የቤት ዋጋ ከውርስ ሀብት ክፍፍል አንጻር


የመኖሪያ ቤት ዋጋ ማለትም የገንዘብ ግምት በተመለከተ በተለያዩ የፍርድ ቤት መዝገቦች የክርክር ምንጭ ሲሆን ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ከውርስ ሀብትና የባልና ሚስት የጋራ ንብረት  ክፍፍል ጋር በተያያዘ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ጎልተው የሚታዩት አቋሞችን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች በተለይም የፌደራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለቤት ዋጋ የመሃንዲስ ግምትን መሰረት ያደርጋሉ፡፡ ይህም ቤቱን ለመስራት ጥቅም ላይ የዋሉትን ዕቃዎችና የቤቱን ክፍሎች በመለካትና በመተመን የሚገኘው  ውጤት ሲሆን ሁልጊዜም ቢሆን ቤቱ ቢሸጥ ከሚያወጣው ዋጋ ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከውርስና ከፍቺ ጋር በተያያዘ ንብረት ሲገመት የገበያ ዋጋ ማለትም ቤቱ በዕለቱ የሚያወጣውን የገበያ ዋጋ መሰረት ማድረግ እንዳለበት አቋም ይዞበታል፡፡

በአመልካች ወ/ሮ አስካለ ለማ  ተጠሪ ሣህለ ሚካኤል በዛብህ መካከል በሰበር ችሎት በታየ የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል ጉዳይ በሰበር መዝገብ ቁጥር 26839 ኀዳር 10 ቀን 2000 ዓ.ም. በዋለው ቸሎት በተሰጠው ውሳኔ የቤት ግምት የመሀንዲስ ግምትን ሳይሆን የገበያ ዋጋን መሰረት እንዳለበት አቋም ላይ የተደረሰበት ሲሆን የመሀንዲስ ግምት ላይ መሰረት ተደርጎ የተሰጠው የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔም በሰበር ችሎቱ ተሸሯል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የውርስ ሀብት ክፍፍልን በተመለከተም በአመልካች ወ/ሮ እልፍነሽ ከበደና ተጠሪ አቶ ፋሲል ይሔይስ (የሰበር መዝገብ ቁጥር 35013) መካከል በነበረው ክርክር ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በተሰጠው ውሳኔ የቤት ግምት ማለት የቤቱ የገበያ ዋጋ ስለመሆኑ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡

የቤት ዋጋ በመሀንዲስ አሊያም በገበያ ዋጋ ይገመት የሚል ሙግት በተካራካሪ ወገኖች ሲቀርብ በቤቱ አገማመት ላይ ሁለቱም ተጻራሪ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ ክርክር የተነሳበት ቤት በሐራጅ ተሸጦ የሚገኘው ገንዘብ የሚከፋፈል በሚሆንበት ጊዜ ዋጋ ከፍ እንዲል የሁሉም የጋራ ጥቅም እንደመሆኑ በመሀንዲስ ይገመትልኝ የሚል ወገን አይኖርም፡፡ አለመስማማቱ የሚመጣው አንደኛው ወገን የቤቱን ግምት ከፍሎ ቤቱን እንዲያስቀር መብት በሚያገኘበት ጊዜ ነው በዚህን ጊዜ ይህ ተከራካሪ ወገን ቤቱ በመሀንዲስ  እንዲገመትለት ሽንጡን ገትሮ ይሟገታል፡፡ የቤቱን ግማሽ ወይም የተወሰነ ድርሻ የሚያገኘው ተከራካሪ ደግሞ ቤቱ በገበያ ዋጋ እንዲገመትለት አጥብቆ ይከራከራል

በዚህ ረገድ ከውርስ ሀብትና የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ንብረት ክፍፍል ጋር በተያያዘ አንደኛው ተከራካሪ ወገን የቤቱን ግምት ከፍሎ ቤቱን ለራሱ ለማስቀረት መብት በሚያገኝበት ጊዜ የቤቱ ዋጋ መገመት ያለበት በመሀንዲስ ሳይሆን በገበያ ዋጋ ስለመሆኑ በሰበር አቋም የተያዘበት እንደመሆኑ የስር የፌደራል ፍርደ ቤቶች ሆኑ በማናቸውም ደረጃ የሚገኙ የክልል ፍርድ ቤቶች አቋማቸውን ከሰበር ጋር በማጣጣም ተመሳሳይ ውሳኔ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

በአመልካች ወ/ሮ እልፍነሽ ከበደና ተጠሪ አቶ ፋሲል ይሔይስ መካከል በሰበር መዝገብ ቁጥር 35013 ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም.የተሰጠው ውሳኔ ከዚህ በታች የሚገኝ ሲሆን በአመልካች ወ/ሮ አስካለ ለማ እና ተጠሪ ሣህለ ሚካኤል በዛብህ መካከል በሰበር ችሎት  የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል ጉዳይ አስመልክቶ በሰበር መዝገብ ቁጥር 26839 ኀዳር 10 ቀን 2000 በዋለው ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ እዚህ በመጫን ማውረድ ይቻላል፡፡

የሰ/መ/ቁ 35013

ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡

ዓብዱልቃድር መሐመድ

       ሂሩት መለሰ

       ታፈሰ ይርጋ

       አልማው ወሌ

       ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- ወ/ሮ እልፍነሽ ከበደ ጠበቃ ተስፋሁን ፀጋዬ ቀረበ

ተጠሪ፡- አቶ ፋሲል ይሔይስ ጠበቃ ኒቆዲሞስ ጌታሁን ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 22251 ሰኔ 12 ቀን 1998 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የከፍተኛው ፍርድ ቤት 47751 ታህሣሥ 8 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት በማመልከታቸው ነው፡፡

የክርክሩ መነሻ የአሁን ተጠሪ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ነው፡፡ ተጠሪ ወላጅ አባቱ አቶ ጽጌ ገላዬ በቀድሞው አሠራር ወረዳ 12 ቀበሌ 22 በአሁኑ አጠራር በየካ ክፍለ ከተማ 01 ቀበሌ የቤት ቁጥሩ 334 ግማሽ ድርሻ ለእኔና ለእህቴ ለወ/ሪት ኤልሳቤት ፅጌ በኑዛዜ ሰጥቶናል፡፡ ወላጅ አባታችን የቤቱ ግማሽ ድርሻ የተከሳሽ (የአሁን አመልካች) መሆኑን በኑዛዜው ገልጿል፡፡ ስለዚህ የቤቱን ግማሽ ዋጋ ክፍያ ቤቱን እንድታስረክበኝ ብጠይቃት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ተከሳሽ(አመልካች) የቤቱን ግማሽ ዋጋ ከፍላ እንድታስረክበኝ ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡ አመልካች በበኩላቸው በተከሳሽነት ቀርበው እኔ የሟች የአቶ ፅጌ ገላዬ ሚስት በመሆኔ ከሳሽ ክስ ያቀረበበት ሀብት የጋራ ሀብቴ ነው፡፡ ከሳሽ(ተጠሪ)  በቤቱ ላይ ያለው ድርሻ አንድ አራተኛ በመሆኑ የቤቱን ግማሽ ዋጋ ከፍዬ ትልቀቅልኝ ብሎ መጠየቅ አይቻልም፡፡ የእህቱንም ድርሻ መጠየቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ ከሳሽ(ተጠሪ) በቤቱ ላይ ያለውን ድርሻ ዋጋውን አልከፍልህም ብዬ ሣላሣውቀው አላግባብ የከሰሰኝ በመሆኑ መዝገቡ ከበቂ ኪሣራ ጋር እንዲያሰናብተኝ በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

ክርክሩን በመጀመሪያ ያየው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክር የተነሳበት ቤት አቶ ፅጌ ገላዬ የግል ንብረት የነበረ መሆኑና ሟች አቶ ፅጌ ገላዬ ለአመልካች የቤቱ ግማሽ ድርሻ በገንዘብ ተገምቶ እንዲወስዱ እና ሁለቱ ልጆቻቸው ቤቱን እንዲይዙ የተናዘዙ በመሆኑ ቤቱን በመሀንዲስ ባወጣው ግምት መሠረት 16‚361.65 /አስራ ስድስት ሺ ሶስት መቶ ስልሣ አንድ ብር ከስልሣ አምስት ሣንቲም/ በመቀበል ቤቱን ለተጠሪና በሥር የወ/ሪት ኤልሳቤጥ ወራሽ ነኝ በማለት በጣልቃገብነት ለተከራከረው ሰው እንዲያስረክቡ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን የከፍተኛው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ አፅንቶታል፡፡

አመልካች ጥር 12 ቀን 2000 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ የሟች አቶ ፅጌ ገላዬ ሚስትና ክርክር የተነሳበት ቤት ግማሽ የኑዛዜ ወራሽ መሆኔ ተረጋግጧል፡፡ ይኸ ከሆነ የቤቱ ግማሽ ዋጋ ሊከፈለኝ የሚገባው ቤቱ በአሁኑ ጊዜ በሚያወጣው የገበያ ዋጋ መሆን ሲገባው በመሀንዲስ ግምት ተቀብዬ ቤቱን እንዲለቅ መወሰኑ ተገቢ አይደለም፡፡ አመልካች አዛውንት በመሆኔ የቤቱን ግማሽ ዋጋ ከፍዬ ቤቱን እንዳስቀር ወይም በገበያ ዋጋ ተገምቶ ግማሹ እንዲከፈለኝ ማድረግ ይኸም ካልሆነ ቤቱ ተሽጦ የሚያወጣውን ዋጋ እኩል መካፈል ሲገባኝ በውርስ የተገኘ የጋራ ባለሀብትነት መርህን በሚፃረር መንገድ በመሀንዲስ ግምት ግማሽ ዋጋ ተቀብዬ ቤቱን እንዲለቀቅ መወሰኑ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል፡፡

ተጠሪ በበኩሉ አመልካች ግማሽ ዋጋ ከፍዬ ቤቱን እንዳስቀር በማለት የሚያቀርቡት ክርክር የህግ መሠረት የለውም፡፡ የቤቱ ባለንብረት ባደረጉት ኑዛዜ አመልካች በቤቱ ላይ የሚኖራቸው መብት በግልፅ የተወሰነና የተቀመጠ ነው፡፡ ኑዛዜው ቤቱ ተሽጦ እኩል ይካፈሉ ስለማይል በዚህ በኩል ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡ የቤቱ ዋጋ እንዲገመት የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ ተገምቶ ቀርቧል፡፡ ኑዛዜው የቤቱን ግምት ግማሽ ወስደው ቤቱን ለተጠሪ እና ለእህቴ እንዲለቁ የሚል ነው፡፡ ኑዛዜው የቤቱን የገበያ ዋጋ ግምት ግማሽ ያግኙ አይልም፡፡ ቤቱ ሁለት ጊዜ በባለሙያ የተገመተ በመሆኑ በሥር ፍርድ ቤት በኩል የተፈፀመ የህግ ስህተት የለም በማለት በፅሑፍ መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በበኩላቸው ሟች የቤቱን ዋጋ ግማሽ እንድወስድ ኑዛዜ ያደረገው ቤቱ የተሠራበትን ማቴሪያል የእርጅና እና ሌሎች የመሀንዲስ ቅንስናሽ ተደርጎለት የሚያወጣውን ግምት እንዲወስድ በማሰብ ሣይሆን ቤቱ ቢሸጥ የማያወጣውን ዋጋ ግምት ግማሹን እንዲወስድ በማሰብ ስለሆነ የተጠሪ ክርክር ተቀባይነት የለውም የሚል የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር አመልካችና ተጠሪ ያደረጉት የፅሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ሟች የቤቱን ግምት ግማሽ ዋጋ እንድትወስድ ቤቱ ለተጠሪና ለእህቱ እንዲቀር የተናዘዘ በመሆኑ አመልካች የቤቱን ግምት ክፍያ ቤቱን እኔ እንዳስቀር በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ ድጋፍና ተቀባይነት የለውም፡፡

ሟች “የቤቱን ግምት ግማሽ ዋጋ” በማለት ያደረገው ኑዛዜ መተርጎም ያለበት ቤቱን ጣራና ግድግዳ የተሠራበት ዋጋ በመሀንዲስ ተገምቶ ግማሹን ዋጋ አመልካች እንድትወስድ በሚል መንገድ መሆን የለበትም፡፡ ይህ አባባል መተርጎም ያለበት በፍታብሔር ህግ ቁጥር 911 ንዑስ ቁጥር 1 መሠረት ንብረቱ ሟች ሲሞት በሚያወጣው የገበያ ዋጋ መሠረት ተገምቶ ግማሹን አመልካች እንድትወስድ ያደረገው ኑዛዜ እንደሆነ ትርጉም ሊሰጠው የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

የማይንቀሣቀሥ ንብረት የመሀንዲስ ግምትና ንብረቱ በወቅቱ ገበያ የሚያወጣው የገበያ ዋጋ ግምት የተለያዩ መሆናቸውን የሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠ በመሆኑ ተጠሪ ንብረቱ በወቅቱ ገበያ የሚያወጣው ዋጋ በባለሙያ ተገምቶ ቀርቧል በማለት ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች በኑዛዜ ወራሽ መሆን ያገኙት ቤት በወቅቱ ገበያ የሚያወጣው ዋጋ ሣይጣራ በባለሙያ ግምት ግማሹን በመውሰድ ቤቱን ለተጠሪ እንዲያስረክቡ በማለት የሰጡት ውሣኔ መሠታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ ተሽሯል፡፡
  2. አመልካች ቤቱ አሁን ባለው የገበያ የሚያወጣውን ዋጋ ግምት ግማሹን ከተጠሪ በመቀበል ቤቱን ለተጠሪ ያስረክቡ ብለናል፡፡
  3. ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ

ይኸ ፍርድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሙሉ ድምፅ ተሰጠ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

 

 

1 Comment

  1. ashenafi says:

    this is god information for me thank you

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s