በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ


የሰ/መ/ቁ. 319ዐ6

4/3/2ዐዐ1 ዓ.ም.

ዳኞች፡- አብዱልቃድር መሐመድ

ሒሩት መለሠ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ – ነ/ፈጅ ሒሩት አሥራት

ተጠሪ፡- የአቶ መርስኤ መንበሩ ወራሾች አልቀረቡም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ቀጥሎ የተመለከተው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ነክ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን ተጠሪዎች ለዚሁ ፍ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ሟች አባታችን በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 3 ቀበሌ 53 ክልል ቁጥር 849 የሆነውን ቤት በ1957 ዓ.ም. ከቀድሞ ባለ ርስት በጭሰኝነት ተመርተው ተገቢው ኪራይ እየከፈሉ ሲገለገሉ የቆየ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 47/67 ሲታወጅ የባለርስትና የጭሰኛ ግንኙነት በመቋረጡ የአፈር ግብር ለመንግሥት እየከፈሉ የቆዩ ቢሆንም የቤት ባለቤትነት ደብተር ለማውጣት በቦታው ላይ ይዞታ እንደነበራቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከፍ/ቤት አስመስክረንና አረጋግጠን እንድንቀርብ የተጠየቅን በመሆኑ የቤት ባለቤትነት ደብተሩን ማግኘት እንድንችል በቦታው ላይ ይዞታ ያለን ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሰጠን በማለት ጠይቀዋል፡፡
አመልካቾች በተጠሪነት ያጣመሩት ባለመኖሩ ፍ/ቤቱ የአመልካካቾችን ምስክሮች ሰምቶ የአመልካቾች አባት ቦታውን በ1959 ዓ.ም. ከልዕልት ተናኘ ወርቅ ላይ በጭሰኝነት ተመርተው ውሃና መብራት በማስገባት ቤት ሠርተው የጋራዥ ድርጅት አቋቁመው ሲሰሩበት እንደበር አዋጅ ቁጥር 47/67 ከታወጀ በኋላ የቦታና የቤት ግብር ለመንግሥት ሲከፍል እንደነበር በማስረጃ የተረጋገጠ ስለሆነ ይሄው ተገልጾ ለሚመለከተው ክፍል ይፃፍላቸው በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በኋላም የአሁን አመልካች የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በወቅቱ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት አመልካቾች በይዞታቸው ሥር እንደሆነ ተገልጾ ማስረጃ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ የተሰጠበት ድርጅት በአዋጅ 47/67 መሠረት የተወረሰና የሚያስተዳድረው መሆኑን ገልጾ በሌለበት የተሰጠው ትዕዛዝ መብቱን እንደነካ በመግለጽ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 358 መሠረት በተቃዋሚነት ወደ ክርክሩ ለመግባት ጠይቆ በተፈቀደለት መሠረት ወደ ክርክሩ በመግባት ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ ክርክር የተነሳበት ድርጅት በአዋጅ 47/67 መሠረት ተወርሷል አልተወረሰም የሚለውን ጭብጥ ይዞ ጉዳዩን በመመርመር መወረሱ ስለተረጋጠ አመልካቾች ከአዋጅ 47/67 መንፈስ ውጭ ተወስዶብናል የሚሉ ከሆነ ይህንኑ ጥያቄያቸውን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ከሚያቀርቡ በስተቀር በተያዘው መዝገብ እንደማይስተናገድ ጠቅሶ አስቀድሞ ለአመልካቾች ይዞታ ያላቸው መሆኑ ተጠቅሶ እንዲፃፍላቸው የተሰጠው ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል በማለት አንስቷል፡፡ አመልካቾች በዚህ ውሣኔ ቅሬታ አድሮባቸው የይግባኝ ቅሬታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ ነክ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙ አከራክሮ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ድርጅት በይግባኝ ባዮች ይዞታ ሥር እንደነበርና በአዋጅም እንዳልተወረሰ የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያረጋግጡ እንደመሆኑ መጠን መልስ ሰጭው ድርጅቱ መወረሱን ባላረጋገጠበት ሁኔታ የሥር ፍ/ቤት ድርጅቱ መወረሱ ተረጋግጧል በማለት አስቀድሞ የሰጠውን ትዕዛዝ ማንሣቱ በአግባቡ አይደለም ሲል በመሻር የቀድሞው ትዕዛዝ ሊሰረዝ አይገባም በማለት ውሣኔ ሠጥቷል፡፡
የከተማው አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ሰበር ችሎትም ይሄው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አልተፈጸመበትም በማለት አመልካች ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ ሳይቀረበለው ቀርቷል፡፡ ለዚህ ችሎትም የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህንኑ በመቃወም ሲሆን ችሎቱም አቤቱታውን መርምሮ በሚያከራክረው ንብረት ላይ ተጠሪዎች የይዞታ ማስረጃ እንዲሰጣቸው በፍ/ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ተገቢ ነው ተብሎ የአመልካች መቃወሚያ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውድቅ መደረጉ ለሰበር ቀርቦ ሊታይ እንደሚገባው በማመኑ ተጠሪዎችን ጠርቷል፡፡ ሆኖም ተጠሪዎች በአድራሻቸው ሊገኙ ባለመቻላቸው በጋዜጣ ተጠርተው ስላልቀረቡ በጽሁፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል፡፡ በቃል ክርክርም ጊዜ ስላልቀረቡ ችሎቱ የአመልካችን የቃል ክርክር ብቻ አዳምጧል፡፡ በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆነ ችሎቱም ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ በቅድሚያ ችሎቱ የተመለከተው አመልካቾች አቤቱታ ያቀረቡበት ጉዳይ ለፍ/ቤት ሊቀርብ የሚችልና ዳኝነት የሚያፈልገው /Justicable/ መሆኑን በተመለከተ ነው፡፡ ተጠሪዎች በከተማ ነክ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ለክርክሩ ምክንያት በሆነው የንግድ ድርጅት ላይ የይዞታ መብት ያለን መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሰጠን በማለት ነው፡፡ ተጠሪዎች የዚህ ዓይነቱ ማስረጃ ከፍ/ቤቱ እንዲሰጣቸው የጠየቁትም የቤት ባለቤትነት ደብተር ከሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ለማግኘት እንደሆነም በአቤቱታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1195 ላይ የተመለከተ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን በማወቅ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የሚሰጠው በመንግሥት የአስተዳደር መ/ቤት በኩል እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንደዚሁም የምስክር ወረቀት የሚሰጥበት ሥርዓት የአስተዳደር መስሪያ ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት እንደሚወሰንም በዚሁ ድንጋጌ ሥር ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም ሰው በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ማግኘት የሚችለው ከሚመለከተው የመንግሥት አስተዳደር መስሪያ ቤት በኩል ሲሆን የሚመለከተው የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤት የምስክር ወረቀት አሰጣጡን አስመልክቶ በሚያወጣው የምስክር ወረቀትም እንደሚሰጥ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕጉ በዚህ መልኩ የባለቤትነት የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ከደነገገ የምስክር ወረቀቱን ለማግኘት እንዲቻል የይዞታ ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲሰጥ ፍ/ቤትን መጠየቅ ከነመነሻውም ቢሆን ጉዳዩ በፍ/ቤት ቀርቦ ዳኝነት የሚያስፈልገው /Jusciable matter/ እንዳልሆነ ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም የዚህ ዓይነቱ ማስረጃ ይሰጠኝ በማለት በፍ/ቤት የሚቀርብ አቤቱታ በፍ/ቤት ሊስተናገድ እንደማይችል ግልጽ በመሆኑ ከመነሻውም ቢሆን ፍ/ቤቱ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም በማለት መመለስ ሲገባው ጉዳዩን ማስተናገዱ አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ከዚህም በኋላ አመልካች በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 358 መሠረት መቃወሚያ ሲያቀርብ ፍ/ቤቱ የቀድመውን ትዕዛዝ መሰረዙ ከውጤት አኳያ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ይህንኑ ትዕዛዝ ምክንያቱን ለውጦ ሊያጸናው ሲገባ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ድርጅት መወረሱ አልተረጋገጠም በማለት መሻሩ ጉድለት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የከተማው ይግባኝ ሰማ ሰበር ችሎትም መሠረታዊ የሕግ ስህተት አልተፈጸመም በማለት ይህንኑ ጉድለት ሳያርም መቅረቱ በአግባቡ ሆኖ አላገኘነው፡፡

ው ሣ ኔ

1. በአዲስ አበባ ከተማ ነክ ሰበር ችሎት በመ/ቁ. ዐ1998 ሚያዝያ 19 ቀን 1999 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ እንደዚሁም ይግባኙ ችሎቱ በመ/ቁ. ዐዐ682 በ3ዐ/3/97 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሠረት በአብላጫ ድምጽ ሽረነዋል፡፡
2. ተጠሪዎች የቤት ባለቤትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት እንድችል የይዞታ መብት ያለን መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከፍ/ቤቱ ይሰጠን በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ለፍ/ቤት ቀርቦ ዳኝነት ሊሰጥበት የማይችል ጉዳይ /Justicable matter/ ስላልሆነ አቤቱታው ከመነሻውም ቢሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ነበር በማለት ወስነናል፡፡
3. ግራ ቀኙ ወጭና ኪሣራ ይቻቻሉ ብለን መዝገቡንዘግተን ወደ መ/ቤት መልሰናል፡፡
የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

የሀሣብ ልዩነት
እኔ በአምስተኛው ተራ ቁጥር የተሰየምኩት ዳኛ በመጀመሪያ ተጠሪዎች ክርክር የተነሳበትን ቤትና ቦታ በከፍተኛ 3 ቀበሌ 53 ፍርድ ሸንጎ ውሣኔ መሠረት መያዛቸውን አንስተው የተከራከሩ በመሆኑና አመልካችም በበኩሉ ተጠሪዎች ኪራይ እንዲከፍሉ ሚያዝያ 5 ቀን 1981 ዓ.ም. በቀበሌ ሸንጎ አስወስኛለሁ የሚል ክርክር ያለው በመሆኑ የቀበሌ ፍርድ ሸንጎ ጥር 26 ቀን 1973 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔና ሚያዝያ 5 ቀን 1981 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ በመመርመር ተገቢውን ውሣኔ ለመስጠት ይህ ሰበር ችሎት በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቶ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት መዝገቡ አልተገኘም የሚል ምላሽ የቀረበ ሲሆን እነዚህን አመልካችም ሆነ ተጠሪዎች የፍርድ ባለ መብት ሁነንባቸዋል የሚላቸውን ውሣኔዎች
በማግኘት የሚያስችል ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ መስጠቱን በአዋጅ ቁጥር 47/1967 በተሰጣቸው ስልጣን መሠረት የቀበሌ ሸንጎዎች የሰጡት አስገዳጅ ውሣኔ መኖር አለመኖሩን በማጣራት ለጉዳዩ እልባት መስጠት ይገባ ነበር፡፡ ይህ ሣይደረግ መዝገቡ አሁን ባለበት ሁኔታ መርምሮ ውሣኔ መስጠቱ፣ ተገቢ አይደለም የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የአንድ ቦታና ንብረት ሕጋዊ ባለይዞታ መሆኔ በፍርድ ይረጋገጥልኝ የሚል ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም ወይም በፍርድ ቤት ከስ ሊቀርብበት ውሣኔ ሊሰጥበት የሚችል /Justicable/ አይደለም የሚለውና የአብላጫው ድምጽ መደምደሚያ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቲም ይዞታን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት የመስጠት ስልጣን የአስተዳደር አካላት መሆኑ የማይካድና የይዞታ የምስክር ወረቀትም በአስተዳደር ደንብ መሠረት መከናወን ያለበት መሆኑ ያማያከራክር ቢሆንም የሕጉን ሥርዓትና ደንቡን ያሟላ ባይዞታዎች በአስተዳደር በኩል የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ጠይቀው አላግባብ ቢከለከሉ ይህንንም እስከ መጨረሻው አስተዳደራዊ እርከን ድረስ ለማሣረም ሞክረው የይዞታ የምስክር ወረቀት አታገኙም ተብሎ ቢወስንባቸው ይህንን አስተዳደራዊ ውሣኔ በመቃወም ሕጉንና ደንቡን አሟልተው በቦታው ላይ የሚገኙ ሕጋዊ ባለይዞታዎች መሆናቸውን በፍርድ እንዲረጋገጥላቸው ከመጠየቅ የሚገድባቸው ሕግ የሌለ በመሆኑ ጉዳዩ የክስ ምክንያት የለውም በሚለው መደምደሚያ ባለመስማማት ከሙያ አጋሮቼ በሀሣብ ተለይቻለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረትና ቦታ ሕጋዊ ባለይዞታ መሆኔ በፍርድ ይረጋገጥልኝ የሚለው ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባል ከሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1168 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት አንድ የማይነቀሳቀስ ንብረት በይዞታቸው ሥር በማድረግ ለአስራ አምስት ዓመት ግብር እየገበሩ የኖሩ ሰዎች አስተዳደሩ ለአስራ አምስት ዓመት የቦታውና የንብረቱ ባለይዞታ መሆናቸውን እና
በስማቸው ግብር መክፈላቸውን የሚያረጋግጥ የይዞታ የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ባይቀርብላቸው ይህንን በማስረጃ በማጣራት ፍርድ ቤቱ የንብረቱ ባለይዞታ ብቻ ሣይሆኑ የንብረቱ ባለቤት መሆናቸውን በፍርድ እንዲያረጋግጥላቸው የሚያቀርቡትን ጥያቄ በፍርድ ቤት ሊወሰን አይችልም በሚል መንገድ፣ የሚዘጋበት የሕግ አተረጓጎም እና መደምደሚያ የሚያስከትል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1168 ንዑስ አንቀጽ 1 የተረጋገጠላቸውን መብት በአስተዳደር አካላት ቢጣስ በፍርድ ቤት ክስ አቅርበው መብታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ መታየት አለበት የሚል ሀሣብ አለኝ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ ከዚህ በፊት ስልጣን ባላቸው አካላት ታይቶ የተወሰነ መሆኑን ተከራካሪዎቹ ካደረጉት ክርክር ለመረዳት የሚቻል ሲሆን፣ ይህ ችሎትም እነዚያን ውሣኔዎች ይዘትና ምንነት በመመርመር ለመወሰን የሚያስችለውን ሥርዓት መከተል ነበረበት፡፡ በሌላ በኩል የይዞታ መብት ጥያቄና ይዞታን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የማግኘት ጥያቄ በባሕሪው በፍርድ ቤት የማይታይና ክስ የማይቀርብበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አስተዳደሪዊ መፍትሔዎችን አሟጥጦ የጨረሰ ሰው እስከመጨረሻው እርካን ድረስ ባለው አስተዳደራዊ መዋቅር የተሰጠው ውሣኔ ሕጋዊ የይዞታ መብቴ እውቅና የማይሰጥና መብቴን የሚሸራርፍ ነው ብሎ ሲያስብ በበቂ ማስረጃ ለፍርድ ቤቶች ክስ ማቅረብና የቦታውና የነብረቱ ሕጋዊ ባለ ይዞታ መሆኑን፣ በፍርድ እንዲረጋገጥለት መጠየቅና ፍርድ ቤቶችም ጉዳዩን አይተው ለመወሰን የዳኝነት ስልጣን አላቸው በማለት አብላጫው ድምጽ ከሰጠው የሕግ ትጉምና ከደረሰበት መደምደሚያ በሀሣብ ተለይቻለሁ፡፡

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

ነ/ዓ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s