አሠሪና ሠራተኛ ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ህግ


የስነ-ስርዓት ህግ ግብ በፍርድ ቤት የሚካሄዱ ክርክሮች ቀልጣፋ፤ ወጪ ቆጣቢና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲቋጩ ማስቻል ነው።  የዚህ ግብ መሳካት በተለይ በሥራ ክርክሮች ላይ የተለየ እንደምታ አለው። የሥራ ውል መቋረጥ በሠራተኛው እና በቤተሰቡ ዕለታዊ ኑሮ ላይ ከሚያሳድረው ከባድ ጫና አንጻር አሠሪው ላይ የሚያቀርባቸው የመብት ጥያቄዎች ሳይውሉ ሳያድሩ በፍጥነት መቋጨት ይኖርባቸዋል። ይህን እውን ለማድረግ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ከፊል የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎች የሥራ ክርክርን ልዩ ባህርያት ግምት ባስገባ መልኩ እንዲቀረጹ ተደርጓል።

በሁለቱም ወገን ለአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ የሚቀርብ እንዲሁም በሠራተኛ ወይም በሠራተኛ ማህበር ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የሥራ ክርክር ከዳኝነት ክፍያ ነፃ መሆኑ[1]፤ ቦርዱ የቀረበለትን ጉዳይ በ30 ቀናት[2]ይግባኝ ሰሚ ሥራ ክርክር ችሎት ደግሞ በ60 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ያለባቸው መሆኑ[3]፤ አማራጭ የሥራ ክርክር መፍቻ ዘዴዎች በህጉ መዘርጋታቸው[4] እንዲሁም የቋሚ ወይም ጊዜያዊ አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በልዩ የስነ-ስርዓት ደንቦች እንዲገዛ መደረጉ[5] እና ቦርዱ የራሱን ስነ-ስርዓት ደንቦች እንዲያወጣ ስልጣን መሰጠቱ[6]ሁሉም የሥራ ክርክሮችን የተለየ ባህርይ ግምት ውስጥ በማስገባት የተቀረጹ የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎች ናቸው። በአጠቃላይ አነጋገር ለአሠሪና ሠራተኛ ህግ መሰረታዊ ዓላማዎች ውጤታማ ስኬት በልኩ የተሰፋ የስነ-ስርዓት ህግ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል።

አሠሪና ሠራተኛ ህጉ ላይ ያሉ ልዩ የስነ-ስርዓት ደንቦች ለህጉ ውጤታማ አተገባበር ምን ያህል በቂ ናቸው? በተጨባጭ ያመጡት ለውጥስ እንዴት ይመዘናል? የሚለው ጥያቄ ራሱን የቻለ ዳሰሳ ይፈልጋል። በዚህ የተነሳ ዝምድናቸውን በተለይም በሥራ ክርክር ወቅት የስነ-ስርዓቱ ድንጋጌዎች የአሠሪና ሠራተኛ ህጉን ዓላማ ውጤት በሚሰጥ መልኩ የመተርጎም አስፈላጊነት ለማሳየት ያክል ‘በፍርድ ያለቀ ጉዳይ’ ተፈጻሚ የሆነበት መንገድ እንደሚከተለው ተዳሷል። 

በፍርድ ያለቀ ጉዳይ

በሥራ ክርክር ችሎት ሠራተኛው የፈፀመው ድርጊት ከሥራ ለማሰናበት በቂ አይደለም ተብሎ መወሰኑ አሠሪው በሠራተኛው ላይ በፍትሐብሔር ጉዳይ ሊያቀርብ የሚችለውን ክስ የሚያስቀር የመጨረሻ ፍርድ /ውሳኔ/ አይደለም። (አመልካች የኢትዮጵያ እህሌ ንግድ ድርጅት እና ተጠሪ እነ ኃይለየሱስ ቱኪ /4 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁ. 44588 ቅጽ 10 ሚያዝያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም) በዚህ ነጥብ ችሎቱ እንዳብራራው፤

የአሠሪና ሠራተኛ ክርክር ችሎት የሚወሰነው መሰረታዊ ጭብጥ ሠራተኛው በፍትሐብሔር ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው ሣይሆን አሠሪው ሠራተኛውን ከሥራ ለማሰናበት የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለ ወይስ የለም? የሥራ ስንብቱ የሕጉን ሥርአት ተከትሎ የተፈፀመ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው።

የችሎቱ አነጋገር ከፊል እውነት ቢኖረውም መነሻው ድርጊት በፍትሐብሔር ሆነ በአሠሪና ሠራተኛ ህግ ተመሳሳይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሠራተኛው በአንደኛው ህግ ከሀላፊነት ነጻ በሌላኛው ህግ ደግሞ ሀላፊ የሚሆንበት የህግ መሰረት የለም። ‘ገንዘብ አጉድለሀል’ በሚል ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ አለማጉደሉ ተረጋግጦ ስንብቱ ህገ-ወጥ ከተደረገ በፍትሐብሔር ለጉደለቱ ተጠያቂ ሆኖ እንዲከፍል ሊወሰንበት አይገባም። እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ሙሉ በሙሉ ከፍትሐብሔር ህግ ተነጥሎ ራሱ የቻለ የህግ ክፍል እንደሆነ ያልተገባ አቋም እንደመያዝ ይቆጠራል። በሁለቱ መካከል ልዩነት መኖሩ ባይካድም የልዩነታቸው መልክ እንደ ወንጀል እና ፍትሐብሔር ህግ ጫፍ እና ጫፍ የሚያራርቃቸው አይደለም።

ፍርድ ያገኘው ጉዳይ እና አዲስ የሚጠየቀው ዳኝነት ሁለቱም የሥራ ክርክሮች በሚሆኑበት ጊዜ በመርህ ደረጃ የፍ/ስ/ስህ/ቁ. 5 ያለቅደመ ሁኔታ ተፈጻሚነት ሊያገኝ የሚገባ ቢሆንም ይህ አነጋገር ግን በጊዜ ሂደት ድጋሚ መሆናቸው ቀርቶ አዲስ መልክ የሚይዙ የመብት ጥያቄዎችን አያጠቃልልም። ክሱ በቀረበበት ወቅት የማይኖር መብት ከጊዜ በኋላ ሊፈጠር ስለሚችል ጥያቄው ‘በፍርድ ያለቀ’ ተብሎ ውድቅ ሊደረግ አይገባም።

ይህ መሰረታዊ ሀሳብ በሰ/መ/ቁ 12380 (አመልካች የግብርና ምርት ማሣደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ጀማል አሕመድ ጥቅምት 16 ቀን 1999 ዓ.ም. ያልታተመ) ላይ በጥንቃቄ ባለመፈተሹ የስነ ስርዓት ህጉ በተዛባ መንገድ እንዲተረጎም ምክንያት ሆኗል። በዚህ መዝገብ ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ በጫኝና አውራጅነት ሥራ ብር 1000 (አንድ ሺ ብር) እየተከፈላቸው ከ1974 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 1994 ዓ.ም. ድረስ ሲሰሩ ቆይተው የሥራ ውላቸው ከህግ ውጭ በመቋረጡ ካሳ፣ የስንብት ክፍያ፣ የ17 ዓመት የበዓላት ክፍያ እና የዓመት እረፍት ክፍያ እንዲከፈላቸው በስር ፍ/ቤት ተወስኖላቸዋል። አመልካች በበኩሉ ውሳኔው በሰበር ችሎት እንዲታረምለት አቤቱታውን አቅርቧል። በተጨማሪም የአሁን ተጠሪ ቀደም ሲል ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በመሆን የቋሚነት ጥያቄ አቅርበው ውድቅ መደረጉን የሚያሳይ የውሳኔ ግልባጭ ከአቤቱታው ጋር አያይዟል።

በሰበር ውሳኔው ላይ እንደተዘገበው አመልካች ቅሬታ ያደረበት ተጠሪ ቋሚ ሠራተኛ ተብለው ከ1974 ዓ.ም. እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ ያለው የበዓላት ክፍያ እና የዓመት እረፍት እንዲከፈላቸው በስር ፍ/ቤት በተሰጠው የውሳኔ ክፍል ላይ ነው። ሆኖም የቋሚነት ጥያቄውን አስመልክቶ አመልካች በስር ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አላነሳም። በተጨማሪም የታለፈበት ወይም ውድቅ የተደረገበት መቃወሚያ ስለመኖሩ በመጥቀስ አልተከራከረም።

ከተረጋገጡት ፍሬ ነገሮችና ከአመልካች ክርክር ብሎም ከስር ፍ/ቤት ውሳኔ ይዘት አንጻር የሥራ ውሉ የቆይታ ጊዜ እና የመቋረጡ ህጋዊነት በጭብጥነት ተይዘው መመርመር ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ችሎቱ የመሰረተው ጭብጥ “የአሁኑ ተጠሪ ክርክር በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 5 መሰረት ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል ወይስ አይገባም?” የሚል ነው። የተሳሳተ ጭብጥ ወደ ተሳሳተ ውሳኔ እንደሚያመራ ግልጽ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ችሎቱ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሲሽር ከጭብጥ አያያዝ የማይመዘዙ ተጨማሪ ስህተቶችን ሰርቷል።

ከላይ ለማመልከት እንደተሞከረው ተጠሪ ለሰበር ክርክሩ መነሻ ከሆነው ክስ በፊት ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በመሆን የቋሚነት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም። ተቀባይነት አለማግኘቱ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ለመሻር በችሎቱ ዘንድ በቂና ብቸኛ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል። በዚህ ነጥብ ላይ ሐተታው እንደሚከተለው ይነበባል።

…ተጠሪ በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲል ሥልጣን ባለው አካል ውሳኔ እንዳልተሰጠ በማስመሰል…በድጋሚ አዲስ ክስ በማቅረብ ተወስኖ እንዲፀና የተደረገው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 5 የሚቃረን መሠረታዊ የህግ ሥህተት ነው ብለናል።

ድምዳሜው በአንክሮ ሲፈተሽ ግድፈቶቹ ጎልተው ይታያሉ። ለመጥቀስ ያክል፤

  • መቃወሚያው በስር ፍ/ቤት አልተነሳም። ውሳኔም አላረፈበትም። የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 5 በመቃወሚያነት በስር ፍ/ቤት ሳይነሳ በሰበር የሚስተናገድበት ስርዓት የለም። የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ህጉም በግልጽ ይከለክላል።[7] የሰበር ችሎት ስልጣን መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ውሳኔ ማረም እንጂ በመቃወሚያ ላይ ብይን መስጠት አይደለም። ከፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 5 ጋር በተያያዘ የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ብይን ሆነ ውሳኔ የለም። ውሳኔ ያላረፈበት ጉዳይ ከችሎቱ የስልጣን ክልል ውጪ ነው። ጉዳዩ ውሳኔ ስላላረፈበት በሐተታው የተተቸው የስር ፍ/ቤት ሳይሆን ተጠሪ ነው። “ተጠሪ በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲል ሥልጣን ባለው አካል ውሳኔ እንዳልተሰጠ በማስመሰል…” የሚለው አገላለጽ በእርግጥ የታረመው የተጠሪ ስህተት ነው ወይስ የስር ፍ/ቤቶች? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
  • ተጠሪ ቀድሞ ክስ ያቀረቡበት ጉዳይ እና በሰ/መ/ቁ 12380 በስር ፍ/ቤት ዳኝነት የጠየቁበት ጉዳይ ለየቅል ናቸው። የቋሚ ልሁን ጥያቄ ከሥራ ውል መቋረጥ ብሎም ከበዓላትና የዓመት እረፍት የክፍያ ጥያቄ ጋር ምን ያገናኘዋል? የሥረ ነገርና የጭብጥ አንድነት በሌለበት የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 5 ድንጋጌ እንደ መቃወሚያ ተነስቶ መዝገብ አያዘጋም። የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አያስለውጥም።
  • የተጠሪ የቋሚነት ጥያቄ አስቀድሞ በፍርድ የተወሰነ ነው ቢባል እንኳን በውጤት ደረጃ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለመሻር የሚያስችል በቂ ምክንያት አይደለም። ሊሻር የሚችለው ቋሚነትን አስመልክቶ በስር ፍ/ቤት የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ብቻ ነው። የመሻሩ ውጤት ተጠሪ ለተወሰነ ሥራ ወይም ጊዜ መቀጠራቸውን ድምዳሜ ላይ ከሚያደርስ በስተቀር የሥራ ውሉን መቋረጥ ህጋዊ አያደርገውም። የውሉ መቋረጥ ህጋዊነት ከአዋጁ አንቀጽ 24(4) አንጻር በጭብጥነት ተይዞ ሊመረመር ይገባው ነበር።

ችሎቱ የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 5 ድንጋጌን ቀጣይነት እና ዘላቂነት ባለው የቅጥር ግንኙነት ላይ ሁልጊዜ ተፈጻሚ ማድረጉ አግባብነት እንደሌለው በጊዜ ሂደት የተረዳው ይመስላል። ከአራት ዓመታት በኋላ በሰ/መ/ቁ 66242 (አመልካች ሙሉ ደምሴ እና ተጠሪ ሸራተን አዲስ ሐምሌ 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 9) የተንጸባረቀው አቋም የሰ/መ/ቁ 12380 የህግ ትርጉም በግልጽ መለወጡን ባይጠቅስም በውጤት ደረጃ የአስገዳጅነት ኃይሉን እንዳሳጣው በእርግጠኝነት መናገር ይችላል። በሰ/መ/ቁ 66241 አመልካች ካቀረቡት የተለያዩ የክፍያ ጥያቄዎች መካከል ከፊሉ ቀደም ሲል በፍ/ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎባቸዋል። አመልካች ውሳኔ ባገኘው ጉዳይ ላይ በድጋሚ ክስ ሲመሰርቱ የስር ፍ/ቤቶች ጉዳዩ አስቀድሞ ውሳኔ እንዳገኘ በመጠቆም የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 5 ድንጋጌን ጠቅሰው ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ይሁን እንጂ የስር ፍ/ቤቶች የስነ ስርዓት ህጉን ድንጋጌ ከቅጥር ግንኙነት ልዩ ባህርይ አንጻር ማጣጣም ባለመቻላቸው በዚህ ነጥብ ላይ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ተሽሯል። የተጣጣመው የችሎቱ የህግ ትርጉም እንደሚከተለው ይነበባል።

የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ካለው ቀጣይነትና ዘላቂነት አንጻር…ሠራተኛው በአንድ ወቅት ሊጠበቅልኝ ወይም ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ያቀረበው የመብት ወይም የክፍያ ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉ በሌላ ጊዜ መብቱን ወይም ክፍያውን ለመጠየቅ የሚያስችለውን የስራ ውል የህግ ድንጋጌ ወይም የህብረት ስምምነት ዋቢ በማድረግ እንዳይጠይቅ የሚገድበው አይደለም።


[1] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 162

[2] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 152/1/

[3] አዋጅ ቁ. 1156/2011

[4] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 141-144

[5] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 147

[6] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 149

[7] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 244(3) ይመለከቷል፡፡

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s