የአሠሪና ሠራተኛ ህግ እና የውል ህግ ተዛምዶ


የአሠሪና ሠራተኛ ህግ እና የውል ህግ

የአሠሪና ሠራተኛ ህግ የሥራ ውል እንደመሆኑ ለውል ህግ መሰረታዊ ደንቦች ይገዛል። ስምምነቱ በህግ ማዕቀፍ የሥራ ውል ተብሎ በሚጠራው የውል ዓይነት አማካይነት መልክ ይዞ ይቀረጻል። የሥራ ውል እንደማንኛውም ዓይነት ውል ሁሉ ለውል ህግ መሰረታዊ መርሆዎችና ደንቦች ተገዢ ነው። በፍ/ህ/ቁ 1676(1) ግልጽ ሆኖ እንደተደነገገው ውሎች ዓይነታቸው ሆነ ምክንያታቸው ማንኛውም ቢሆን በውል ህግ ጠቅላላ ደንቦች ይመራሉ። የሥራ ውል ሲመሰረት የሠራተኛው ሥራ የመሥራት፤ የአሠሪው ደመወዝ የመክፈል ግዴታዎች የተዋዋይ ወገኖች ተቀዳሚ ግዴታዎች ናቸው። በግላዊ የቅጥር ግንኙነት ውስጥ የሥራ ውል የሚጫወተውን ዓይነተኛ ሚና እንዲሁም በግዴታዎቹ መካከል ያለውን ትስስር የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 17189 (አመልካች የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ንጉሴ ዘለቀ ጥቅምት 17 ቀን 1998 ዓ.ም. ቅጽ 2) ሰፋ ያለ ትንተና በመስጠት እንደሚከተለው ገልጾታል።

“የሠራተኛና የአሠሪ ግንኙነት የሚመነጨው ሁለቱም ወገን ከሚገቡት ውል ነው። ይኸው ውል እንደማንኛውም ሌላ ውል ለሁለቱም ወገን መብት ያመነጫል ግዴታንም ይጥላል። ከነዚህ ተያያዥ መብትና ግዴታዎች አንዱ ሠራተኛው በውል ለማከናወን ቃል የገባውን ሥራ የማከናወን በተሠራው ሥራ መጠን ደግሞ በውሉ በተጠቀሰው ጊዜና መጠን ደመወዝ የማግኘት መብትና ግዴታ ነው። በዚህ መሠረት አሠሪው ከሠራተኛው ግልጋሎት ያገኛል። ባገኘው ግልጋሎት መጠንም በውሉ የተጠቀሰውን ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል። በመርህ ደረጃ እነዚህ መብትና ግዴታዎች ከውል የሚመነጩ አንዱ ያለሌላው ሊታሰቡ የማይችሉ የአንድ ሕጋዊ ግንኙነት ሁለት ገጽታዎች ናቸው።”

የችሎቱ ትንተና የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ያልሸፈናቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ውል ህግ ድንጋጌዎች መሄድ እንደሚገባ ጠቃሚ ቁምነገር ያስጨብጠናል። ቁምነገሩ ግን ሌላ ጠቃሚ ቁምነገር ይወልዳል፤ ይኸውም ወደ ውል ህግ ከማማተር በፊት በቅድሚያ የአሠሪና ሠራተኛ ህጉን ‘አሟጦ’ ለመተርጎም መሞከርና በትርጉም የማይደፈን ቀዳዳ መኖሩ ማረጋገጥ ይገባል። በተጠቀሰው መዝገብ ወደ ውል ህግ ትንተና የተገባው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ፀንቶ በነበረበት ጊዜ የሥራ ውል ከህግ ውጭ ሲቋረጥ የውዝፍ ደመወዝ አከፋፈልን ለመወሰን ነው። ለዚህ ደግሞ ህጉ ራሱ በቂ ምላሽ ነበረው። ‘ወደ ሥራ መመለስ’ ከእንግሊዝኛ አቻው reinstatement ጋር ከተገናዘበ በህገ-ወጥ መንገድ የተሰናበተ ሠራተኛ ወደ ሥራ እንዲመለስ /reinstated/ ሲወሰንለት የሚመለሰው ባዶ እጁን ስላለመሆኑ የእንግሊዝኛውን ቃል ጽንሰ ሀሳብ መረዳት ብቻውን ይበቃል።

የችሎቱ ትንተና አግባብነት ትንተና በተሰጠበት በዛው መዝገብ ሳይሆን በሰ/መ/ቁ 03171 (አመልካች የኢት/ኤሌክትሪክ ኃ/ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ ወ/ት ትርሲት ደገፉ ህዳር 16 ቀን 2001 ዓ.ም ቅጽ 8) ጎልቶ ይታያል። በዚህ መዝገብ የሥራ ውል የሚመሰረትበት ጊዜ አከራካሪ ጭብጥ ነበር። የሥራ ውል አለ የሚባለው ሠራተኛው ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ነው? ወይስ የቅጥር ደብዳቤ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ? አሠሪና ሠራተኛ ህግ ቦታውን ለውል ህግ ካላስረከበ በቀር ጥያቄው አይመለስም። የሰበር ችሎት በውል ህግ የውል አቀራረብ እና አቀባበል የሚመሩባቸውን ድንጋጌዎች ወደ ሥራ ውል በማምጣት የሥራ ውል ተመስርቷል የሚባለው ሠራተኛው ሥራ ሲጀምር ሳይሆን የቅጥር ደብዳቤ ሲቀበል እንደሆነ በማተት የአዋጁ ክፍተት እንዲሞላ አድርጓል።

የውል ህግን ፋይዳ ለማጉላት ተጨማሪ አስረጂ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል። በአዋጁ አንቀጽ 36-38 አሠሪው ደመወዝን ጨምሮ ሌሎች ክፍያዎች በሰባት ቀናት ውስጥ ለመክፈል የሚገደደው፤ ግዴታውን ጥሶ ክፍያ ካዘገየም ቅጣት የሚከፍለው የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ነው። የሥራ ውል ፀንቶ ባለበት ጊዜ የደመወዝ ክፍያ በመዘግየቱ የተነሳ በሠራተኛው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ህጉ መፍትሔ አላበጀለትም። እንበልና ለስድስት ወር ደመወዝ ያልተከፈለው ሠራተኛ በፍርድ ቤት ክስ ቢመሰርት ከረጅም ጊዜ ክርክር በኋላ ካልተከፈለው ደመወዝ ውጭ ሌላ ዳኝነት አያገኝም። ምክንያቱም የአሠሪና ሠራተኛ ህጉ የሥራ ውል ሲቋረጥ እንጂ ፀንቶ ባለበት ጊዜ ለመደመዝ ክፍያ በቂ አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ ተስኖታል። ይሄን የህጉን ድክመት ማረም የሚቻለው በመደበኛው የውል ህግ ድንጋጌዎች ነው። ደመወዝ መክፈል ዓይነተኛ የአሠሪ ግዴታ እንደመሆኑ ይሄን ግዴታውን የጣሰ አሠሪ በውል መጣስ ሠራተኛው ላይ ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናል። ደመወዝ ማዘግየት ውል መጣስ እንደመሆኑ ሠራተኛው የደረሰበት ጉዳት በውል ህግ ድንጋጌዎች ተመዝኖ ይካሳል።

ከአሠሪና ሠራተኛ ህግ የሚመመዘዙ ጥያቄዎችን ለመፍታት የውል ህግ ተገቢ የሚሆንባቸው ሌሎች ሁኔታዎች /ከሥራ ውል መቋረጥ ጋር በተያያዘ/ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 (6.5 በአዋጁ ያልተካተቱ ጉዳዮች) በሚለው ክፍል ስር የተዳሰሱ በመሆኑ ለበለጠ ግንዛቤ አንባቢ እንዲመለከተው ይመከራል።

የውል ህግ ‘ክፍተት የመሙላት’ ሚና ከአሠሪና ሠራተኛ ህግ መሰረታዊ ዓላማ ጋር መናበብ ይኖርበታል። ለምሳሌ የፀና ውል እንዲኖር በውል ህግ አንቀጽ 1678 ከተጠቀሱት መካከል የተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ እና የውሉ ህጋዊነት በተመሳሳይ ለሥራ ውልም ተፈጻሚነት አላቸው። እንበልና አሠሪው ድርጅት የተቋቋመበት መንገድ ህገ-ወጥ ከሆነ የሥራ ውሉ ህጋዊነት ኖሮት ሊቀጥል አይችልም። በውል ህግ መነጽር ሲታይ እንዲህ ዓይነት ውል ዋጋ አልባ ቢሆንም የድርጅቱን ሠራተኞች ያልተከፈለ ደመወዝ እና ሌሎች ክፍያዎች የማሳጣት ውጤት ሊኖረው አይገባም።

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s