አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩ ዓ.ም የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ


                   አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩ ዓ.ም.

የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር ፪፻፹፭/፲፱፻፺፬፺ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭ ንዑስ አንቀፅ /፩/ እና /፲፩/ መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

. አጭርርዕስ
ይህ አዋጅ ‹‹የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

. ማሻሻያ
የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር ፪፻፹፭/፲፱፻፺፬ እንደሚከተለው ተሻሽሏል፣
፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፪ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ተተክቷል፣
‹‹፬/ ‹‹ባለሥልጣን›› ማለት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፤››
፪/ ከአዋጁ አንቀጽ ፪ ሥር የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፳፭/ እና /፳፮/ ተጨምረዋል፡፡
‹‹፳፭/ ‹‹የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ›› ማለት የጥሬ ገንዘብ መመዝገቢያ መሣሪያ ወይም የሽያጭ ነቁጣ መሣሪያ ነው፣
‹‹፳፮/ ‹‹አቅራቢ›› ማለት የሽያል መመዝገቢያ መሣሪያዎችን ወይም በመሣሪያው ላይ ተጭኖ አገልግሎት የሚሰጥ ሶፍት ዌርን ወይም ሁለቱንም በአንድ ላይ የሚያቀርብ ሰው ነው፡፡››
፫/ በአዋጁ አንቀጽ ፮ ውስጥ ‹‹በማንኛውም ሰው›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹በማንኛውም የተመዘገበ ሰው›› እንደዚሁም ‹‹ባለማቋረጥ ወይም በመደበኛ ሥራነት›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹‹በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፬/ ከአዋጁ አንቀጽ ፯ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ቀጥሎ የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፭/ ተጨምሯል፣
‹‹፭/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ሀ/ ተፈፃሚ የሚሆንበት ግብይት ሲከናወን እንደአስፈላጊነቱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሚወጣ መመሪያ መሠረት ታክሱ ግዢውን በሚፈፀመው አካል ተይዞ ለባለሥልጣኑ ይከፈላል፡፡››
፭/ የአዋጁ አንቀጽ ፰ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ፊደል ተራ /ሀ/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ፊደል ተራ /ሀ/ ተተክቷል፣
‹‹ሀ. ቢያንስ ሁለት ዓመት ያገለገለ የመኖሪያ ቤት ሽያጭና የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣››
፮/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፮/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንኡስ አንቀጽ /፪/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፣
፯/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፯/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፰/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፰/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፰/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ/፭/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፱/ የአዋጁ አንቀጽ ፲፮ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተተክቷል፡፡
‹‹፫. ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ያለበት ሰው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ሀ/ የተመለከተው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ባለው ወር እስከ መጨረሻ ቀን ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ለ/ የተመለከተው ጊዜ በተጠናቀቀበት ወር እስከ መጨረሻ ቀን ለምዝገባ ማመልከቻ ማቅረብና መመዝገብ አለበት፡፡››
፲/ በአዋጁ አንቀጽ ፳፪ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተተክቷል፣
‹‹፩/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፮/ እና /፯/ በሌላ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበና ታክስ የሚከፈልበት ግብይት የሚያካሂድ ሰው ደረሰኝ ወዲያውኑ መስጠት አለበት፡፡ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገበ ሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መስጠት አይችልም፡፡››
፲፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፳፪ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተሰርዞ ንዑስ አንቀጽ /፬/፣ /፭/፣ /፮/ እና /፯/ እንደ ቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ /፫/፣ /፬/፣ /፭/ እና /፮/ ሆነዋል፡፡
፲፪/ የአዋጁ አንቀጽ ፳፮ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተተክቷል፣
‹‹፩/ እያንዳንዱ የተመዘገበ ሰው፣
ሀ/ በአንድ የሂሳብ ጊዜ ውስጥ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት ቢሆንም ባይሆንም በእያንዳንዱ የሂሳብ ጊዜ ሂሳቡን ግብር ባለሥልጣኑ ዘንድ በመቅረብ ወይም በኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ዘዴ ወይም ባለሥልጣኑ ለሚወክለው የፋይናንስ ተቋም ማስታወቀ፣ እና
ለ/ ለእያንዳንዱ የሂሳብ ጊዜ የተሰጠውን የመጨረሻ ታክስ መክፈያ ጊዜ ገደብ ጠብቆ ለባለሥልጣኑ ወይም ባለሥልጣኑ ለወከለው ሰው ከገቢ ማስታወቂያው ጋር በአንድነት ታክሱን መክፈል አለበት፡፡››
፲፫/ ከአዋጁ አንቀጽ ፴ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጾች /፫/፣ /፬/ እና /፭/ ተጨምረዋል፣
‹‹፫/ በታክስ ከፋዩ የንግድ ሥራ ቦታ በመገኘት ምርመራ ለማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ማናቸውንም ሕገ ወጥ ደረሰኝ ወይም የሂሳብ ሰነድ ወይም የሂሳብ መዝገብ ካገኙ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳያስፈልግ ሕገወጥ የሆነውን ደረሰኝ ወይም ሰነድ መያዝ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተያዘ ወይም የተገኘ ሰነድ በማስረጃነት በፍርድ ቤት ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡
፬/ ሕገወጥ ደረሰኞችን ወይም ሰነዶችን ለመስጠት ፍቃደኛ ባልሆነ ግብር ከፋይ ላይ የፖሊስ ኃይል በመጠቀም ማስገደድ ይቻላል፡፡
፭/ ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፫/ አፈፃፀም በባለሥልጣኑ ሠራተኛ ትብብር የተጠየቀ ማናቸውም የፖሊስ ኃይል አባል የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
፲፬/ የአዋጁ አንቀጽ ፵፪ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ አንቀጽ ፵፪ተተክቷል፣

‹‹፵፪/ መቀጫንስለማንሳት
፩/ ባለሥልጣኑ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በታክስ ከፋይ ላይ የተጣለ አስተዳደራዊ መቀጫ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ ለማድረግ ይችላል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ መሠረት የሚነሳው መቀጫ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፵፯ መሠረት የሚታሰበውን ወለድ አይጨምርም፡፡››
፲፭/ በአዋጁ አንቀጽ ፵፫ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ውስጥ ‹‹የሚፈለግበትን ታክስ ካልከፈለ›› ከሚለው ሐረግ ቀጥሎ ‹‹ወይም ይግባኝ ካላቀረበ›› የሚል ሐረግ ተጨምሯል፡፡
፲፮/ የአዋጁ አንቀጽ ፵፭ ንዑስ አንቀጽ /ሀ/፣ /ለ/፣ /ሐ/ እና /መ/ የንዑስ አንቀጽ /፩/ ፊደል ተራ /ሀ/፣ /ለ/፣ /ሐ/ እና /መ/ ሆነው የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ተጨምሯል፣
‹‹፪/ ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ለ/ አፈጻጸም ‹‹ሀሰተኛ ደረሰኝ›› ማለት በባለሥልጣኑ ሳይፈቀድ የታተመ ወይም በኮምፒውተር የተዘጋጀ ደረሰኝ ወይም የግዢውን ወይም የሽያጩን ሂሣብ ለማሳነስ ወይም ለመጨመር በማሰብ ወይም በቸልተኛነት በሰነዱ ላይ አሀዝ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማተም ወይም በማባዛት ወይም ሁሉንም ቅጂዎች እንደበራሪ መጠቀም ወይም የሚፈቀደው የታክስ ተቀናሽ ወይም የተመላሽ ሂሣብ እንዲጨምር ወይም የማይገባውን ተመላሽ ለማግኘት ወይም ሌላ ማናቸውም የማጭበርበር ተግባር ለመፈጸም የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡››
፲፯/ ከአዋጁ አንቀጽ ፵፮ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ቀጥሎ የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፭/ ተጨምሯል፣
‹‹፭/ ማናቸውም ታክስ ከፋይ በማንኛውም የሂሳብ ጊዜ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ባይኖረውም የታክስ ማስታወቂያ ካላቀረበ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንጽ ፬/ሀ/ መሠረት ይቀጣል፡፡››
፲፰/ ከአዋጁ አንቀጽ ፵፯ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ አንቀጽ ፵፯ሀ፣ ፵፯ለ እና ፵፯ሐ ተጨምረዋል፣

‹‹፵፯ሀየሽያጭመመዝገቢያመሣሪያአጠቃቀምግዴታዎችንባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ ያለበት ሰው፣
፩/ ዕውቅና ያልተሰጠው ወይም በባለሥልጣኑ ዘንድ ያልተመዘገበ መሣሪያ ወይም የሽያጭ ነቁጣ ሶፍትዌር ሲጠቀም ከተደረሰበት ለተጠቀመበት ለእያንዳንዱ መሣሪያ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፪/ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ በሌላ ማናቸውም ዓይነት ደረሰኝ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፫/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም የፊሲካል ማስታወሻው እንዲቀየር ያደረገ ወይም ጉዳት ለማድረስ ወይም ማስታወሻውን ለመቀየር ሙከራ ያደረገ ከሆነ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፬/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ሥርዓት ኦዲት እንዳያደርግ መሰናክል ከፈጠረ ወይም በመሳሪያው ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በአገልግሎት ማዕከል የቴክኒክ ምርመራ ካላስደረገ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፭/ በንግድ ሥራው ለሚጠቀምበት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከአገልግሎት ማዕከል ጋር ውል ካልፈጸመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን ከተርሚናል ጋር ሳያያይዝ ከተጠቀመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የምርመራ መዝገብ ከመሣሪያው ጎን እንዲቀመጥ ካላደረገ ወይም በሽያጭ መመዝገቢያ የተመዘገቡ ዕቃዎች ተመላሽ መደረጋቸው ወይም ደንበኛው የተመላሽ ጥያቄ ማቅረቡ በተመላሽ መዝገብ ላይ በትክክል መመዝገቡ ሳይረጋገጥ የተመላሽ ደረሰኝ ከሰጠ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፮/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው በስርቆት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ አገልግሎት መስጠት ሲያቋርጥ በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው ብልሽት ባጋጠመው በሁለት ሰዓት ውስጥ ለአገልግሎት ማዕከሉና ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፹ሺ ይቀጣል፣
፯/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የሚቀመጥበትን የንግድ ቦታ ትክክለኛ አድራሻ ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፰/ የአድራሻ ወይም የስም ለውጥ ሲያደርግ ወይም የንግድ ሥራውን የሚያቋርጥ ሲሆን ከሦስት ቀናት አስቀድሞ ለአገልግሎት ማዕከሉና ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፱/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው ጥቅም ላይ በሚውልበት የንግድ ሥራ ቦታው፣
ሀ/ የተጠቃሚውን ስም፣ የንግድ ስም፣ የንግዱ ሥራ የሚካሄድበትን አድራሻ፣ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን የዕውቅና እና የመጠቀሚያ ፈቃድ ቁጥር፣
ለ/ ‹‹የሽያጭ ሠራተኞች መሣሪያው የተበላሸ ከሆነ በባለሥልጣኑ ፈቃድ የታተመ ተከታታይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ ለደንበኛው የመስጠት ግዴታ አለባቸው›› የሚል ማስታወቂያ፣ እና
ሐ/ ‹‹ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ማስታወቂያ፣ በግልጽና በሚታይ ቦታ ለጥፎ ካልተገኘ ብር ፲ሺ ይቀጣል፣
፲/ ሥራ ላይ የዋለውን የሽያጭ ነቁጣ ሶፍት ዌር ባለሥልጣኑ ዕውቅና ባልሰጠው ሰው እንዲቀየር ወይም እንዲሻሻል ካደረገ ብር ፴ሺ ይቀጣል፡፡

፵፯ለየአቅራቢነትግዴታዎችንባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማንኛውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ወይም ሶፍትዌር አቅራቢነት ዕውቅናና ፈቃድ የተሰጠው ሰው፣
፩/ የንግድ ሥራውን የአድራሻ ለውጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፪/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ለገበያ ካዋለ ብር ፭፻ሺ ይቀጣል፣
፫/ ለእያንዳንዱ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ምዝገባ ከባለሥልጣኑ የመሣሪያ መለያ ቁጥር ካልወሰደ ወይም የወሰደውን የመሣሪያ መለያ ቁጥር ለእይታ በሚያመች ቦታ በመሣሪያው ላይ ካልለጠፈ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፬/ በሥራ ላይ ባሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርገውን ማናቸውም ለውጥ ለባለሥልጣኑ በቅድሚያ ካላስታወቀ ወይም ስለ መሣሪያው አጠቃቀም በሚያብራራው የአጠቃቀም መመሪያ ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ካስገባ ወይም ትክክለኛውን መረጃ ከቀነሰ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፭/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በመሰረቃቸው ወይም ሊጠገኑ በማይቻልበት ሁኔታ በአደጋ ምክንያት ብልሽት የደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀው እንዲተኩላቸው ለሚጠይቁ የአገልግሎት ማዕከላት በሦስት ቀናት ውስጥ ለማቅረብ አለመቻሉን ለባለ ሥልጣኑ አስቀድሞ ካላስታወቀ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፮/ ውል ስለተዋዋላቸው የአገልግሎት ማዕከላት መረጃ ካልያዘ ወይም ውላቸውን ስላቋረጡ ወይም አዲስ ስለተዋዋላቸው የአገልግሎት ማዕከላት ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣

፵፯ሐየአገልግሎትማዕከልግዴታዎችን ባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል፣
፩/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የፊሲካል ማስታወሻ በተተካ በሁለት ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፳ሺ ይቀጣል፣
፪/ ውል የገባባቸውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በዓመት አንድ ጊዜ የቴክኒክ ምርመራ ካላደረገ ብር ፳ሺ ይቀጣል፣
፫/ አቅራቢው ዕውቅና ሳይሰጠውና በባለሥልጣኑ ዘንድ ሳይመዘገብ በሥራ ላሰማራው ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ብር ፶ሺ ይቀጣል፡፡››
፲፱/ ከአዋጁ አንቀጽ ፶ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ አንቀጽ ፶ሀ፣ ፶ለ፣ ፶ሐ፣ ፶መ፣ ፶ሠ፣ እና ፶ረ፣ ተጨምረዋል፣

‹‹፶ሀ. ለተጨማሪእሴትታክስከፋይነትአለመመዝገብ
ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት የመመዝገብ ግዴታ ያለበት ሆኖ ሳይመዘገብ የተገኘ ግብር ከፋይ ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ እስከ ብር ፶ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እሥራት ይቀጣል፡፡
፶ለ. የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ ደረሰኝ
ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ማካሄድ
፩/ ማንኛውም ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበ ሰው ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይት ሲያካሂድ ከተገኘ ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ በማያንስ እና ከብር ፩፻ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ በተጠቀሰው ሕገወጥ ደረሰኝ ላይ በተመለከተው የገንዘብ መጠን መሠረት መከፈል የነበረበት ታክስ ከብር ፩፻ሺ በላይ ከሆነ የሚጣለው የገንዘብ ቅጣት የታክሱን መጠን ያህል ይሆናል፡፡

፶ሐ. ያልተፈቀደደረሰኝመጠቀምወይምማተም
ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳይሰጥ በኮምፒውተር የተዘጋጀ ደረሰኝ ወይም ደረሰኝ በማሳተም የተጠቀመ ወይም የደረሰኝ ሕትመት አገልግሎት የሰጠ ሰው ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ እስከ ብር ፩፻ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት ያስቀጣል፡፡

፶መ. የሽያጭመመዝገቢያመሣሪያአጠቃቀምን በሚመለከትስለሚፈጸምጥፋት
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ ያለበት ሰው፡-
፩/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠው ወይም ያልተመዘገበ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከተጠቀመ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፪/ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፫/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የፊሲካል ማስታወሻ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም የፊሲካል ማስታወሻው እንዲቀየር ያደረገ ወይም ጉዳት ለማድረስ ወይም ማስታወሻውን ለመቀየር ሙከራ ያደረገ ከሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፬/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን ሥርዓት ኦዲት እንዳያደርግ መሰናክል የፈጠረ ወይም በመሣሪያው ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በአገልግሎት ማዕከል የቴክኒክ ምርመራ ያላስደረገ ከሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፭/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የሚገኝበትን የንግድ ቦታ ትክክለኛ አድራሻ ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡

፶ሠ. በአቅራቢያዎችየሚፈጸሙጥፋቶች
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ወይም ሶፍትዌር አቅራቢነት ዕውቅናና ፈቃድ የተሰጠው ሰው፡-
፩/ የንግድ ሥራውን የአድራሻ ለውጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፪/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠውን መሣሪያ ለገበያ ካዋለ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፫/ በሥራ ላይ ባሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርገውን ማናቸውም ለውጥ ለባለሥልጣኑ በቅድሚያ ካላስታወቀ ወይም በመሣሪያው የአጠቃቀም መመሪያ ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ካስገባ ወይም ትክክለኛውን መረጃ ከቀነሰ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡

፶ረ. በሽያጭመመዝገቢያመሣሪያዎች የአገልግሎትማዕከልናሠራተኞችየሚፈጸሙጥፋቶች
፩/ ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል አቅራቢው ዕውቅና ያልሰጠውንና በባለሥልጣኑ ዘንድ ያልተመዘገበ ሠራተኛ በሥራ ላይ አሰማርቶ ከተገኘ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪/ ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ያለአገልግሎት ማዕከሉና ያለባለሥልጣኑ ዕውቅና ከፈታታ ወይም ከገጣጠመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ሳይበላሽ ሆን ብሎ እሽጉን ካነሳ ወይም አካሉን ከቀየረ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ አድራጎቶች ከፈጸመ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፭ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡››
፳/ በአዋጁ አንቀጽ ፶፩ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ውስጥ ‹‹በ፪ /ሁለት/ ዓመት እስራት›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹‹ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፳፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፶፫ ንዑስ አንቀጽ /፪/ እና /፫/ የነበሩት ንዑስ አንቀጽ /፬/ እና /፭/ ሆነው የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፪/ እና /፫/ ተጨምረዋል፣
‹‹፪/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች አጠቃቀም ደንብና መመሪያዎችን በመተላለፍ፣
ሀ/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የፈታታ ወይም የገጣጠመ ወይም የሰርቪስ ሠራተኛ በሌለበት ሥራ ላይ እንዲውል የፈቀደ ወይም የመሣሪያውን መለያ ቁጥር ያቀያየረ እንደሆነ፣ ወይም
ለ/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ተጠቃሚው ወይም በአገልግሎት ማዕከሉ ወይም በሠራተኛው ወይም በአቅራቢው የተፈጸመን ማናቸውንም ሕገ ወጥ አድራጎት እያወቀ ወይም በቸልተኝነት በ፳፬ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ለባለሥልጣኑ ሪፖርት ያላደረገ እንደሆነ፣
ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፭ሺ በማያንስና ከብር ፲ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡
፫/ የግብር ባለሥልጣኑ ሠራተኛ ያለ በቂ ምክንያት ጉዳይን በማጓተት በግብር ከፋይ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት በፍትሐ ብሔር ያለበት ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ጥፋተኛነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡››

. አዋጁየሚፀናበትጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ታህሣሥ ፲፮ ቀን ፪ሺ፩ ዓ.ም.
ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

1 Comment

  1. Abdush Husen says:

    its nice

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s