የተቀላቀለ የግልና የጋራ ንብረት በፍቺ ወቅት ስለሚከፋፈልበት ሁኔታ፤ በ7 ቀናት ልዩነት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በሰበር የተሰጠ የተለያየ ውሳኔ


የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጥ የህግ ትርጉም ለበታች የክልልና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት እንዲኖረው የሚል አስገዳጅ ህግ ከወጣ (አዋጅ ቁጥር 454/1997) ድፍን ስድስት ዓመት አለፈው በነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ህጉና አፈጻጸሙ ለፍትህ ስርዓቱ ያደረገው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እና ያስከተለው ችግር በተመለከተ የዳሰሳና የክለሳ ጥናት ተደርጎ ውጤቱ ይፋ የሆነ ሪፖርት እስካሁን ድረስ የለም እስከ አሁን ድረስ የህጉ አጠቃላይ ተቀባይነት መሰረት ያደረገው አሰራሩ ወጥነትን ያመጣል ከሚል በሀሳብ ደረጃ ሊያሳምን የሚችል አመለካከት እንጂ በተግባር ተፈትኖ እየታየ ያለ ሀቅ አይደለም፡፡

እንግዲህ ተግባራዊ የመለኪያ ሚዛንን ለጊዜው ወደ ጎን እንተወውና ወጥነት የአዋጁ ዋና ዓላማና ግብ ነው ብለን እንነሳ፡፡ ችግሩ ግን ከዚሁ ይጀምራል፡፡ አዋጅ ቁጥር 454/1997 ወጥነትን እንደ ዋና ሆነ ተጓዳኝ ዓላማና ግብ ይዞ ስለመነሳቱ በግልጽ የሚነግረን ነገር የለም፡፡

በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 454/1997 ሊወጣ የቻለው ስለፌደራል ፍርድ ቤቶች የወጣውን አዋጅ ቁጥር 25/88 (እንደተሻሻለ) እንደገና ማሻሻል አስፈለጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የአስፈላጊነቱ መሰረት ምን እንደሆነ በግልጽ የተመለከተ ነገር የለም፡፡
አዋጁ ዝምታን ቢመርጥም የሰበር ውሳኔ አስገዳጅነት እንዲኖረው የሚደነግገው ህግ ሊያሳካ የፈለገው አንደኛው ግብ የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች በተመሳይ ጉዳይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ወጥነት እንዲኖራቸውና ተገማች እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ ታሳቢ አድርገን እንነሳለን፡፡
እንግዲህ ወጥነትና ተገማችነት የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ዋነኛው ገጽታ እንዲሆን ከታለመ ከብዙ ነገሮች መሐል ቢያንስ የሚከተሉት ሁለቱ ተሟልተው ይገኙ ዘንድ ግድ ይላል ፡፡

1. በሰበር ችሎቱ በራሱ የሚሰጡ ውሳኔዎች ወጥነት ሊኖራቸው ይገባል
ምንም እንኳን የሰበር ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ እንዲሚችል በአዋጁ ላይ የተመለከተ ቢሆንም ድንጋጌው በጠባቡ ብቻ ሳይሆን ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበ ሁኔታ ካልተተገበረ የሰበር ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ሊኖረው የሚገባውን የተሰሚነትና የተቀባይነት ደረጃ በእጅጉ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ በአንድ ጭብጥ ላይ በጊዜው የሚቀያየር የሰበር ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ዘንድ ተፈጻሚነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ አሁንም በተግባር እንደሚታየው የስር ፍርድ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ የሰበርን ውሳኔ የሚጠቅሱት መጀመሪያውኑ የሚያምኑበትን አቋም የሚያጠናክርና የሚደግፍ ሆኖ ሲያገኙት ነው፡፡ ፈጽሞ መዘንጋት የሌለብን ነገር የስር ፍርድ ቤቶች ህግን እንደሚተረጉሙት ሁሉ የውሳኔውንም ይዘት ለመተርጎም ሰፊ ስልጣን አላቸው፡፡ ስለሆነም በአንድ ጭብጥ ላይ ወዲያው ወዲያው በሰበር ችሎት የአቋም ለውጥ በሚኖር ጊዜ የስር ፍርድ ቤቶችን ከማደናገሩም በላይ የውሳኔውን የተሰሚነት ደረጃ ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህም
• በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም መስጠት እጅግ አስፈላጊ የሚያደር ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች መኖራቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ አንድ ጊዜ የተሰጠ ውሳኔ ፀንቶ ሊቆይ ይገባል
• የተለየ ትርጉም ሲያስፈልግ ለውጥ ማድረግ የተፈለገበትን ምክንያት በአዲሱ ውሳኔ ላይ በግልጽ ማመልከትና የበፊቱን ውሳኔ በማያሻማ መልኩ በግልጽ መሻር ያስፈልጋል

2. በሰበር የተሰጠ ውሳኔ በብርሀን ፍጥነት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችና ለሕዝቡ መድረስ አለባቸው ቅጽ እስኪዘጋጅ ከዓመት በላይ እየተጠበቀ ውጤት ለማግኘት የሚታሰብ አይደለም

3. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጥ የህግ ትርጉም ለበታች የክልልና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት ኖሮት በዚህም ወጥነትና ተገማችነት ያለው ብሎም ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ የዳበረ የፍትህ ስርዓት ሊኖር የሚችለው “ከአምስት ያላነሱት ዳኞች” ሁሌም ቋሚ የችሎቱ ዳኞች ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ቁጥራቸው 5 ሆነ 50 ዋናው አስፈላጊ ነገር በችሎት ላይ የሚቀመጡት ዳኞች እስከመጨረሻው እነዛው ዳኞች ብቻ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በተመሳሳይ ጭብጥ ተቃራኒና እርስ በርሱ የሚጋጭ ውሳኔ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በአንድ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ የሆኑ የሰበር ውሳኔዎች ተሰጥተዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተዳሰሱት ሁለት ውሳኔዎች ግን ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ የሚለያቸውም ውሳኔዎቹ በአንድ ሳምንት ልዩነት መሰጠታቸው ማለትም በአጭር ቀናት ልዩነት መሰጠታቸው ሲሆን እርስ በእርስ ከሚቃረኑ ሌሎች ውሳኔዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ደግሞ በሁለቱም መዝገቦች ላይ የተሰየሙት ዳኞች በከፊል የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡

አንባቢያን በራሳችሁ ትረዱት ዘንድ በሁለቱ መዝገቦች ላይ የተነሳው ፍሬ ነገር፡ ለውሳኔ መሰረት የተደረገው ህግ፡ የችሎቱ ትንተናና ሐተታ በመጨረሻም በሁለቱም መዝገቦች ላይ የተደረሰው ተቃራኒ አቋም እንደሚከተለው ቀርቦላችኋል

ውሳኔ አንድ

የማይንቀሳቀስ ንብረት (መኖሪያ ቤት) ግንባታ ከጋብቻ በፊት ቢጀመርም ግንባታው የተጠናቀቀው ባልና ሚስት በጋብቻ ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ ውስጥ ከሆነ በተለይም አንደኛው ወገን ለቤቱ ግንባታ የገንዘብ አስተዋጽኦ አድርጎ ከሆነ በፍቺ ጊዜ ሁለቱም የቤቱን እኩል ድርሻ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

የሰ/መ/ቁ. 25005
ኀዳር 3 ቀን 2000 ዓ.ም.

አመልካች፡- መኮንን በላቸው
ተጠሪ፡- ወ/ሮ አለሚቱ አደም

በዚህ ጉዳይ ላይ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት ያረፈበት መሬት ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት ተጠሪ በማኀበር ከተመራች በኋላ የቤት ስራው መስከረም 29 ቀን 1979 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን ጋብቻው ታሕሣሥ 26 ቀን 79 ዓ.ም. ተፈጽሟል ቤቱ ሥራው አልቆ ለማኀበሩ አባላት የተከፋፈለው በጥቅምት ወር 1980 ዓ.ም. ሲሆን ቤቱ ተስፋፍቶ የተሠራውና ቤትም የሆነው ግን ጋብቻው ከተፈፀመ በኋላ ነው፡፡ ለቤቱ ማሠሪያ ከባንክ በብድር ገንዘብ የወሰደችው ተጠሪ ብትሆንም፣ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ ጋብቻው በፍቺ እስከፈረሰበት 93 ዓ.ም. ድረስ በአመልካች በኩል ሲከፈል መቆየቱ በስር ፍ/ቤቶች በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቤቱ ግንባታ ከጋብቻ በፊት መጀመሩን መሰረት በማድረግ ቤቱ የተጠሪ የግል ሀብት ነው ካለ በኋላ አመልካች ለቤቱ ያወጣው ገንዘብ ታስቦ ይመለስለት የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ቅሬታ ያደረበት አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን የሰበር ችሎቱም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕ/አዋጅ ቁ. 213/92/ አንቀጽ 62/1/ በመጥቀስ በዚሁ ህግ መሰረትም የባልና ሚስት የጋራ ሃብት የሚባለው ባልና ሚስቱ ከግል ንብረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኙትን ገቢዎች ሁሉ እንደሚያጠቃልል በተጨማሪም አንደኛው ተጋቢ ሃብቱ የግሉ ስለመሆኑ ካላስረዳ ንብረቱ በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበም ቢሆን የባልና ሚስቱ የጋራ ሃብት ነው ተብሎ በሕግ እንደሚገመት ሐተታ በመስጠት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመሻር ቤቱን ተጠሪና አመልካች እኩል እንዲከፋፈሉት ውሳኔ ሰጥቷል
ውሳኔ ሁለት

የማይንቀሳቀስ ንብረት (መኖሪያ ቤት) ግንባታ ከጋብቻ በፊት ተጀምሮ ባልና ሚስቱ በትዳር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ከተጠናቀቀ በፍቺ ወቅት ለንብረቱ መገኘት ተጋቢዎቹ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተመርምሮ እንደነገሩ ሁኔታ የግል ወይም የጋራ ሊባል ይገባል፡፡ ይህንንም ለመወሰን በንጽጽር ሲታይ አብዛኛው መዋጮ የተደረገው የግል ነው ወይስ ከጋራ የሚለውን ከግምት ማስገባቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ንብረቱ በአብዛኛው ከጋራ ሃብት መዋጮ የተገኘ ከሆነና የግል ንብረቱ ትንሽ ከሆነ ንብረቱ የጋራ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ በንብረቱ ላይ የተቀላቀለውን የግል ሃብት በተቀላቀለው መጠን የግሉ የሆነው ተጋቢ ሊወስድ ይገባል፡፡

የሰ/መ/ቁ. 26839
ኀዳር 10 ቀን 2000 ዓ.ም.
አመልካች፡- ወ/ሮ አስካለ ለማ
ተጠሪ፡- ሣህለ ሚካኤል በዛብህ

በዚህ ጉዳይ ላይ ክርክር የተነሳበትን ቤት በተመለከተ በተጠሪ የቀረበው መከራከሪያ በ82 ካ.ሜ. ላይ የተሠራ ቪላ ቤት ከጋብቻ በፊት የተሰራ የግሌ ነው የሚል ሲሆን አመልካች በበኩላቸው የግል ቤቴን ሸጬ ባገኘሁት ገንዘብ ቤቱን ከማኀበሩ ተረክበን አፍርሰን አሁን ያለውን ይዘት እንዲኖረው አድርገን ስለሰራነው እንዲሁም ቤቱን ለመስራት የዋለው እዳው ከጋብቻ በኋላ የተከፈለ ስለሆነ ቤቱ የተጠሪ የግል ንብረት ሊባል አይገባም በማለት ተከራክረዋል

ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ ያየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ክሱን ያቀረቡት ደግሞ ተጠሪ ናቸው ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ቤቱ የተጠሪ የግል ንብረት ነው ካለ በኋላ አመልካች በጋብቻው ወቅት ላደረጉት የገንዘብ አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ተሰሩ የተባሉት ስራዎች ተገምተው ብር 82‚293 (ሰማኒያ ሁለት ሺ ሁለት መቶ ዘጠና ሶስት) ስለሆኑ የዚህን ዋጋ ግማሽ ተጠሪ ለአመልካች ከፍለው ቤቱን
ያስቀሩ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል ጉዳዩን በይግባኝ ያየው የፌ/ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የስር ውሣኔን አጽንቶታል፡፡

በመጨረሻም በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ቅር በመሰኘት አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን መርምሮ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ለችሎቱ የቀረበውን ጉዳይ በፍቺ ወቅት የጋራ ንብረት አከፋፈልን የሚገዙት መደበኛ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በውሳኔው የሐተታ ክፍል ላይ ገልጾታል

ፍርድ ቤቱ እንዳለው “ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በየግላቸው ያገኗቸው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ሆነው እንደሚቀሩ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቁጥር 57 ያመለክታል፡፡ አንድ ንብረት ከግል እና ከጋራ ሃብት ተቀላቅሎ የተገኘ ከሆነ ግን ንብረቱ የጋራ ወይም የግል ተብሎ እንደሚቆጠር የሕጉ ድንጋጌ በግልጽ አያመለክትም፡፡”

ይህን መሰሉ ሁኔታ ሲጋጥም የንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ተፈጻሚ የሚሆነው ድንጋጌ ከዓላማው አንጻር ሊተረጎም እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡ በዚሁ መሰረት የሰበር ችሎቱ የሚከተለውን ሐተታ ሰጥቷል

“ከጋብቻ በፊት የነበረ ንብረት የጋራ እንዳይሆን የተፈለገበት ምክንያት ጋብቻ ንብረት ለማግኘት በሚል ሃሣብ ብቻ እንዳይቋቋምና እንዳይፈርስ ለመከላከል ሲባል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ምንም ንብረት ያልነበረው ሰው ንብረት ያለውን ሰው በማግባት ጋብቻ ሲፈርስ ያላፈራውን ንብረት የሚካፈልበት ሁኔታ ማመቻቸት ለፍትሕ እና ለሕሊና ተቃራኒ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡”

ስለሆነም ከዚህ በችሎቱ ከተቀመጠው ዓላማ አንጻር ለንብረቱ መገኘት ተጋቢዎቹ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተመርምሮ እንደነገሩ ሁኔታ የግል ወይም የጋራ ሊባል ይገባል፡፡ ይህንንም ለመወሰን በንጽጽር ሲታይ አብዛኛው መዋጮ የተደረገው ከግል ነው ወይስ ከጋራ የሚለውን ከግምት ማስገባቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ንብረቱ በአብዛኛው ከጋራ ሃብት መዋጮ የተገኘ ከሆነና የግል ንብረቱ ትንሽ ከሆነ ንብረቱ የጋራ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ በንብረቱ ላይ የተቀላቀለውን የግል ሃብት በተቀላቀለው መጠን የግሉ የሆነው ተጋቢ ሊወስድ ይገባል፡፡

ችሎቱ በውሳኔው ላይ ትኩረት ሰጥቶ የገለጸው ጉዳይ ንብረቱ በአብዛኛው ከጋራ ሃብት መዋጮ ሲገኝ የንብረት ክፍፍሉ ምን መምሰል እንዳለበት ሲሆን በተቃራኒው ንብረቱ በአብዛኛው ከግል ሃብት መዋጮ ሲገኝ ክፍፍሉ ምን መምሰል እንዳለበት በግልጽ የደረሰበት ድምዳሜ የለም ይሁን እንጂ አጠቃላይ በሆነ አነጋገር ንጽጽርን መሰረት ባደረገ መልኩ “አብዛኛው መዋጮ የተደረገው ከግል ነው ወይስ ከጋራ የሚለውን ከግምት” ማስገባት እንደሚያስፈልግ ችሎቱ ግልጽ አቋም ላይ የደረሰበት ነጥብ በመሆኑ የግል ሃብት መዋጮ በአብዛኛው በልጦ ሲገኝም በተመሳሳይ መልኩ ንብረቱ የግል ከተባለ በኋላ በትዳር ውስጥ የነበረው የጋራ መዋጮ ተገምቶ ላዋጣው ወገን ተመላሽ ሊሆንለት እንደሚገባ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል

በሁለቱም ሁኔታዎች የግልና የጋራ የንብረት ተቀላቅሎ በሚገኝበት ጊዜ ለአንደኛው ወገን መዋጮው ሲመለስለት ያዋጣው መጠን ስለሚለካበት መንገድ የሰበር ችሎት ከስር ፍርድ ቤቶች የተለየበት ነጥብ ነበር ስለሆነም አብዛኛው መዋጮ የጋራ ሲሆን በመጀመሪያ ከጋብቻ በፊት የተሠራው ሥራ ምን ያሕል እንደሆነ ተጣርቶ መታወቅ አለበት

በመቀጠልም በጋብቻ ውስጥ የተሰራው ስራ በመሃንዲስ ሳይሆን በገበያ ዋጋ ተገምቶ መቅረብ ይኖርበታል ምንም እንኳን ችሎቱ በጋብቻ ውስጥ የተሰራው ስራ መገመት እንዳለበት የጠቆመ ቢሆንም የውሳኔው አጠቃላይ ክፍል በተለይም ውሳኔ በሚል ርዕስ የተሰጠው የውሳኔው ክፍል ሲታይ ችሎቱ ይህን አባባል የተጠቀመው የቤቱን አጠቃላይ ግምት ለማለት ነው ቤቱ መገመት ያለበትም በመሐንዲስ ማለትም ጣራ ግድግዳው ቆርቆሮው ወዘተ…ሳይሆን በገበያ ዋጋ መሰረት ነው

ችሎቱ ሐተታውን ከላይ በተመለከተው መልኩ ከሰጠ በኋላ አስገዳጅ ወይም አሳሪ በሆነው በውሳኔው ክፍል የሚከተለውን ፍርድ ሰጥቷል

ሀ. ክርክር የተነሳበትን ቤት በተመለከተ በፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት የተሰጠው የውሣኔ ክፍል ብቻ ተሽሯል፡፡
ለ. የክርክር ምክንያት የሆነው ቤት የግራ ቀኙ የጋራ ሃብት ነው፡፡
ሐ. ከጋብቻ በፊት የተሠራው ሥራ ተገምቶ ግምቱ ለተጠሪ ይከፈል፡፡ ቤቱን ከተቻለ ግራ ቀኙ በዓይነት ይካፈሉ፣ ካልተቻለ አንዱ ለአንዱ የቤቱን የገበያ ዋጋ ግምት ከፍሎ ያስቀር፣ በዚህ የማይስማሙ ከሆነ ቤቱ ተገምቶ በሃራጅ ተሸጦ የሽያጩን ገንዘብ እኩል ይካፈሉ፡፡

1 Comment

 1. Yitbay Ze Gendekore says:

  1. “በሰበር የተሰጠ ውሳኔ በብርሀን ፍጥነት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችና ለሕዝቡ መድረስ አለባቸው…(speed of light = 299 792 458 m / s) “ፅድቁ ቀርቶብኝ…”
  2. “በችሎት ላይ የሚቀመጡት ዳኞች እስከመጨረሻው እነዛው ዳኞች ብቻ ሊሆኑ ይገባል፡፡” i.e life tenure?

  They have the authority to overturn old precedents and set new ones when appropriate but not within days. Like a well-known example in Supreme Court of the United States – when the Warren Court decided segregation was unconstitutional in Brown v. Board of Education, (1954). This overturned a precedent known as the “separate but equal” doctrine affirmed in Plessy v. Ferguson, (1896) that declared providing separate facilities for African-Americans and Caucasians was constitutional, as long as the facilities were of equal quality (which was seldom the case).
  I agree with you all Abraham.
  An article worth sharing!

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s