አሠሪና ሠራተኛ ህግ ንድፈ—ሀሳባዊ ምልከታዎች


አሠሪና ሠራተኛ ህግ ንድፈ—ሀሳባዊ ምልከታዎች

በአሠሪና ሠራተኛ ህግ እድገት ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ኢኮኖሚክስንና ሰብዓዊ መብትን መሠረት ያደረጉ ሁለት ግዙፍ የአስተሳሰብ አቅጣጫዎች በተለያየ ደረጃ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ኢኮኖሚክስን መነሻ በማድረግ የተቃኙ አስተሳሰቦች የአሠሪና ሠራተኛ ህግን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት መነጽር ምርታማነትንና የነጻ ገበያ ውድድርን ማዕከል ያደርጋል። የዚህ አስተሳሰብ ቀንደኛ አራማጆች ከሆኑት መካከል ኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች (neoclassical economists) አነስተኛ የሥራ ሁኔታዎችን የሚያዩት እንደ ጫና (ሸክም) ነው። ለምሳሌ ሠራተኛው እረፍት ሲወጣ አሠሪው ስራ ለማይሰራ ሠራተኛ ደመወዝ እንዲከፍል ይገደዳል። እረፍት በወጡ ሠራተኞች ምክንያት ትርፍና ምርታማነት እንዳይቀንስ አሠሪው የሚኖረው አማራጭ በስራ ገበታ ያሉትን ሠራተኞች ስራውን ደርበው እንዲሰሩ ማድረግ ወይም አዲስ ምትክ ሠራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት ነው። የመጀመሪያው አማራጭ ምርታማነትን ይቀንሳል። ሁለተኛው ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋል።

በሁለተኛው አማራጭ አሠሪው ለምትክ ሠራተኞች በሚከፍለው ደመወዝ የተነሳ ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳረግ በሚያመርተው ምርት ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ይገደዳል። ዋጋ በጨመረ ቁጥር በገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ያቅተዋል። ስለሆነም በኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አመለካከት በመንግስት የሚደነገጉ አነስተኛ የስራ ሁኔታዎች በምርታማነት ላይ ደንቃራ እንቅፋት በመፍጠር ጤናማ የገበያ ውድድርን ስለሚያዳክሙ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያስከትላሉ። በዚህም የተነሳ እነዚህ ኢኮኖሚስቶች የዓመት ፈቃድን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሁኔታዎች አስገዳጅ በሆነ መልኩ በህግ መደንገግ እንደሌለባቸው ይሟገታሉ።

ከእነዚህ ኢኮኖሚስቶች ጎራ የወጡትና ኒው ኢንስቲቱሸናሊስት (new institutionalist) በመባል የሚጠሩት ደግሞ በመነሻው ባይሆንም በመድረሻው ላይ የተለያ አመለካከት አላቸው። ሀሳባቸው ሲጠቃለል አነስተኛ የሠራተኛ መብቶች ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር አሠሪውን ተጠቃሚ ያደርጉታል የሚል ነው። ስለሆነም በስራ ሰዓት ላይ የሚደረግ ገደብ ምርታማነትን የሚቀንስ ሳይሆን በተቃራኒው ስለሚጨምር ከዚህ አንጻር ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ ለቁፋሮ የተቀጠረ ሠራተኛ በተከታታይ ያለ ዕረፍት ለአስራ ስድስት ሰዓታት ከሚቆፍር ይልቅ በቀን ስምንት ሰዓት ቢቆፍር በስራው የበለጠ ውጤት ያስገኛል። በቀን፣ በሳምንትና በዓመት የተወሰነ ዕረፍት ቢሰጠው ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል። ኒው ኢንስቲቱሺናሊስቶች በህግ የሚደነገጉ አነስተኛ የሠራተኛ መብቶች አስፈላጊነት ይቀበላሉ። አስፈላጊነታቸውን የሚመዝኑት ግን ከምርታማነት ማለትም ለአሠሪው ከሚያስገኙት ጥቅም አንጻር ነው። ስለሆነም የዓመት ፈቃድ የሚያስፈልግበት ምክንያት ሠራተኛው አካሉ እና አዕምሮው ታድሶ በብቃት ለመስራት እንዲያስችለውና በዚህም ውጤታማነቱ እንዲጨምር ነው።

ከላይኞቹ አስተሳሰቦች በተቃራኒ የሚገኘው ሰብዓዊ መብትን ማዕከል ያደረገ አቀራረብ መነሻውም ሆነ መድረሻው ሠራተኛው ነው። በዚህ መሠረት ለሠራተኞች መብቶች በህግ ዕውቅና መስጠት የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት ሠራተኛው ሰብዓዊ ክብሩ እና ጤንነቱ በአሠሪው እንዳይጣስ ከለላ ለመስጠት ነው። አነስተኛ የሥራ ሁኔታዎች የአሠሪውን ምርታማነት አሳደጉም አላሳደጉም ለሠራተኛው በህግ ሊታወቁለት ይገባል። ሠራተኛው በቀን አስራ ስድስት ሰዓት መስራት የማይኖርበት በስራው ውጤታማ ስለማይሆን አይደለም። ይልቅስ አስራ ስድስት ሰዓት ማሰራት ኢ-ሰብዓዊ የጉልበት ብዝበዛ በመሆኑ ነው። በቀን፣ በሳምንት፣ በዓመት ዕረፍት ያስፈለገበት መሰረታዊ ምክንያት የበለጠ ለስራው ብቁ ስለሚያደርገው በዚህም የአሠሪው ምርታማነት እንዲጨምር አይደለም። ከዚያ ይልቅ መሰረታዊ ምክንያቱ ካለዕረፍት ማሰራት የሠራተኛን ሰብዓዊ ክብር የሚንድ ተግባር በመሆኑ ብቻ ነው። ስለሆነም በዚህ በሁለተኛው የአስተሳሰብ መስመር አስገዳጅነት ያላቸውን አነስተኛ ሁኔታዎች በመወሰን ከአሠሪ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች ከለላ እና ጥበቃ የሚያደርግ ህግ ሊኖር ይገባል።

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s