የስራ መሪ -የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ


የስራ መሪ የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ ክፍል አንድ

የስራ መሪ ትርጉም

ለስራ መሪ የተሰጠው ትርጓሜ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/1996 አንቀጽ 2(ሐ) ላይ የተመለከተ ሲሆን በሰበር በተሰጡ ውሳኔዎች የድንጋጌውን ይዘት እንደወረደ ከመድገም ባለፈ ድንጋጌውን ለመረዳት የሚያስችል ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ትንተና አልተሰጠም ለምሳሌ በሰ.መ.ቁ. 42901 (አመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም) በአንቀጽ 2(ሐ) ላይ የተመለከተው የስራ መሪ ትርጉም እንደወረደ ከመደገሙ በስተቀር በድንጋጌው ይዘት የታከለበት ማብራሪያ ሆነ ትንተና የለም

በአዋጁ አንቀጽ 2(ሐ) ላይ የስራ መሪ ትርጉም እንደሚከተለው ተቀምጧል
“የሥራ መሪ የሚባለው በሕግ ወይም እንደ ድርጅቱ የሥራ ፀባይ በአሠሪው በተሠጠው ውክልና ሥልጣን መሠረት የሥራ አመራር ፖሊሲዎችን የማውጣትና የማስፈፀም ከዚህ በተጨማሪ ወይም እነዚህኑ ሳይጨምር ሠራተኛን መቅጠር ማዛወር የማገድ የማሰናበት የመመደበ ወይም የሥነ ሥርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውንና የሚወስን ግለሰብ ነው ፡፡”

ከዚህ ጠቅለል ካለው አገላለጽ በተጨማሪ ድንጋጌው የተወሰኑ ተግባራት የሚያከናውኑ ሰራተኞችን በስራ መሪነት ይፈርጃቸዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ከላይ የተመለከቱትን የስራ አመራር ጉዳዮች አስመልክቶ የአሰሪውን ጥቅም ለመጠበቅ አሰሪው ሊወስደው ስለሚገባው እርምጃ በራሱ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ባለሙያ የስራ ሐላፊም ጭምር እንደ ስራ መሪ ይቆጠራል፡፡
የስራ መሪ ትርጓሜ ላይ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 494/1998 ተሻሽሎ በአዲስ የተተካ ቢሆንም በይዘት ረገድ ግን የህግ አገልግሎት ሐላፊ እንደ ስራ መሪ በተጨማሪነት ከመካተቱ በቀር የተለወጠ ነገር የለም

የማስረዳት ግዴታ እና የማስረጃ ጫና

የስራ ክርክር ያቀረበ ሰራተኛ የስራ መሪ ነው የሚል መቃወሚያ በአሰሪው በኩል የተነሳበት እንደሆነ ይህንን የማስረዳት የማስረጃ ጫናው በአሰሪው ላይ ያርፋል ፡፡ (አመልካች ርሆቦት ሆሊሺየር ኃ/የተ/የግ/ማ እና ተጠሪ አቶ አማረ አድማሱ ሰ/መ/ቁ 38811 የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም)
ሰበር እዚህ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ የቻለው የሰራተኛው የስራ ሀላፊነት የስራ መሪ የሚያደርገው ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በማስረጃ የሚረጋገጥ የፍሬ ነገር ጉዳይ ነው በሚል ምክንያት ነው፡፡ የሰበር ችሎት ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው በማለት አመልካች ያቀረበውን ቅሬታ ውድቅ ሲያደርግ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡
“የተጠሪ የስራ ሃላፊነት የስራ መሪ የሚያሠኛቸው ነው ወይስ አይደለም የሚለው በማስረጃ የሚረጋገጥ የፍሬ ነገር ጉዳይ እንደመሆኑ አመልካች ይህንኑ የማስረዳት ሸክም አለበት ነገር ግን ከመዝገቡ እንደተረዳነው በስር ፍ/ቤት አመልካች ይህንን ለማስረዳት ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ በመሆኑም በዚህ በኩል ያቀረበው የሠበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡”

ማስረዳት ስለሚቻልባቸው መንገዶች

የስራ መሪ ነው የሚል መቃወሚያ በአሰሪው በኩል ሲቀርብ ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ የራሱ የአሰሪው ስለመሆኑ በሰ/መ/ቁ 38811 ላይ በሰበር አቋም የተወሰደበት ነጥብ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይነት የሚነሳው ጥያቄ አሰሪው ከሳሽ ሰራተኛ ሳይሆን የስራ መሪ እንደሆነ ማስረዳት የሚችልባቸው መንገዶች ምንድናቸው? የሚል ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ለሰበር ከቀረቡት ጉዳዮች ለመረዳት እንደሚቻለው በአሰሪው በኩል ሁለት የማስረጃ መንገዶች በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ሲሆን በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝተው ለሰበር ውሳኔዎች መሰረት በመሆን ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡እነሱም፡-

ሀ. የስራ ኃላፊነት መዘርዘር (ሰ/መ/ቁ 36894፤ 42901)
ለ. የህብረት ስምምነት (ሰ/መ/ቁ 39658፤ 38894፤ 42901)

ሀ. የስራ ኃላፊነት መዘርዘር

የስራ ኃላፊነት መዘርዝር ሰራተኛው በእርግጥ ሲሰራ የነበረው ስራ እና በእርግጥ የነበረው ስልጣን መሰረት የሚያደርግ ሳይሆን በድርጅቱ መዋቅር ለየመደብ ክፍሉ የስራ ኃላፊነት የተቀመጠ የስራ ተግባራት ዝርዝር ነው፡፡ ስለሆነም በወረቀት የተቀመጠውንና በተግባር ያለውን እውነታ የሚያስታርቅ አይደለም፡፡

በአመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ አቶ ሙላት ታረቀኝ (የሰ.መ.ቁ. 36894 ታህሳስ 30 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በነበረው ክርክር የሰበር ችሎት ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በዋናነት መሰረት ያደረገው የተጠሪን የስራ ሃላፊነት ዝርዝር ነበር፡፡

ከሰበር ውሳኔው ለመረዳት እንደሚቻለው ተጠሪ ተመድበው ይሰሩበት የነበረው የሂሳብ ክፍል ረዳት ኃላፊ የሥራ ቦታ ላይ ሲሆን በቦታው ላይ የተመደቡትም በቋሚነት ሳይሆን በተጠባባቂነት (በአመልካች አገላለጽ ደግሞ በጊዜያዊነት) ነው፡፡ የሰበር ችሎት የተጠሪን የሥራ መደብ የሥራ መዘርዝርን በተመለከተ እንዳለው የተጠሪ የስራ ኃላፊነት የክፍሉን እንቅስቃሴዎች የመቆጣጠር፤ የዕለት ከዕለት የሒሳብ ቁልፎችን መያዝና የሒሳብ ከፋዮችን የዕለት ከዕለት የሥራ ምደባ ፕሮግራም ማዘጋጀትን ያጠቃልላል፡፡

ከዚሁ በመነሳት ተጠሪ የስራ ሃላፊነታቸው የስራ መሪ እንደሚያደርጋቸው የሰበር ችሎቱ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው የፌደራል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው በማለት በአመልካች የቀረበውን መቃወሚያ በመቀበል የተጠሪን የስራ ክርክር ክስ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ የሻረው ሲሆን ለውሳኔው በዋናነት መሰረት ያደረገው ግን የሥራ መደቡ የሥራ መዘርዝር ተጠሪን የስራ መሪ አያደርጋቸውም በማለት ሳይሆን ተጠሪ ምክትል የግምጃ ቤት ሓላፊ በመሆን ያገለገሉት በጊዜአዊነት በመሆኑ በቋሚነት ተመድበው ያልሰሩበት የሥራ መደብ የሥራ መሪ ሊያሰኛቸው አይችልም የሚል ምክንያት በመስጠት ነው፡፡

የሰበር ችሎት የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሲሽር በመዝገቡ ላይ ከተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች አንጻር ፍርድ ቤቱ የፈጸመውን መሰረታዊ የህግ ግድፈት ከመመርመር አልፎ ያለስልጣኑ ተጨማሪ ፍሬ ነገሮችን አጣርቷል፡፡ ተጣርቷል የተባለው ፍሬ ነገር በሰበር ደረጃ ማስረጃ የቀረበበት ሳይሆን በችሎቱ ፊት የተደረገውን የቃል ክርክር መሰረት ያደረገ ነው፡፡

የሰበር ችሎት የተጠሪን የስራ መዘርዝር በማየት የስራ መሪ ናቸው ካለ በኋላ በቀጣይነት የመረመረው ጭብጥ ተጠሪ በሥራ መደቡ ይሰራ የነበረው በቋሚነት ሳይሆን በተጠባባቂነት መሆኑ ተጠሪን ሰራተኛ ያሰኘዋል ወይስ አያሰኘውም? የሚል ሲሆን ይህን ነጥብ በተመለከተም “ተጠሪ በተጠባባቂነት ተመድበው ሲሰሩ ለቦታው የሚገባውን ጥቅማጥቅም የሚያገኙ እንደነበርና ለሥራው ሙሉ ሃላፊነት ወስደው ይሰሩ እንደነበር” በስርና በሰበር ችሎቱ የተደረገው ክርክር እንደሚያሳይ ችሎቱ በውሳኔው ላይ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ፍሬ ነገር በመነሳትም ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሰበር በታየ ሌላ ክርክር (አመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ የሰ.መ.ቁ 42901 ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም.) ተጠሪ የድርጅቱ የሀገር ውስጥ ዕቃ ግዥ ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን እንዲሁም በተጨማሪነት የውጪ ሀገር ዕቃ ግዥ ዋና ክፍልና የሽያጭ ዋና ክፍልን የሚያካትተውን የንግድ መምሪያ ኃላፊነትን ደርበው ይሠሩ ነበር፡፡

የሰበር ችሎ በቀጣይነት የሥራ መደቡ ዋና ተግባራት ምንድናቸው? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ጉዳዩን የመረመረ ሲሆን የተጠሪን የሥራ መዘርዝር /job description/ በመጥቀስ የሥራ መደቡ በአጠቃላይ በድርጅቱ መመሪያ መሠረት ማስተባበር፣ መምራት፣ ማደራጀት እና መቆጣጣር እንዲሁም ዕቅድና በጀት ዝግጅት ላይ መሳተፍ እንደሚያጠቃልል በውሳኔው ላይ አመልክቷል፡፡

በመቀጠለም “ተጠሪ ሥራን የማቀድ፣ የመምራት፣ የመቆጣጠር፣ የማደራጀትና የማስተባበር ተግባራትን የሚያከናውኑ መሆኑን ከክርክሩም ሆነ ከቀረቡ ሰነዶች መረዳት” እንደተቻለ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
ከዚህ በመነሳትም “የተጠሪ የሥራ ተግባር በፍሬ ነገር ረገድ የተረጋገጠው የድርጅቱን ዋና ክፍል ሥራ በኃላፊነት መምራት፣ ማደራጀት መቆጣጠርና ማስተባበር ከመሆኑ አንፃር በሕጉ ትርጉም ከተሠጠው የሥራ ዘርፍ የሚመደቡ በመሆናቸው የሥራ መሪ ናቸው እንጅ ሠራተኛ አይደሉም፡፡” የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተጠሪ የስራ መሪ አለመሆናቸውን ለማሳየት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቦርድም የማናጅመንት አባላት ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ እሳቸውን እንደማይሸፍን በመጥቀስ የማናጅመንት አባል አለመሆናቸው ሰራተኛ እንደሚያደርጋቸው ለችሎቱ ክርክራቸውን ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም በማናጅመንት አባልና በስራ መሪ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ሳያመለክት ክርክራቸውን ለጉዳዩ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎባቸዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ ሰበር ትንተና የሰጠው በሚከተለው መልኩ ነበር፡፡

“የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቦርድም የማናጅመንት አባላት ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ እኔን አይጨምርም በማለት ከተጠሪ የቀረበውን ክርክር በተመለከተ መመሪያው ለቦርድና ማናጅመንት አባላት ሊከፈል የሚገባውን ክፍያ አስመልክቶ የወጣ የአፈፃፀም መመሪያ እንጅ ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚ ስለማይሆን ለክርክሩ አግባብነት የሌለው ነው፡፡”

ለ. የህብረት ስምምነት

የህብረት ስምምነት በአሰሪ በኩል የስራ መሪን ለማስረዳት የሚቀርብ ሌላው የማስረጃ መንገደ ሲሆን በሰበር በኩልም ያለአንዳች ትችት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

በሰ.መ.ቁ.36894 እና ሰ.መ.ቁ.42901 በሰበር በተሱጡት ውሳኔዎች ላይ ምንም እንኳን የስራ ኃላፊነት መዘርዝር የስራ መሪን ለማስረዳት በሰበር በኩል ተቀባ ይነት ቢያገኝም ብቻውን የቆመ ምክንያት ግን አልነበረውም፡፡ በሁለቱም መዝገቦች ላይ የሰራተኛው የስራ መዘርዘር ከተጠቀሰና ከተለየ በኃላ ‘የስራ መሪ ነው’ የሚል መደምደሚያ ላይ ሲደረስ የኅብረት ስምምነትም እንደማጠናከሪያነት ተጠቅሷል ስለሆነም በሁለቱም መዝገቦች የስራ መዘርዝር ባልቀረበበት ሁኔታ አንድ የስራ ክፍል በህብረት ስምምነት በስራ መሪነት ስለተፈረጀ ብቻ በዚያ የስራ ክፍል ላይ ተመድቦ የሚሰራ ግለሰብ እንደ ስራ መሪ አልተቆጠረም፡፡

ሰራተኛው የሕብረት ስምምነቱ ሰራተኛ ሳይሆን የስራ መሪ የሚያደርገው ቢሆንም የሰበር ችሎት በሰ.መ.ቁ.36894 እና ሰ.መ.ቁ.42901 ለውሳኔው በዋናነት መሰረት ያደረገው ግን የስራ መዘርዘሩን ነው፡፡
ይሁን እንጂ በአመልካች የሸዋ ጥጥ ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ታከለ ቀፀላ (የሰ.መ.ቁ 39658 ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በነበረው ክርክር ምንም አይነት የስራ መዘርዘር ሳይቀርብ የስራ መደቡ በህብረት ስምምነት ላይ መጠቀሱን መሰረት በማድረግ ብቻ ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ከውሳኔው ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት ክስ ሲያቀርቡ የፈረቃ ምርት ሀላፊ መሆናቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ የሰበር ችሎቱ ከዚህ በመነሳት “ተጠሪ በክሳቸው የገለፁት እና የተመደቡበት የኃላፊነት ቦታ በአመልካችና በአመልካች ድርጅት ያሉ ሠራተኞች ባቋቋሙት የሠራተኛ ማህበር ድርድር ባፀደቀው ሶስተኛው የህብረት ስምምነት በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 6 /ሐ/ የሥራ መሪ መሆናቸው” በግልፅ እንደተደነገገ በመጠቆም የህብረት ስምምነቱን ይዘት ምን እንደሆነ በውሳኔው ላይ ሳያሰፍር ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው የሚል አቋም ላይ ደርሷል፡፡

የስር ፍርድ ቤቶች የሰጧቸውን ውሳኔዎችንም እንደሚከተለው ተችቷል፡፡
“ተጠሪ የሥራ መሪ መሆናቸው አመልካችና የሠራተኛ ማህበሩ ባደረጉት ድርድር በፀደቀው ሶስተኛው የሕብረት ስምምነት በግልፅ በተደነገገበት ሁኔታ የበታች ፍርድ ቤቶች ህብረት ስምምነቱን ድንጋጌ ወደ ጎን በመተው ተጠሪ ሠራተኛ ነው በማለት የደረሱበት መደምደሚያና ለተጠሪ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የሰጡት ውሣኔ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/2/ሐ እንደተሻሻለ የሚተላለፍ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡”
አንድ ተቀጣሪ የስራ መሪ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ በበአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/2/ሐ እንደተሻሻለ በተቀመጠው መለኪያ ተመዝኖ በፍርድ ቤቶች ፍርድ ማግኘት ያለበት ነጥብ እንጂ ሰራተኛውና አሰሪው ተደራድረው በህብረት ስምምነት የሚወስኑት የስራ ሁኔታ ስላለመሆኑ ከድንጋጌው ምንባብ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግት አይደለም፡፡ የሰበር ችሎት ይህን ነጥብ መዘንጋቱ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም የህብረት ስምምነት ከተዋዋይ ወገኖች በዘለለ በድርድሩ ላይ ምንም ተጽዕኖ ሆነ ሚና ባልነበራቸው ግለሰቦች ላይ እንዴት ተፈጻሚነት ሊያገኝ እንደቻለ ሌላው በሰበር ያልተመለሰ ጥያቄ ነው ችሎቱ ጥያቄውን መጀመሪያውኑ ባለማንሳቱ ውሳኔውም የተሳሳተ ሊሆን ችሏል፡፡

2 Comments

  1. zeleke says:

    የሥራ መሪን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄን መመለስ የሚችል ወትነት ያለዉ ህግ ቢኖር ይመረጣል።

  2. Endashaw Beyene says:

    Nice!

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s