የስራ መሪ – የፍርድ ቤት ስልጣን (የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ ክፍል ሁለት)


የስራ መሪ – የፍርድ ቤት ስልጣን

ላይ ላዩን ሲታይ የስራ መሪ የሚያቀርበውን ክስ ለማየት የዳኝነት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት መለየት ቀላል ቢመስልም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 የፍርድ ቤቶችን ስልጣን በተመለከተ እልባት ሳይሰጥ በቸልታ ካለፈው መሰረታዊ ጥያቄ አንጻር ሲታይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት ምክንያትን መሰረት ያደረገ ጥልቅ ፍተሻ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቁመናል፡፡

ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 ክፍል ሁለት ድንጋጌዎች በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አዋጁ የአሰሪና ሰራተኛ ፍርድ ቤቶችን አያቋቁምም፡፡ የአዋጁ ክፍል ሁለት ርዕስ የአማርኛ ምንባብ ‘ስለ ስራ ክርክር ችሎቶች’ በሚል የተቀመጠ ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ የእንግሊዝኛው ቅጂ Labour Courts የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል፡፡ በይዘትም ሆነ በተፈጻሚነት ወሰን ረገድ የስራ ክርክር ችሎቶች እና Labour Courts እጅግ የተራራቁ ናቸው፡፡ Labour Courts በህጋዊ ሰውነት፤ በአደረጃጀት በሰራተኛ ቅጥርና አስተዳደር ብሎም በበጀት አስተዳደር ከመደበኛው ፍርድ ቤት በተለየ መንገድ በራሳቸው የሚመሩና የራሳቸው መዋቅርና ፕሬዚደንት ያላቸው በልዩ ህግ የሚቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ በአንጻሩ የስራ ክርክር ችሎቶች በመደበኛው ፍርድ ስር እንደ አንድ ልዩ ችሎት የተዋቀሩ ከመሆናቸውም ባሻገር በውስጥ አደረጃጀት ሆነ በመዋቅር ደረጃ ራሳቸውን ችለው የቆሙ አሊያም የተቋቋሙ የዳኝነት አካላት አይደሉም፡፡

የአዋጁ ክፍል ሁለት የአማርኛ ሆነ የእንግሊዝኛ ዝርዝር ድንጋጌዎች ስለ ስራ ክርክር ችሎቶች የሚያወሩ እንደመሆናቸው በዚህ ረገድ ሊፈጠር የሚችል ውዥንብር አይኖርም፡፡ ሆኖም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የስራ ክርክር ችሎቶች እንጂ የስራ ክርክር ፍርድ ቤቶች እንዳልተቋቋሙ ልብ ልንል ይገባል፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 137 በሁሉም ክልሎች በሶስት ደረጃ የተዋቀሩ የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ ይገልጻል፡፡ እነዚህም፤

ሀ. የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

ለ. ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት ይግባኝ የሚሰማ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

ሐ. የማዕከላዊ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

አዋጁ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ ስለሚታዩ ወይም ሊታዩ ስለሚገባቸው  የስራ ክርክሮች በተመለከተ በዝምታ ብቻ ሳይሆን በቸልታ ማለፍን መርጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ሰለሚፈጠሩ የስራ ክርክሮችም በየትኛው ፍርድ ቤት ወይም ችሎት እንደሚታዩ አዋጁ በቂ ምላሽ አይሰጥም፡፡

የክልል የመጀመሪያ ደረጅ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት የዳኝነት ስልጣን በየክልሉ በተመዘገቡ የክልል የንግድ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር ብቻ ይሁን በፌደራል መንግስት በተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር ጭምር ስለመሆኑ ከአዋጁ ፍንጭ እንኳን ማግኘት ያዳግታል፡፡ በፌደራልና በክልል የስራ ክርክር መካከል ያለው ክፍፍል በድሬዳዋና በአዲስ አበባም የሚከሰት ነው፡፡

በሁለቱም መስተዳደሮች ውስጥ በፌደራልና በየመስተዳደሩ ተለይተው በተመዘገቡ አሰሪዎችና ሰራተኞች ራሳቸውን የቻሉ የስራ ክርክሮች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች እነዚህን የስራ ክርክሮች ያለልዩነት ማየት ይችላሉ ቢባል እንኳን አዋጁ የስራ ክርክር ችሎቶችን ያቋቋመው በክልል ደረጃ ብቻ እንደመሆኑ አሰሪው፤ሰራተኛው ብሎም የስራ መሪ የሚያቀርቡት ክስ ለስራ ክርክር ችሎት ቀርቧል? አልቀረበም? በሚል ጭብጥ ተይዞ የፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውሳኔ መስጠት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ ሊሆን አይችልም፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 20 እና 23 በፌደራል በመጀመሪያ፤ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፍትሐ ብሔር፤ የወንጀል እና የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ ይደነግጋል፡፡ የስራ ክርክር (Labour Dispute) ሲባል ከአዋጅ ቁጥር 377/96 ባለፈ ማናቸውንም ከአሰሪና ሰራተና ግንኙነት የሚመነጩ የስራ ክርክሮች ያቅፋል፡፡

በሰበር ችሎት ያለው አቋም

ክሱን ያቀረበው ከሳሽ የስራ መሪ መሆኑ ከተረጋገጠ በጉዳዩ ላይ የዳኝነት ስልጣን ያለውን ፍርድ ቤትና ተፈጻሚ የሚሆነውን ህግ መለየት በቀጣይነት እልባት ማግኘት ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ክፍል ሁለት የዳኝነት ስልጣን በተመለከተ የሰበር ችሎት በሚከተለው መልኩ አስገዳጅነት ያላቸውን ውሳኔዎች ሰጥቷል፡፡

በሰበር ከተሰጡት ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ሰራተኛ ነኝ በሚል እምነት ክሱን ለስራ ክርክር ችሎት ያቀረበ ከሳሽ በአሰሪው የሚነሳን መቃወሚያ መሰረት በማድረግ ችሎቱ ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ የደረሰ እንደሆነ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም ብሎ መዝገቡን መዝጋት ይኖርበታል፡፡ ከሳሽ በስር ፍርድ ቤት ሰራተኛ ተብሎ በይግባኝ ውሳኔው ተሸሮ የስራ መሪ ነው የሚል አቋም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተያዘ እንደሆነም በቀጣይነት መዝገቡን መዝጋት እንጂ ለስራ መሪ ተፈጻሚ በሚሆነው ህግ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም፡፡

በአመልካች የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ እና ተጠሪ አቶ ከበደ ወንድሙ (የሰ.መ.ቁ. 41321 የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በሰበር በቀረበ ክርክር ላይ ተጠሪው በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ  ለረጅም ዓመታት የምርት ጥራት ቁጥጥርና አገልግሎት ኃላፊ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ፀሐፊ ሆኖ ሲሰራ ለ19 ዓመታት ካገለገለበት ድርጅት የሥራ ውሉን  አመልካች (በስር ፍርድ ቤት ተከሳሽ) ከሕግ ውጪ ያቋረጠው በመሆኑ የአንድ ወር ከ14 ቀን ደመወዝ ተከፍሎት ወደሥራ እንዲመለስ ውሳኔ እንዲሰጠው ዳኝነት የጠየቀ ሲሆን አመልካቹም “ከሣሽ የሥራ መሪ እንጅ ሠራተኛ አይደለም፤ ጉዳዩ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሊታይ አይገባም” በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና ስንብቱም በሥራ መመሪያዎች መሠረት ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆኑና እምቢተኛ በመሆኑ በአግባቡ ነው በማለት በአማራጭ ተከራክሯል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተጠሪ የሥራ መሪ አይደለም በማለትና የመቃወሚያውን ክርክር ውድቅ በማድረግ የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ስለሆነ የ1 ወር ከ14 ቀን ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራ ይመለስ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪው የሥራ መሪ ነው ነገር ግን ስንብቱ ከሥራ መሪዎች መተዳዳሪያ ደንብ አንቀጽ 1ዐ.5.2 ድንጋጌ ውጪ ነው በማለት ውሉ ተቋርጦ ለቆየበት ጊዜ ያልተከፈለው ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራ ይመለስ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የስር ፍርድ ቤቶች በሰጡት ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት አመልካች ባቀረበው የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የሥራ መሪ ከመሆኑ አንፃር የሥራ ክርክር ችሎት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የላቸውም ተብሎ እንዲሻርለት መከራከሪያውን አቅርቧል፡፡ የሰበር ችሎቱም በአመልካች የቀረበውን መከራከሪያ በመቀበል ይግባኙን የሰማው ፍርድ ቤት ተጠሪ የስራ መሪ መሆኑን ካረጋገጠ የዳኝነት ስልጣን እንደሌለው ገልጾ መዝገቡን መዝጋት እንደነበረበት ካተተ በኋላ ውሳኔውን ሽሮታል፡፡

በሰበር ውሳኔው ላይ በተሰጠው ሀተታ ላይ እንደተመለከተው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተጠሪ“የሥራ መሪ መሆኑን ካረጋገጠና ውሣኔ ከሰጠ ወደ ሌላ ጭብጥ መሄድ የሚጠበቅበት አልነበረም፡፡ የሥራ መሪ መሆኑ ከተረጋገጠና ውሣኔ ከተሰጠ የሥራ መሪዎች ጉዳይ ዳኝነት ሊታይ የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት በሥራ ክርክር ሂደትና ችሎት ሣይሆን በፍትሐብሔር ሕግ በተመለከቱ ሥርዓቶች መሠረት ነው፡፡”

በተመሳሳይ መልኩ በአመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ (የሰ.መ.ቁ. 42901) ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም በሰበር ታይቶ በተሰጠ ውሳኔ ጉዳዩ በመጀመሪያ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ የስራ መሪ ነች በሚል በአመልካች የቀረበለትን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏት ወደ ስራ እንድትመለስ ውሳኔ ሰጥቶ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ውሳኔውን በማጽናቱ በአመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎት ተጠሪ የስራ መሪ ነች የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረሱ ተጠሪ በሥራ ክርክር ችሎት ክስ ለማቅረብም ሆነ ክርክር ለማካሄድና ዳኝነት ለማግኘት የምትችልበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን በማተት የመጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍ/ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

የሰበር ችሎት ይህን አቋሙን ወጥነት ባለው መልኩ ተፈጻሚ በማድረግ በአመልካች የሸዋ ጥጥ ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ታከለ ቀፀላ (የሰ.መ.ቁ.39658) መካከል በነበረው ክርክር የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በሕብረት ስምምነት የስራ መሪ ስለተደረጉ የስራ መሪ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ በዚሁ መሰረት የስር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለማየት ስልጣን እንደማይኖራቸው በመግለጽ የሰጧቸውን ውሳኔዎች ሽሯቸዋል፡፡

በአመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ አቶ ሙሊት ታረቀኝ (የሰ.መ.ቁ.36894) በነበረው ክርክርም ታህሳስ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

መሰረታዊው ጥያቄ

ከለይ በሰበር ከተሰጡት ውሳኔዎች የስራ ክርክር ችሎት ትርጉምን በተመለከተ መሰረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ በክልል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎቶች የተቋቋሙት በአዋጅ ቁጥር 377/96 እንደመሆኑ እነዚህ ችሎቶች በአዋጁ መሰረት በሰራተኛና በአሰሪ ወይም በማህበሮቻቸው ለሚቀርቡ ክሶች ዳኝነት የሚሰጡ የፍርድ አካለት እንደሆኑ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል ስለሆነም በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተ የዳኝነት ስልጣን የላቸውም ወደሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል ይሁን እንጂ በዚህ ድምዳሜ እርግጠኛ ለመሆን የየክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በቀጥታ የስራ ክርክር ችሎቶችን አለማቋቋማቸው ማመሳከር ያስፈልጋል

በክልል ደረጃ የክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የስራ ክርክር ችሎቶን አቋቁሞ እንደሆነ በስራ መሪ የሚቀርብ ክስ የስራ ክርክር ሳይሆን የፍትሀ ብሔር እንደሆነ መውሰዱ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው ምክንያቱም የስራ ክርክር ተብሎ የስልጣኑ ወሰን በግልጽ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ማዕቀፍ ውስጥ እስካልተገደበ ድረስ የስራ ክርክርን ከአዋጅ 377/96 ጋር ብቻ ማቆራኘቱ ከአዋጅ ቁጥር 377/96 ውጪ አሰሪና ሰራተኛ የሚባል ነገር የለም የማለት ያህል ነው ከዚህ ሓሳብ ጋር ለመስማማትም ሆነ ላለመስማማት የስራ ክርክር ለሚለው ቃል ተገቢውን ፍቺ መስጠት ይኖርብናል፡፡

ፍተሻችን የበለጠ ግልጽ እንዲሆን በፌደራል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎት የሚለው ቃል ምን እንደሚወክል እንዳስሳለን ከላይ ግልጽ ለማድረግ እንደሞከርኩት አዋጅ ቁጥር 377/96 በፌደራል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎቶችን አያቋቁምም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በፌደራል በመጀመሪያ፤ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ የተደነገገው በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 20 እና 23 ላይ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ በአዋጁ የሚቋቋሙት የስራ ክርክር ችሎቶች የሚያስተናግዷቸው ጉዳዮች ከአዋጅ 377/96 የሚመነጩትን ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ ሆነ በተዘዋዋሪ የተመለከተ ነገር የለም፡፡ የስራ ክርክር ሲባልም ማናቸውም የስራ ውልን መሰረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮችን በሙሉ የሚያጠቃልል እንጂ በአዋጅ 377/96 መሰረት ከተደረጉ የስራ ውሎች የሚመነጩ ክርክሮች እንደሆነ ተደርጎ አለአግባብ ጠባብ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

የስራ መሪ ከአዋጅ 377/96 ተፈጻሚነት ወሰን ውጪ እንዲሆን የተደረገው ከአሰሪው ጋር የስራ ውል ስለሌለው ሳይሆን በሰራተኞችና መካከል ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ ከሚል የፖሊሲ አቋም የተነሳ ነው ስለሆነም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ.377/96 በስራ መሪ ላይ ተፈጻሚነት የሌለው መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 የተቋቋሙት የስራ ክርክር ችለቶች በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶችን ለማየት የዳኝነት ስልጣን ያጣሉ ማለት አይደለም፡፡

በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶች ላይ በተግባር ተፈጻሚ እየተደረጉ ያሉት ድንጋጌዎች በፍትሐ ብሔር ህጉ ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም በዋነኛነት በስራ በውል ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነትን የሚገዙ ድንጋጌዎች ናቸው ከዚህ ህግ የሚመነጩ ክርክሮችም በባሕሪያቸው የስራ ክርክሮች እንጂ የፍትሐ ብሔር በሚል ድፍን ያለ ፍረጃ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክር ችሎቶችን የዳኝነት ስልጣን የሚያሳጣ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡

በፍትሐ ብሄር ህጉ ውስጥ የተቀመጡት የአሰሪና ሰራተኛ ግኑኘትን የሚመሩት ድንጋጌዎቸ “የፍትሐ ብሄር ህግ” በሚለው ስር በመገኘታቸው ብቻ በስራ መሪ የሚቀርብ ክስም በፍትሐ ብሄር ችሎት መታየት እንዳለበት የፍትሐ ብሄር ክርክር አድርጎ መውሰዱ መሰረታዊውን ጥያቄ መሸሽ እንጂ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አይደለም የአንድ ክርክር ዓይነት ሊወሰን የሚገባው በይዘቱ እንጂ በሚገኝበት መጽሐፍ መሰረት አይደለም፡፡

ስለሆነም ከሳሽ ሰራተኛ ነኝ በሚል እምነት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ በሚደርስበት ጊዜ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96ን ተፈጻሚነት በማስቀረት ተፈጻሚነት ባለው ሌላ ህግ ውሳኔ መስጠት እንጂ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት የቀረበለትን ክስ ወዲያውኑ ሊዘጋው አይገባም፡፡

ከሳሽ በስር ፍርድ ቤት ሰራተኛ ተብሎ በይግባኝ ውሳኔው ተሸሮ የስራ መሪ ነው የሚል አቋም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተያዘ እንደሆነም በቀጣይነት ለስራ መሪ ተፈጻሚ በሚሆነው ህግ ውሳኔ መስጠት እነጂ መዝገቡን ሊዘጋው አይገባም፡፡

ስለሆነም ከላይ በቀረበው የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ ላይ ክሱ ከመጀመሪያውኑ ለፌደራል ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት የቀረበ በሚሆንበት ጊዜ ከሳሽ የስራ መሪ ሆነም አልሆነም ችሎቱ የዳኝነት ስልጣን የሚያጣበት የህግ መሰረት የለም፡፡ የፌደራል የስራ ክርክር ችሎቶች የተቋቋሙት በአዋጅ ቁጥር 25/1988 እንደመሆኑ የስልጣናቸው ወሰንም በስራ መሪ ጭምር የሚቀርብን ማናቸውንም የስራ ክርክሮች እንጂ ከአዋጅ ቁ 377/96 በሚመነጩት የስራ ክርክሮች የተገደበ አይደለም፡፡

ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ አይደለም አቋም ከተያዘ በቀጣይነት የሚነሳው ጥያቄ ተፈጻሚ የሚሆነውን ህግ መለየት እንጂ የፍርድ ቤቱ ስልጣን አይደለም፡፡ ጉዳዩን የያዘው የፌደራል ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት ሆኖ በህግ እስከተቋቋመ ድረስ የስራ ክርክሩ መሰረት ያደረገበት ህግ የፍትሐ ብሄር የስራ ውል ድንጋጌዎች ሆነ አዋጅ ቁ 377/96 ሁለቱንም ያለ ልዩነት ተቀብሎ ዳኝነት ለመስጠት ከተቋቋመበት ህግ የመነጨ የዳኝነት ስልጣን አለው፡፡

10 Comments

 1. Bronze says:

  I think this kind of intellectual dialogue should be encouraged. Well done Bela Libeliha.

 2. siraj mehdi says:

  i like it keep it up

 3. Afework says:

  Mr. Bela Leblha, I think it presented by professional way of cogent arguments, specially the court’s jurisdiction. On the other side if the cornered body takes this point positively, it becomes a good means for delivery of justice within reasonable time to those people who look for the court.

 4. Abera Dugo says:

  where do managers go?

 5. arambana kobo says:

  it is difficult to talk on such issue in this country even if we said we are democratic people are not getting the right justice

 6. Abraham Seyoum says:

  I think it is a good observation, if you are interested please prepare panel discussion in this matter

 7. tilahun says:

  የሰበር ሰሚ ችሎትን ጉደይ ገዘዚበሀህረር የይፍርድባቸዉ እንጂ ምንም መናገር አያስፈልግም

 8. Samson Abera says:

  wow good view

 9. Tewodros Tamrat says:

  Very enkighting and well written
  Tewodros

 10. Hussein says:

  It is marvelouos work. Keep it up. Thank you!

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s