የመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ በሚያስተዳድራቸው ቤቶች የተፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ስርዓት ለማስያዝ እንዲቻል ተሻሽሎ የተዘጋጀ መመሪያ፣


 የመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ በሚያስተዳድራቸው ቤቶች የተፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ስርዓት ለማስያዝ እንዲቻል ተሻሽሎ የተዘጋጀ መመሪያ  (DOWNLOAD PDF)


ህዳር/2004

አዲስ አበባ

 

I.  መግቢያ፣

የመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ በአዋጅ 555/2000 በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነቶች በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የመንግስት የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን (ቀበሌ ከሚያስተዳድራቸው ውጪ) በተገቢው መንገድ ያስተዳድራል፣ ኪራይ ይሠበስባል፣ ጥገና ያደርጋል፣…ወዘተ፡፡

ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ የተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባራት እንዳይፈፀሙ ለመከላከል እና እንዲሁም ቀደም ብለው በቤቶቹ ላይ የተፈፀሙትን የተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባሮች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሠድ እንዲያስችለው የካቲት 24/2002 የአዋጅ 555/2000 አንቀድ 6(3) ማስፈፀሚያ መመሪያ እና ሐምሌ 2002 ዓ/ም የዋና የስራ ሂደት የቤቶች አስተዳደር መመሪያዎችን እንዲሁም የኤጄንሲው የስራ አመራር ኮሚቴ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ አሠራሮችን አውጥቶ ወደ ተግባር በመግባት ብዙ ውጤታማ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡

ነገር ግን ቀደምባሉት አመታት ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው የንግድ ቤቶች ላይ የተፈፀመው ህገ-ወጥ ተግባር ውስብስብና መንግስት ችግሩን ለመፍታት ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ከላይ በተገለፁ ሁለት መመሪያዎች የማይሸፈኑ/መስተናገድ የማይችሉ በመሆናቸው ምክንያትና እነዚህ ህገ-ወጥ ተግባሮችም የግድ  መፍትሔ ማግኘት ስለአለባቸው ይህን መመሪያ ለማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡

II.  ክፍል አንድ

   ጠቅላላ

1.  አጭር ርዕስ፣

ይህ መመሪያ በኤጄንሲው ቤቶች ላይ የተፈፀሙ ውስብስብ ህገ-ወጥ ተግባራትን መፍትሔ ለመስጠት የተዘጋጀ መመሪያ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2.  ዓላማ፣

2.1. ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ በተፈፀሙ ውስብስብ እና ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ መፍትሔ ለመስጠት፣

2.2. በአዋጅ 555/2000 አንቀጽ 6(3) ማስፈፀሚያና በቤቶች አስተዳደር መመሪያዎች የማይሸፈኑ ጉዳዮችን ህጋዊ በሆነ አሰራር ለማስተካከል፣

2.3. በመንግስት ሀብት ግለሠቦች አላግባብ ሣይሠሩ እየከበሩ ያለበትን የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ በተቻለ መጠን ለማድረቅ፣

2.4. የኤጄንሲውን የቤቶች አስተዳደር ስርዓት መልክ ለማስያዝ እንዲቻል፣

2.5. ኤጄንሲው ከሚያስተዳድራቸው ንግድ ቤቶች መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ ለማድረግ፣

2.6. በንግድ ሥራ የተሠማራውን ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ፣

2.7. ከዚህ በኋላ ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቀነስ፣

3.  ትርጓሜ፣

     የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ፣

3.1.  “ኤጄንሲ” ወይም ዳይሬክተር “ማለት እንደቅደም ተከተላቸው የመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ ወይም የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ማለት ነው፡፡

3.2.  “ሽንሽን” ማለት ከኤጄንሲው እውቅና ውጪ የተከራየውን ቤት ቅርፁን ሙሉ በሙሉ ቀይሮና አፍርሶ መስራት ወይም የቤቱን በረንዳዎች መውጣጫዎች፣ መተላለፊያዎችን ዘግቶ ወደ ብዙ ክፍል መቀየር ወይም የቤቱን ግድግዳ አፍርሶ ክፍል ማስፋት ሲሆን በአጠቃላይ በአዋጅ 555/2000 አንቀጽ 6(3) ማስፈፀሚያ መመሪያ አንቀጽ 2 (4) የተጠቀሡትን ያጠቃልላል፡፡

3.3.  “ሠው ማለት” የተፈጥሮ ሠው ወይም በሕግ የሠውነት መብት የተሠጠው ድርጅት ወይም መስሪያ ቤት ማለት ነው፡፡

3.4.  “ቅሬታ” ማለት የዚህን መመሪያ አፈፃፀም ሂደት ተከትሎ የሚሰጡ ውሣኔዎችን በመቃወም ለቅሬታ ሠሚ ኮሚቴ የሚቀርብ አቤቱታ ነው፡፡

3.5.  “ቅሬታ ሠሚ” ማለት በዚህ መመሪያ አፈፃፀም ምክንያት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መርምሮ ውሣኔ እንዲሠጥ የተቋቋመ አካል ነው፡፡

3.6.  “ህገ-ወጥ ተግባር” ማለት ከኤጄንሲው የተከራየውን ቤት ከኤጄንሲው እውቅና ውጪ የቤቱን ቅርፅ ቀይሮና አፍርሶ ክፍሎች መስራትና ማከራየት ወይም የተከራየውን ቤት ለሦስተኛ ወገን ማከራየት ወይም የተከራየውን ቤት አገልግሎት ከኤጄንሲው እውቅና ውጪ ቀይሮ ለሌላ አገልግሎት መጠቀም ወይም በተከራየው ቤት ይዞታ ላይ ተጨማሪ ግንባታ ማከናዎን ማለት ነው፡፡

3.7.  “አብይ ኮሚቴ” ማለት በዚህ መመሪያ መሠረት አፈፃፀሙን በበላይነት የሚመራና የሚከታተል በዋና ዳይሬክተር ሠብሳቢነት የተቋቋመ ኮሚቴ ማለት ነው፡፡

3.8.  “አስፈፃሚ ኮሚቴ” ማለት በዚህ መመሪያ መሠረት በአራቱም የቅርንጫፍ የስራ ሂደቶች አፈፃፀሙን የሚመራና የሚከታተል በስራ ሂደት መሪው ሠብሳቢነት የተቋቋመ ኮሚቴ ማለት ነው፡፡

  1. 4.     የተፈፃሚነት ወሠን፣

ይህ መመሪያ ተፈፃሚነት የሚኖረው ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ ይህ መመሪያ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ማለትም በዚህ መመሪያ አንቀፅ 5፣6፣7፣8 እና 9 ላይ የተመለከቱትን  በአዋጅ 555/2000 አንቀፅ 6(3) ማስፈፀሚያና በቤቶች አስተዳደር መመሪያዎች መሸፈን ያልቻሉትን ይሆናል፡፡

  1. III.     ክፍል ሁለት

በህገ-ወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን የተላለፉ ወይም የተሸነሸኑ የንግድ ቤቶችን በተመለከተ፣

5.  ቤቱን ሸንሽነው ለሦስተኛ ወገኖች ባከራዩ ላይ ስለሚወሠድ እርምጃ፣\

5.1. በሽንሽን ቤቱ የተከራዩ ግለሠቦች ማህበር አቋቁመው እንዲመጡ ይደረጋል፡፡

5.2. የተሸነሸነው ቤት እያንዳንዱ ክፍል የጨረታ መነሻ ዋጋ ተመን ከወጣለት በኋላ 10% ተጨምሮ በማህበሩ ስም ዉል እንዲሞሉ ይደረጋል ፡፡

5.3. በዚህ መመሪያ መሠረት ተጠቃሚ የሚሆኑ አንድ ቤት ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ተከራዮች በየግላቸው በሚነግዱበት ሽንሽን ወይም ክፋይ ለኪራይ ዓላማ ሲባል በየግላቸው ውል ገብተው ይስተናገዳሉ፡፡

5.4. በተራ ቁጥር 5.3 የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ የእያንዳንዱን ሽንሽን እጣፋንታ እና የነባሩን የቤቱን ይዘት በተመለከቱ ጉዳዮች ግን በሽንሻኖ በአጠቃላይ የሚነግዱ ተከራዮች በጋራ በመሠረቱት ማህበር ወይም አደረጃጀት አማካኝነት ብቻ ከመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ በሚደረግ ግንኙነት የሚወሰን ይሆናል፡፡

5.5. የመጀመሪያ የውል ተከራይ በተሸነሸነው ቤት ውስጥ በግሉ የያዘው/የያዘችው ክፍሎች ካሉ ኪራይ በጨረታ መነሻ ዋጋ ተተምኖና 10% ተጨምሮ ህጋዊ ይደረጋል፡፡

5.6. የተከራዩትን ቤት ሳይሸነሽኑ ወይም ሣይከፋፍሉ የቤቱን የተወሠኑ ክፍሎች ራሣቸው እየተገለገሉ የተወሠኑትን ለሦስተኛ ወገን ያከራዩት ከላይ ከተራ ቁጥር 5.1-5.5 በተጠቀሠው መሠረት ይስተናገዳሉ፡፡

6. ቤቱን ሸንሽነው ወይም ከፋፍለው ለሦስተኛ ወገን ሣያስተላልፉ ራሣቸው ለተለያዩ የንግድ አገልግሎት በሚጠቀሙ፣

6.1. የተከፋፈሉትን ወይም የተሸነሸኑትን ቤቶች የእያንዳንዳቸው የጨረታ መነሻ ዋጋ አውጥቶና 10% ጨምሮ የቤቱን የኪራይ ተመን በማውጣት ይከራያል፣

6.2. በተመኑ መሠረት ማህበር (PLC) ከሆነ ማህበሩ በውልና ማስረጃ ወይም በፍርድ ቤት የፀደቀ ማስረጃ ሲያቀርብ ወይም ማህበር ከሌለው በተከራዩ ስም  ይህ መመሪያ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በ6.1 መሠረት ውል እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡

6.3. የቤቱ አገልግሎትም በቤት አከረያየት መመሪያ መሠረት ይፈፀማል፣

6.4. ተከራዩ በዚህ ካልተስማማ ቤቱን  እንዲያስረክብ ይደረጋል፡፡

7.  የተከራዩትን የንግድ ቤት ለሦስተኛ ወገን ባስተላለፉት ተከራዬች፣

7.1. የቤቱ የጨረታ መነሻ ዋጋ እንዲተመን ከተደረገ በኋላ 10% ተጨምሮ አጠቃላይ የቤቱ ወርሃዊ ኪራይ በመተመን በሶስተኛ ወገን ተከራዮች ስም ዉል ይሞላል፡፡

7.2.  ተከራዩ ማህበር (PLC) ከሆነ በተመኑና በተራ ቁጥር 6.2 መሠረት ሂሳቡን ከፍሎ ውል እንዲሞላ ይደረጋል፡፡

8. የመኖሪያ ቤትን ወደ ንግድ ድርጅት በቀየሩ ወይም በሁለቱም አገልግሎት እየተጠቀሙ ባሉ፣

8.1. የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ንግድ ድርጅት የቀየሩትን እና ራሣቸው እየተገለገሉበት ያሉትን በመለየት የንግድ ቤቱን የጨረታ መነሻ ዋጋ በመተመንና 10% በመጨመር በተመኑ መሠረት ይህ መመሪያ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የሚኖረው ሂሳብ ከፍለው ውል እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡

8.2. ወደ ንግድ ድርጅት የተቀየረውን ቤት ሙሉ በሙሉ ለሦስተኛ ወገን የተላለፈ ከሆነ ሦስተኛ ወገኑ በተራ ቁጥር 8.1 ላይ በተተመነው መሠረት ይህ መመሪያ ሥራ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ የሚኖረው ሂሳብ ከፍሎ ውል እንዲሞላ ይደረጋል፡፡

8.3. ቤቱን እየተገለገለበት ያለው የንግድ ማህበር (PLC) ከሆነ በተመኑ እና በ6.2 መሰረት ውል እንዲሞላ ይደረጋል፣

8.4. ከቤቱ የመኖሪያ አገልግሎት በተጨማሪ ከፊሉን ወይም በቤቱ ይዞታ ላይ ግንባታ ገንብቶ የንግድ አገልግሎት እየሠራ ያለ ከሆነ ለንግድ ቤቱ በህዝባር ቁጥር ተሠጥቶት የቤቱ የኪራይ ተመን ከላይ በተራ ቁጥር 8.1-8.3 በተጠቀሠው መሠረት እንዲስተናገድ ይደረጋል፡፡

8.5. በተራ ቁጥር 8.4 የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ የንግድ ድርጅቱን ለሦስተኛ ወገን ያከራዩ ከሆነ ቤቱን በህዝባር ቁጥር ተሠጥቶት ለሦስተኛው ወገን በተተመነው የቤቱ ኪራይ እንዲሁም ማህበር ከሆነ በተራ ቁጥር 6.2 መሠረት ውል እንዲሞላ ይደረጋል፡፡

9. በዳግም የንግድ ምዝገባ የተመዘገቡም ሆነ ያልተመዘገቡ ተከራዮችን  ስለማስተናገድ

በዚህ መመሪያ አንቀጽ 5-8 የተጠቀሱት ሕገ-ወጥ ተግባራት የተፈጸመባቸውን ንግድ ቤቶች ከግለሰቦች ተከራይተው የነበሩና በአከራዮቻቸው ጫና ከሐምሌ 1  ቀን 2003 ዓ.ም ወዲህ ከቤቱ እንዲለቁ የደረጉ ወይም እስከአሁን በቤቱ እየተገለገሉ ያሉ ንግድ ፍቃድ ባይኖራቸውም ከሚከተሉት መስፈርቶች አንዱን ካሟሉ፣

9.1  በቤቱ ተከራይተው ኪራይ ይከፍሉ እንደነበረ የሚያስረዳ በአከራዩ የተፈረመ የክፍያ ሰነድ ወይም፣

9.2  በአሻራ ላይ የተመሠረተ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ወይም፣

9.3  በመካከላቸው የተደረገ የአከራይ ተከራይ ውል ወይም፣

9.4  በአካባቢው በሚገኙ ሕጋዊ ነጋዴዎች ቢያንስ በሶስት ሰው ምስክርነት በቤቱ  ይገለገል እንደነበረ ወይም እየተገለገለበት ለመሆኑ ሲረጋገጥ የኪራይ ውል እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡

10.  ልዩ ሁኔታዎች

 

ከተራ ቁጥር 5 እስከ 9 የተገለፀው ቢኖርም ንግድ ቤቱን ያከራዩት ሌላ መጦሪያ የሌላቸው አረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የኤች አይቪ ህመምተኞች፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ በሽተኞች እና ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናት ከሚመለከተው ህጋዊ ተቋም ማስረጃውን እንዲያቀርቡ እና እንደቤቱ ሁኔታ ታይቶ ውል ሞልተው እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡

11.  ይህ መመሪያ የማይሸፍናቸው ጉዳዮች፣

11.1. ይህ መመሪያ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ  ከሆነ፤

11.2. ምንም አይነት ህገ-ወጥ ተግባር ሣይፈፀምበት ነገር ግን ከ3 ዓመት ወዲህ በተሠጠ ውክልና የተያዙ ንግድ ቤቶች ከሆኑ፤

11.3. ከዚህ ቀደም በተወሠደ እርምጃ ህገ-ወጥ ድርጊቱ የተስተካከለባቸው ቤቶች ከሆኑ፤ማለትም የገነቡትን ህገ ወጥ ግንባታ ያፈረሰሱና ያስተካከሉ፣ዉል የሞሉና ኪራ ከፍለዉ በሂደት ለይ ያሉትን አያካትትም፡፡

11.4. ህገ-ወጥ ድርጊት በመፈፀማቸው በመመሪያው መሠረት ቤቶቹን የተረከብናቸውን ከሆኑ፤

11.5. በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ መኖሪያ ቤቶችን አያካትትም፡፡

11.6. ይህ መመሪያ ስራ ላይ ከዋለ ከ ______ጥቅምት 17 2004 ዓም ጀምሮ ኤጄንሲው በሚያስተዳድራቸው የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ህገ-ወጥ ተግባር የተከራየውን ቤት ያስነጥቃል፡፡

  1. IV.     ክፍል ሦስት

አብይ፣ አስፈፃሚ እና የቅሬታ ሠሚ ኮሚቴዎችን ስለማቋቋም፣

12. አብይ ኮሚቴ

12.1. በኤጄንሲው ደረጃ የሚቋቋመው ኮሚቴ በዋና ዳይሬክተር የሚመራ ሆኖ  ሌሎች ስምንት አባላት ይኖሩታል፡፡

12.2 በዚህ መመሪያ ከአንቀጽ 5 እስከ 10 የተመለከቱትን ተግባራት በየቅርንጫፍ የስራ ሂደቱ በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል በየጊዜው በአፈፃፀም ሂደት ወቅት ለሚገጥሙ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

12.3. በማዕከል በአዲስ አበባ ደረጃ በተቋቋመው ኮሚቴ የሚሠጡ አቅጣጫዎችን ተቀብሎ በኤጄንሲው ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጋል፣

12.4. የአብይ ኮሚቴው የስብሰባ ጊዜ በኮሚቴው እንደአመችነቱ ይወሠናል፣

13.  አስፈፃሚ ኮሚቴ

 

13.1. በአራቱም የቅርንጫፍ የስራ ሂደቶች በስራ ሂደት መሪው የሚመራ ሌሎች 5 አባላት ያሉት ኮሚቴ ይሆናል፡፡

13.2. በየቅርንጫፉ የተቋቋመው ኮሚቴ እንደአመቺነቱ ፈፃሚዎችን በቡድን እያደራጀ ያሠማራል፣ ይከታተላል፣ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል፡፡

13.3. በየቅርንጫፍ የስራ ሂደቱ የተቋቋመውን ኮሚቴ ለስራው አጋዥ በሆነ መልኩ በየአካባቢው ከሚገኙ ከክ/ከተማ መስተዳድር እና የፖሊስ አካላት፣ የወረዳ አመራሮች ጋር እየተገናኘ መረጃ ይለዋወጣል፣ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል፣

14.  የአስፈፃሚ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት፣

14.1    ይሄን መመሪያና ሌሎች ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ሠነዶችን እንዲሁም ስለስራው አፈፃፀም ለአስፈፃሚዎች ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡

14.2    በዚህ መመሪያ መሠረት የሚሸፈኑ ህገ-ወጥ ተግባር የተፈፀመባቸውን ቤቶች ዝርዝር መረጃ አደራጅቶ ይይዛል፣

14.3    የእያንዳንዱ ቤት የኪራይ ተመን በባለሙያዎች ተሠርቶ እንዲቀርብ ያደርጋል፣

14.4    ከተከራዬች የሚፈለጉ መረጃዎች በወቅቱ ተሟልተው እንዲቀርቡ ያደርጋል፣

14.5    የቀረበው የእያንዳንዱ ቤት መረጃና የኪራይ ተመን ትክክለኛ መሆኑን እያረጋገጠ ውል በዚህ መሠረት ውል እንዲሞላ ያደርጋል፣

14.6    በአፈፃፀም ወቅት የታዩ መልካም ተሞክሮዎችንና የገጠሙ ችግሮችን እንዲሁም የተወሠዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እየቀመረ ለአብይ ኮሚቴው ሪፖርት ያደርጋል፣

15.  የቅሬታ ሠሚ ኮሚቴ ስለማቋቋም፣

 

በአዋጅ 555/2000 አንቀፅ (3) ማስፈፀሚያ መመሪያ መሠረት በተከራዩት ቤት ህገ-ወጥ ተግባር በፈፀሙና ቤቱን ለሦስተኛ ወገን ባስተላለፉት ላይ በሚወሠድ እርምጃ ቅሬታ የሚያቀርቡ ዜጐችን ለማስተናገድ በቅርቡ በኤጄንሲው ስራ አመራር አማካኝነት የተቋቋመው ኮሚቴ ይሄን ተግባር በሃላፊነት ያከናውናል፣

የቅሬታ ሠሚው ኮሚቴ በ5/01/2004 በፀደቀው እና በዚህ መመሪያ መሠረት ቅሬታዎችን ተቀብሎ ስራውን ያከናውናል፡፡

የቅሬታ ሠሚው ኮሚቴ የደረሠበትን ውጤት ለአብይ ኮሚቴው ሪፖርት ያቀርባል፡፡

የቅሬታ ኮሚቴው ስራውን ከመጀመሩ በፊት ስለዚህ መመሪያ ይዘትና አፈፃፀም የተሟላ ግንዛቤ እንዲይዙ ይደረጋል፡፡

VI.  ክፍል አራት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን

16.  ስለይርጋ

በኤጄንሲው ውሣኔ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ሠው ውሣኔውን ካወቀበት በ5 ቀን ውስጥ ቅሬታውን ለቅሬታ ሠሚ ኮሚቴ ካላቀረበ ቅሬታው በይርጋ ውድቅ ይሆናል፡፡

17.  በዋቢነት ማለፍ፣

ይሄን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በተቀመጠው አሠራር መሠረት ስራቸውን ለማከናወን በሚንቀሣቀሡ የኤጄንሲው ሃላፊዎችና ሠራተኞች የሚመሠረት የፍታብሔር ክስ ኤጄንሲው በዋቢነት ያልፋቸዋል፡፡

  1. 18.   መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ ከህዳር 18 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s