የአሠሪና ሠራተኛ ህግ በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች እና የውጭ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ላይ ያለው ተፈጻሚነት


መግቢያ

የአንቀጽ 3(3) ሀ ድንጋጌ ይዘት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ወይም ኢትዮጵያ በምትፈራረማቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አዋጁ ተፈፃሚ እንዳይሆን ሊወሰን እንደሚችል ይናገራል። ድንጋጌው በራሱ በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ የሚያገለው ሠራተኛ የለም። እስካሁን ድረስ ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን ተጠቅሞ ያወጣው ማግለያ ደንብ ካለመኖሩም በላይ የህጉ ተፈጻሚነት ወሰን በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች አልተገደበም።

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና የውጭ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ላይ ያለውን ተፈጻሚነት በማስቀረት ረገድ ‘ያለመከሰስ መብት’ (immunity) ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ይህንን ከለላ አልፈው ወደ መደበኛው የክርክር ሂደት የሚዘልቁ ጉዳዮች ኢምንት ናቸው። ስለሆነም ከመነሻው አዋጁ በእነዚህ ድርጅቶችና ሚሲዮኖች ላይ ተፈጻሚ የሚሆንበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በአንቀጽ 3(3) ሀ እንደተመለከተው አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን ዓለም ዓቀፍ ስምምነት መፈረም ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ማውጣት አስፈላጊ አይሆንም።

የሁለትዮሽ ወይም ዓለም ዓቀፍ ስምምነት አስፈላጊ የሚሆነው ከክስ ከለላ ለመስጠት ነው። ያለመከሰስ መብት የሚያጎናጽፍ የሁለትዮሽ ስምምነት የአገሪቱን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ያሳጣቸዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ የሚንቀሳቀስ አህጉራዊ ወይም ዓለም ዓቀፋዊ ድርጅት በፍትሐ ብሔር ሆነ በወንጀል ከመከሰስ ከላለ የሚሰጥ በዋናው ድርጅትና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመ የሁለትዮሽ ስምምነት ካለ የድርጅቱ ሠራተኞች በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የሥራ ክርክር ማቅረብ አይችሉም። (አመልካች አቶ አለማየሁ መኮን እና ተጠሪ የምስራቅ አፍሪካ የበረሀ አንበጣ መከላከያ ድርጅት ታህሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 117390 ቅጽ 19)

የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና የውጭ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ያለ መከሰስ መብት መርሆችና እሴቶች መሰረታቸው የተጣለው በጊዜ ሂደት ዳብረው ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነት ባገኙ ገዢ ደንቦች ሲሆን እነዚህም ‘ልማዳዊ የዓለም ዓቀፍ ህግ’ (Customary International Law) ተብሎ በሚጠራው የህግ ክፍል ውስጥ ተጠቃለው ይገኛሉ። ያለ መከሰስ መብትን የሚመለከቱ አብዛኛዎቹ ደንቦች በጊዜ ሂደት በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ቢተኩም በስምምነቶቹ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች አሁንም ድረስ ልማዳዊ ዓለም ዓቀፍ ህግ ተፈጻሚነት አለው። እዚህ ላይ ያለ መከሰስ መብት ሲባል በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን በእነዚህ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ ክስ ለማቅረብ በሩ ሙሉ በሙሉ ዝግ ነው ማለት አይደለም። በጣም ጠባብ በሆኑ ሁኔታዎች ያለ መከሰስ መብት መከላከያ አይሆንም። የእነዚህ ሁኔታዎች ዝርዝር አፈጻጸም ከዚህ መጽሐፍ ወሰን ውጪ በመሆኑ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን ጨምሮ በሌሎች ዓይነት ግንኙነቶች ላይ ያለ መከሰስ መብትን አስመልክቶ የወጡትን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ጠቅለል ባለ መልኩ እናያለን።

ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከክስ ከለላ የሚሰጥ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት የወጣው እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. ነው። Conventioncc on the Privileges and Immunities of the United Nations በሚል ስያሜ የሚታወቀው ይኸው ስምምነት በአንቀጽ 2 በክፍል ሁለት ላይ የድርጅቱን ያለ መከሰስ መብት እንደሚከተለው ይደነግጋል።

The United Nations, its property and assets wherever located and by whomsoever held, shall enjoy immunity from every form of legal process except insofar as in any particular case it has expressly waived its immunity shall extend to any particular case it has expressly waived its immunity. It is, however, understood that no waiver of immunity shall extend to any measure of execution.

በእርግጥ ከዚህ ስምምነት መውጣት ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር (UN Charter) ለድርጅቱ ያለ መከሰስ መብትና ልዩ መብቶች (privileges) ዕውቅና ሰጥቷል። እነዚህን መብቶች የሚያጎናጽፈው የቻርተሩ አንቀጽ 105 በይዘቱ ጠቅለል ያለ (ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮችን ያልያዘ) ሲሆን ያለ መከሰስ መብትን ከድርጅቱ ዓላማና ተግባር ጋር ያስተሳስረዋል።[1] ዓለም ዓቀፍ ስምምነቱ የቻርተሩ አንቀጽ 105 ዝርዝር ማስፈጸሚያ ተደርጎ ይወሰዳል።[2] በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚገኙት የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እንደ እናት ድርጅታቸው ሁሉ ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1947 ዓ.ም. የወጣው Convention on the Privileges and Immunities of the Specialized Agencies በየአገራቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች እንዳይከሰሱ ከለላ ይሰጣቸዋል።

ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች

የውጭ አገር ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ሲባል ኤምባሲ፣ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤት፣ የክብር ቆንሲላ ጽሕፈት ቤት እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። እነዚህ የአንዲት ሉዓላዊት አገር ወኪሎች ናቸው። ያለ መከሰስ መብቱ የሚሰጠው ለወከሉት አገር ነው። ልማዳዊ ዓለም ዓቀፍ ህግ (Customary International Law) ሙሉ በሙሉ የንግድ ጠባይ ያላቸው ግንኙነቶች ብሎም በግል የሚፈጸሙ ተግባራትን ከአገራዊ፣ ሉዓላዊ ወይም መንግስታዊ ተግባራት ይለያል።[3] አገራት ያለመከሰስ መብት የሚኖራቸው በሁለተኛዎቹ ዓይነት ተግባራት ነው።[4] የአገራት (ስለሆነም ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች) ያለመከሰስ መብት በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ዓለም ዓቀፍ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. የወጣው United Nations Convention on Jurisdictional Immunities of States and Their Property ሲሆን ያለመከሰስ መብትን አስመልክቶ ካቀፋቸው ጠቅለል ያሉ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በቅጥር ግኝኑነት ወቅት የመብቱን አፈጻጸም የሚወሰን ልዩ ድንጋጌ ይዟል።[5]

የፍርድ አፈጻጸም

ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች በራሳቸው ፈቃድ (waiver) ወይም ያለመከሰስ ከለላቸው ተፈጻሚ በማይሆንባቸው ጠባብ ሁኔታዎች አንድ ፍ/ቤት በዋናው ጉዳይ ላይ አከራክሮ ውሳኔ መስጠቱ ውሳኔውን ወዲያውኑ ተፈጻሚ አያደርገውም። የክስ ከለላ (Immunity from Suit) እና የአፈጻጸም ከለላ (Immunity from Execution) ሁለቱም የሚታዩት በተናጠል ነው። ከላይ በተጠቀሱት ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ብሎም ሰፊ ተቀባይነት ባገኙት የልማዳዊ ዓለም ዓቀፍ ህግ መርሆዎች መሰረት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችና መለኪያዎች መሟላታቸው ሳይረጋገጥ በእነዚህ አካላት ላይ የተሰጠ ፍርድ አይፈጸምም። ለምሳሌ ድርጅቶቹ ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ አስፈላጊ በሆነ ንብረት ላይ አፈጻጸም ሊቀጥል አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ ፍርድ የተሰጠው ያለመከሰስ መብትን የሚመለከቱ የዓለም ዓቀፍ ህጎችንና ስምምነቶችን በመጣስ ከሆነ በአፈጻጸም ተግባራዊ የሚደረግበት አግባብ አይኖርም።

ከአፈጻጸም ከለላ ጋር በተያያዘ በሰበር ችሎት በታየ አንድ የሥራ ክርክር መዝገብ (አመልካች አቶ አለማየሁ ኦላና እና ተጠሪ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 98541 ቅጽ 17) ተጠሪ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማስፈጸም የቀረበ ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል። ተጠሪ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ነው። ያለመከሰስ መብትን አስመልክቶ በወጣው ኮንቬንሽን (Convention on the Privileges and Immunities of the Specialized Agencies) አንቀጽ 3 ክፍል 3 እና 4 መሰረት ተቋማቱ በክስ ሆነ በአፈጻጸም በፍ/ቤት ቀርበው እንዳይጠየቁ ከለላ ተሰጥቷቸዋል። ስለሆነም የፍርዱ ፍሬ በአፈጻጸም መነፈጉ ከስምምነቱ ድንጋጌዎች ጋር ይጣጣማል። ያም ሆኖ ግን በሰ/መ/ቁ 98541 የአፈጻጸም ጥያቄውን ላለመቀበል መነሻ የሆነው ምክንያት የአፈጻጸም ከለላ መሰረተ ሓሳብ ሳይሆን የአዋጁ አንቀጽ 3(3) ሀ ድንጋጌ ነው። ይሁን እንጂ የአንቀጽ 3(3) ሀ ድንጋጌ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ላይ ተፈጻሚ ላይሆን የሚችልበትን ሁኔታ ከመጠቆም ውጪ ተፈጻሚነቱን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ አያገልም። ይህን አስመለክቶ ኢትዮጵያ የፈረመቸው ስምምነት ሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣ ደንብ የለም። በተጨማሪም የድንጋጌው ግልጋሎት ከፍርድ በፊት እንጂ በኋላ አይደለም። የድንጋጌውን ትክክለኛ ይዘት ለመረዳት ሁለቱም ነጥቦች ጠቃሚ ቢሆኑም አዋጁ በተጠቀሱት ድርጅቶች ላይ ያለውን ተፈጻሚነት ለመወሰን አስፈላጊ አይደሉም። ያለመከሰስ መብት መልስ ሳያገኝ ስለ አንቀጽ 3(3) ሀ አይወራም። አዋጁን ተንተርሶ የሚቀርብ የሥራ ክርክር ክስ በድርጅቶቹ ያለመከሰስ መብት የተነሳ ውድቅ መደረጉ ስለማይቀር በድንጋጌው የሚመለስ ጭብጥ አይኖርም።


[1] C. F. Amerasinghe, Principles of the institutional law of international organizations (2nd Rev. New York: Cambridge University Press, 2005) ገፅ 317-8

[2] ዝኒ ከማሁ ገፅ 318

[3] Xiaodong Yang, State Immunity in International Law (Cambridge University Press, 2012) ገፅ 34

[4] ዝኒ ከማሁ

[5] ዝኒ ከማሁ በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በቅጥር ግንኙነት ወቅት ያለ መከሰስ መብትን ከቅጥር ግኝኑነት ጋር በተያያዘ በስፋት የተዳሰሰበትን የመጽሐፉን ምዕራፍ 4 (ገፅ 132-198) ይመልከቱ፡፡

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s