነባር ይዞታ›› ማለት የከተማ ቦታ በሊዝ ሥርዓት መተዳደር ከመጀመሩ በፊት በሕጋዊ መንገድ የተያዘ ወይም ሊዝ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ለነባር ይዞታ ተነሺ በምትክ የተሰጠ ቦታ እንደሆነ አዋጁ ይተረጉመዋል። ይህም ማለት ከሊዝ አዋጅ መውጣት በኋላ በሊዝ ውል መሠረት የተያዙ ቦታዎችን አይጨምርም ማለት ነው።

ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ይቀየራል ማለት ቦታው በካዳስተርም ሆነ በተራ ምዝገባ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ የይዞታው ዓይነት ሊዝ መሆኑ ይመዘገባል። ባለ ይዞታውም የከተማ አስተዳደር ዘንድ ቀርቦ የሊዝ ውል ይፈርማል። ለምሳሌ ለመኖርያ ቤት የ99 ዓመት ውል ይፈርማል። ከዚሁ በኋላ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ለተከራዩ የ‹‹ሊዝ ይዞታ ምስክር ወረቀት›› ይሰጠዋል። ይህ በገጠር ለገበሬው የሚሰጠው ዓይነት የይዞታ ምስክር ወረቀት ነው። በውስጡም የባለይዞታው ስም፣ የቦታው ስፋትና አድራሻ፣ የቦታው ቁጥርና አገልግሎት ዓይነት፣ የሊዝ ክፍያ መጠንና የሊዝ ውሉን ዘመን የያዘ ነው። ይህ ሠርተፊኬት ለባለይዞታው በፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችል የይዞታ ማረጋገጫ ነው።

ይዞታ ወደ ሊዝ ሲቀየር ክፍያ ያለው በመሆኑ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ይህን በመገንዘብ አዋጁ ሁሉም ነባር ይዞታዎች አሁኑኑ ወደ ሊዝ ሲስተም ይቀየሩ አላለም። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ጥናት ተደርጎ ይወሰናል በሚል ድፍን ውሳኔ ዘሎታል። ይልቁንስ ነባር ይዞታ የሆነ መሬት ከውርስ ውጭ በሆነ መንገድ (በሽያጭ፣ በስጦታ፣ ወይም በልውውጥ) ለሦስተኛ ወገን ቢተላለፍ፣ ወይም የነባር ይዞታ መሬት በሊዝ ከተገኘ ሌላ መሬት ጋር እንዲዋሃድ ጥያቄ ቀርቦ እንደሆነ፣ ወይም በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ መሬት በተለምዶ ጨረቃ ቤት የሚባል (Informal Settlement) ሕጋዊ እንዲሆን ተፈቅዶ ከሆነ የስም ዝውውርም ሆነ ሕጋዊ ምዝገባ የሚደረገው ከላይ በተጠቀሰው የሊዝ ምዝገባ ሥርዓት ይሆናል።

የዚሁ ውጤት ደግሞ የሊዝ ክፍያን መፈጸም ነው። ይህም ማለት ስም የዞረለት ሰው ቦታው ለሚገኝበት አካባቢ የወጣለትን ‹‹የሊዝ መነሻ ዋጋ›› ከቦታው ስፋት ጋር በማባዛት የሚገኘው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ ያደርጋል። ለምሳሌ በቅርቡ እንደሰማነው ለአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የተባለው ‹‹የሊዝ መነሻ ዋጋ›› 600 ብር ነው። ይህም ማለት እንደየሰፈሩ ሁኔታ እየታየ መነሻ ዋጋው ይቀንሳል ማለት ነው። ስለሆነም ለምሳሌ አቶ ለማ ሽሮ ሜዳ የሚገኘውንና በ200 ካሬ ሜትር ያረፈውን ቤታቸው መሸጥ ፈለጉ እንበል። ለሽሮ ሜዳ አካባቢ የተሰጠው የሊዝ መነሻ ዋጋ ደግሞ 500 ብር ነው እንበል። በሽያጩ ጊዜ ገዥ ለመንግሥት 200 x 500 አንድ መቶ ሺሕ ብር ይከፍላል ማለት ነው። ለመጀመርያ ጊዜ የሚከፍለው 10 በመቶ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በውሉ መሠረት ወለድ እየታሰበለት በረጅም ጊዜያት እንዲከፍል ይደረጋል።

የሕዝቡ ጥያቄ ድንገት የይዞታ መሬት ሁሉ ወደ ሊዝ ይዞታ ቢቀየር ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ሁኔታዎች ሳይኖሩ የሊዝ ክፍያ ከፈሉ ይባል ይሆን ወይ ነው። ድንገት ሳናስበው እያንዳንድህ መቶ ሺሕ ብር ዕዳ አለብህ እንባል ይሆን ወይ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደገለጹት ከሆነ ይህ ለወደፊቱ ከሕዝቡ ጋር ተመክሮበት የሚወሰን ነው ተብሏል።

መሬት የሚገኝባቸው መንገዶች
ከዚህ በፊት የነበረውና አሁን የተሻረው የሊዝ አዋጅ እንደዚሁም የክልል የሊዝ አዋጆች ስንመለከት መሬት ከመንግሥት ወደ ግለሰቦች የሚተላለፉባቸው መንገዶች አምስት እንደነበሩ መገንዘብ ይቻላል። እነዚህም ጨረታ፣ ድርድር፣ ስጦታ፣ ዕጣና ሽልማት ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑቱ ለሙስናና ላልተገባ አሠራር በር ይከፍታሉ ስለተባለ በአዲሱ አዋጅ ውስጥ እንዲካተቱ አልተደረገም። ስለሆነም በአዲሱ አዋጅ መሠረት በአሁኑ ወቅት መሬት በከተማ ማግኘት የሚቻለው በጨረታና በምደባ ብቻ ነው። ምደባ ማለት መሬት በሊዝ መነሻ ዋጋ ያለጨረታ ማስተላለፍ ማለት ነው። ሕጉ በተቻለ መጠን ሁሉም አካል መሬት ተጫርቶ እንዲያገኝ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ለሕዝቡ ከፍተኛ ጥቅምና አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የታሰቡ እንደ መንግሥት መሥርያ ቤቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ የመንግሥት የጋራ ቤቶች ግንባታና የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች መሬት ያለጨረታ በመነሻ ዋጋው ብቻ በምደባ ይሰጣቸዋል። ከዚሁ በተጨማሪ በከተማ መልሶ ማልማት ፕሮግራም ምክንያት ተነሺ የሚሆን የነባር ይዞታ ባለመብት ምትክ ቦታ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ ይህ ሰው በራሱ መኖርያ ቤት ይኖር የነበረ ስለሆነ ምትክ መሬቱ እንደካሳ ስለሚታሰብ የሊዝ ዋጋ ለመሬቱ እንዲከፍል አይደረግም። በአንፃሩ ግን ሰውየው በቀበሌ ቤት ተከራይቶ የሚኖር ከነበረ፣ ከተቻለ ተተኪ ቤት ይሰጠዋል ካልሆነ ግን መሬት በሊዝ መነሻ ዋጋ እንዲከራይ ይደረጋል።

የሊዝ መብት ማስተላለፍ ስለመቻል
የአሁኑም ሆነ የድሮው የሊዝ አዋጆች የሊዝ መብትን ማስተላለፍ አይከለክሉም። በእርግጥ ቀደም ሲል አዲስ አበባን ጨምሮ የአንዳንድ ከተሞች ባለይዞታዎች ባዶ መሬት ወይም መሠረት የወጣለትን ቦታ እንዳያስተላለፉ የውስጥ መመርያ ሲያወጡ ነበር። ይህ መመርያ ግን ቋሚ አልነበረም። ከተሞቹ እነዚህ መብት ገዳቢ የሆኑትን መመርያዎች ማውጣት የተገደዱበት ምክንያት በከተሞቹ እየተስፋፋ የመጣውን ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን›› ለመዋጋት ነበር፡፡ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት (Rent Seeking) ማለት በአንድ ነገር ላይ እሴት (Value) ሳይጨምሩ ትርፍ መፈለግ ነው። በኢኮኖሚ አስተሳሰብ ይህ ያልተለፋበት ገቢ እንደብክነት ይቆጠራል። ይህም ማለት የከተማ ደላሎችና አትራፊዎች (Speculators) ከመንግሥት ያገኙትንና ከሌላ ሰው የተላለፈላቸውን የሊዝ መሬት ምንም እሴት/ግንባታ ሳይጨምሩበት ይልቁንም ጊዜ በመጠበቅ ብቻ ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የመሬት እጥረት ፈጥረዋል፡፡ መሬትና ቤትን የማይገባቸው ዋጋ እንዲከፈልባቸው አድርገዋል የሚሉ ናቸው። በዚህ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት›› ሒደትም ታላላቅ የተባሉ የሪል ስቴት አልሚዎችም ተሳታፊ ስለነበሩ በወቅቱ በቅጣት መልክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ አንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር የሚደርስ መሬት እንደወሰደባቸው ይታወቃል። ይህንን ሁሉም ሰው ስለሚያውቀው ብዙም ማለት አያሻም።

የአሁኑን አዋጅ ስንመለከት የሊዝ መብትን ለሦስተኛ ወገን በማንኛውም መልኩ ማስተላለፍን፣ በዕዳ ማስያዝንና ለንግድ ማኅበር እንደ ካፒታል መዋጮ አድርጎ መስጠትን እንደሚቻል ይገልጻል። ስለዚህ ለወደፊቱ ሌላ ነገር ካልተከሰተ በቀር አዋጁ በመርህ ደረጃ የመሬት የሊዝ መብትን በነፃ ማስተላለፍን ያለምንም ገደብ ፈቅዷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ይህ ቢባልም አዋጁ ከዚህ በፊት የነበረውን የ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ችግር የሚያስወግድበት ስልትም ነድፏል። አጨቃጫቂ ከሆኑት አንቀጾች አንዱም ይህ ነው። የአዋጁን አንቀጽ 24 ስንመለከተው ከላይ የተነሳውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ አራት ስልቶችን አስቀምጧል። አንደኛውና ዋነኛው ባዶ ቦታ (የሊዝ መብትን ብቻ) ወይም ከግማሽ በታች ግንባታ በመሥራት ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ምንም ጥቅም እንዳይኖረው ተደርጓል። በዚህ አንቀጽ መሠረት ማንኛውም የሊዝ ባለይዞታ የሊዝ መብቱን ግንባታ ከመጀመሩ ወይም ግንባታውን በግማሽ ከማጠናቀቁ በፊት ከውርስ በስተቀር ማስተላለፍ የሚችለው አግባብ ባለው አካል ቁጥጥር የሚደረግበት ግልጽ የሽያጭ ሥርዓትን በመከተል ይሆናል፡፡ ግማሽ ግንባታ ማለት ለምሳሌ ለመኖርያ ቪላ መሠረቱ፣ ኮለንና ቢም የታሰረለት ነው። ከዚያ በላይ ከተሠራ እንደ ሙሉ ይቆጠራል።

ሁለተኛ ግንባታ ያልተሠራለት ወይም ግማሽ ግንባታ ያለው ቦታ ሲተላለፍ ባለመብቱ የሚያገኘው የተፈጸመው የሊዝ ክፍያና የሊዝ ክፍያው በባንክ ቢቀመጥ ያስገኝ የነበረው ወለድ፣ የተከናወነው ግንባታ ዋጋና የሊዝ መብቱ በመተላለፉ የተገኘው የሊዝ ዋጋ አምስት በመቶ ብቻ ነው። ይህንንም ግልጽ ለማድረግ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት:፡ አቶ ገዛኸኝ ሽሮ ሜዳ ላይ ባዶ መሬት በሊዝ ጨረታ በካሬ ሜትር በ3500 ብር አሸንፈው ተረከቡ እንበል። የመሬቱ ስፋት 200 ካሬ ሜትር  ሲሆን፣ ለዚህም ቅድሚያ የዋጋው 10 በመቶ 70,000 ብር ከፈሉ እንበል። አቶ ገዛኸኝ በመሬቱ ላይ በ40 ሺሕ ብር መሠረት አወጡ። በጠቅላላ እስካሁን ብር 110,000 አወጡ ማለት ነው። አሁን ግን መቀጠል ስላልቻሉ መሠረት የወጣለትን ቦታቸው በካሬ ሜትር ብር 4000 ለአቶ በየነ ሸጡ። እንግዲህ በካሬ ሜትር በ500 ብር በጠቅላላ ብር 100,000 ትርፍ ተገኘበት ማለት ነው። አሁን ጥያቄው ሻጩ የሚደርሳቸው ምን ያህሉ ነው የሚል ነው። ሻጭ የሚያገኙት ለሊዝ ቅድሚያ ክፍያ የከፈሉት 70,000 ብር፣ የዚሁ ወለድ አምስት በመቶ 3,500 ብር፣ ለመሠረት ግንባታ የተከፈለ 40,000 ብር እና በሊዝ መብቱ መተላለፍ የተገኘውን የመቶ ሺሕ ብር አምስት በመቶ 5,000 ብር ብቻ ይሆናል። ይህም ሲደመር 118,500 ብር ነው። አቶ ገዛኸኝ ያተረፉት 8,500 ብር መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ከሊዝ ሽያጩ የተገኘውን ትርፍ 95 በመቶ 95,000 ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ይደረጋል ማለት ነው።

ሦስተኛ ባለመብቱ ከባንክ መብቱን አስይዞ መበደር ከፈለገ የሊዝ መብቱ (ባዶ መሬት) የሚገመትለት አስቀድሞ በከፈለው የሊዝ ዋጋ ክፍያ መሠረት ነው። ይህም ማለት ለአብነት ከላይ የተጠቀሰው የአቶ ገዛኸኝን ምሳሌ ብንወስድ ባለመብቱ ለሊዝ የከፈሉት 70 ሺሕ ብር ስለሆነ ባንኮች ለመሬቱ/ሊዝ መብቱ ብቻ ከዚህ በላይ ሊያበድሩ አይችሉም። በእርግጥ ተጨማሪ ግንባታ ካለ የዚህን ግምትም መያዛቸው አይቀርም። ቀደም ሲል ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ) ሲያበድሩ ለመሬቱ ብቻ ለምሳሌ ለመርካቶና ለፒያሳ ከአራት ሺሕ ብር በላይ በካሬ ሜትር ይይዙ ነበር። አሁን ግን ተበዳሪው የሚያዝለት የከፈላት ክፍያ ብቻ ናት። አራተኛ አዋጁ ‹‹ማንኛውም ሰው በመሬት የወቅት ጥበቃ የሚመጣን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በተደጋጋሚ ጊዜ ግንባታ ሳያጠናቅቅ የሊዝ መብቱን የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ የሚመለከተው አካል በማንኛውም የሊዝ ጨረታ እንዳይሳተፍ ሊከለክለው ይችላል፤›› የሚል ንዑስ አንቀጽ ማስገባቱ የተባለውን ችግር ለመቅረፍ የተደረገውን ጥረት ያሳያል።

የአንቀጽ 24 ችግሮችን ስንመለከት ደግሞ አንቀጹ የታሰበለትን ዓላማ ስለማሳካቱ ጥርጣሬ አለኝ። በመጀመርያ ደረጃ የሊዝ መብትን ብቻ ወይም ግማሽ ግንባታ የገነባ ሰው የሚያገኘው ጥቅም የለም መባሉ ሞኝነት ይመስለኛል። አሁንም ቢሆን ገዥና ሻጭ ውስጣዊ የሆነ ስምምነት ከማድረግ የሚያቆማቸው ነገር አይኖርም። ሰው መሠረት ካወጣ በኋላ አስተማማኝ ትርፍ ካላገኘበት በቀር እንዲሁ በቀላሉ አይሸጠውም። ገዥ ቦታውን እስከፈለገው ድረስ አዋጁ የሊዝ ባለመብቱ ሊያገኝ የሚገባውን ትርፍ አያሳጣውም። ሁለተኛ እንበልና በዚህም በዚያም ተብሎ መቆጣጣር ተቻለ። የሊዝ ባለ መብቱንም ሆነ አትራፊ ነጋዴውን ግን ግንባታው ከግማሽ በላይ በማድረግ አሁንም ከመሻሻጥ ማቆም አይቻልም። ግማሽ ግንባታ ቢም የታሠረለት ነው ከተባለ ቆርቆሮ በማልበስ ያለቀለት ነው ተብሎ በተፈለገ ዋጋ ይሸጣል። ደላላና አትራፊ ነጋዴ እኮ ድሮውንም የገንዘብ እጥረት የለበትም። ባዶ ቦታ ገዝቶ’ኮ በራሱ ገንዘብ ሕንፃ ሠርቶ ባለመሬቱ የሠራ አስመስሎ ሲሻሻጡ ኖረዋል። መንግሥት ግን ይህንን ሀቅ አላይም በማለት አሁንም ቢሆን ከስህተቱ የተማረ አይመስልም። መፍትሔው ማገድ ሳይሆን መሬትን በብዛት ማቅረብ ነው። ሌላው ምናልባትም ለወደፊቱ በሚወጣው ደንብ ሊወሰን የሚገባ ነገር በነባር ይዞታዎች ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ደረጃውን ያልጠበቀ ግንባታን በተመለከተ ነው። በብዛት ከጭቃ የተሠሩ የከተማውንና አካባቢውን ፕላን ያልጠበቁ ቤቶች በሚሸጡበት ወቅት በምን ዓይነት ደረጃ እንደሚወድቁ መለየት ያስፈልጋል።

ቀሪውን የጽሁፉን ክፍል ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያንብቡ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s