ከስራ የሚያሰናብት ጥፋት


የመ/ቁ. 47334

የካቲት 24 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

ዳኞች፡– ተገኔ ጌታነህ

መንበረፀሐይ ታደሰ

ሂሩት መለሠ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡– ሲዳርታ ዴቨሎÝመንት ኢትዮያ ሥ/አስኪያጅ ፍሬው ገ/ዮሐንስ    ቀረቡ

ተጠሪ፡– አቶ አሸናፊ ከበደ – ቀረቡ

ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው ስራ ክርክርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ተጠሪ ለፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ አመልካች አለአግባብ ከሥራ ስላሰናበታቸው የተለያዩ ክፍያ ከፍሎ ወደ ስራ እንዲመልሣቸው ካልሆነ ሌሎች ተጨማሪ ክፍያ ከፍሎ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡ አመልካች በሰጠው መልስ ተጠሪ ከስራ የተሰናበቱት የተለያየ ጥፋት ፈጽመው ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ በድጋሚ ጥፋት በመፈፀማቸው ስለሆነ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱም ተጠሪ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ከስራ ቀሩ የተባለ ቢሆንም በስራቸው ላይ አንድ ቀን መቅረታቸው ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ስለማያሰናብታቸው ስንብቱ ሕገ-ወጥ ነው በማለት ተጠሪ ወደስራ ከሚመለሱ ይልቅ የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው ከስራ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ አመልካች ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው ፍ/ቤቱ የስር ፍ/ቤትን ውሣኔ አጽንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሣኔ ላይ ነው፡፡ አመልካች በቅሬታው ተጠሪ አስቀድሞ ለፈፀሙት ጥፋት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላም ድጋሚ ጥፋት መፈፀማቸው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 መሠረት ከስራ የሚያሰናብታቸው በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ብሏል፡፡ ችሎቱም ስንብቱ ሕገ-ወጥ ነው በሚል የተሰጠውን ውሣኔ አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በማለቱ ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም መዝገቡን መርምሯል፡፡

አመልካች የተጠሪ የስራ ውል የተቋረጠው ተጠሪ ጥፋት ፈጽመው በመገኘታቸው ከደሞዛቸው 2ዐ% ተቀጥተው እና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በድጋሚ ከስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው መሆኑን ገልፆ ስንብቱ በአዋጁ አንቀጽ 28 መሠረት ሕጋዊ ነው በማለት ይከራከራል፡፡አመልካች የጠቀሰው ድንጋጌ በማስጠንቀቂያ ስራ ውል የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች የሚዘረዝር ነው፡፡ አመልካች የተጠሪ ሁኔታ በድንጋጌው በየትኛው ንዑስ አንቀጽ ስር እንደሚወድቅ ባይገልጽም ክርክሩ ተጠሪ ተቀጥተው በድጋሚ ከስራ መቅረታቸው ለስራው ብቁ አለመሆናቸዉን ያመለክታል የሚል በመሆኑ አግባብነት አለው የሚለው ንዑስ አንቀጽ አንድን መሆኑን ተረድተናል፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ ሰራተኛው ስራውን ለመስራት ተፈላጊው ችሎታና እውቀት ሣይኖረው ሲቀር ተፈፃሚ የሚሆን እንጂ ሰራተኛው ከስራ ሲቀር ተፈፃሚ የሚሆን አይደለም፡፡ አንድ ሰራተኛ በስራ መቅረት ከስራ ሊሰናበት የሚችለው በአዋጅ አንቀጽ 27/1/ለ/ መሠረት ነው፡፡ ተጠሪ ከስራ ቀሩ የተባለው ደግሞ ለአንድ ቀን ብቻ እንጂ ለ5 ተከታታይ ቀናት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በህብረት ስምምነታቸው ላይ ተጠሪ ቀደም ሲል ለፈፀሙት ጥፋት ከተቀጡ በኋላ ለአንድ ቀን ከስራ መቅረት ከስራ እንደሚያሰናብት የተቀመጠ ነገር ስለመኖሩ አመልካች አለማስረዳቱን የስር ፍ/ቤቶች አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም ተጠሪ ቀደም ሲል ጥፋት አጥፍተው ከተቀጡ በኋላ በድጋሚ ለአንድ ቀን ከስራ መቅረታቸው በአዋጁም ሆነ በሕብረት ስምምነቱ የሥራ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችል ባለመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ማለት ስላልተቻለ ተከታዩ ውሣኔ ተሰጥቷል፡፡

ው ሣ ኔ

1.                  የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 13938 መጋቢት 21 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ እና የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 79239 ሐምሌ 2 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡

2.                  ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ፡፡

3.                  ይህ ችሎት ነሐሴ 4 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም የሰጠው የዕግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡

ለሚመለከተው ክፍል ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ተ.ወ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s