የስራ ውል ፀንቶ ስለሚቆይበት ጊዜ


የሰበር መ/ቁ 46275

የካቲት 11 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሒሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

አመልካች፡- የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት – ነ/ፈጅ አንዳርጋቸው በየነ ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡- አቶ አለባቸው መሐመድ ቀረቡ፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ጉዳዩ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 337/96 ‘ን’ መሠረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በአሁኑ ተጠሪ ላይ ጥቅምት 10 ቀን 2001 ዓ.ም በመሠረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም፡- በተጠሪ ድርጅት ውስጥ ከሚያዝያ 01 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ መስከረም 25 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ ለስድስት ወራት ለተወሰነ ጊዜ በተደረገ የስራ ውል ተቀጥረው ከሰሩ በኋላ በቀጣይነት ያለ ውል እስከ ጥቅምት 06 ቀን 2001 ዓ.ም ስራ መስራታቸውን በዚህም ወቅት በሕመም ላይ ስለነበሩ ድርጅቱ ሰራተኛነታቸውን በመቀበል ለሕክምና ወደ ድርጅቱ ክሊኒክ በመላክ ሕክምና እንዲያገኙ ያደረጋቸው መሆኑን ሆኖም የሰሩበትን ደመወዝ ለመቀበል ሲሄዱ ውሉ ሳይታደስ ደመወዝ አይከፈልም በሚል መከልከላቸውን ገልፀው የውል ጊዜው ከአለፈ በኋላ አስራ አንድ  ቀናትን ያህል ስለሰሩ ቋሚ ልሆን ሲገባ የላግባብ ሳልሆን ስለቀረሁ ቋሚ እንድሆን ይወሰንልኝ የሚል ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ድርጅትም በተከሳሽነቱ  ቀርቦ ተጠሪ የውል ጊዜ ካለቀ በኋላ የሰራው የአመልካችን ፈቃደኝነትን ሳያገኝ መሆኑን የስራው ፀባይ ቀጣይነት የሌለውና በቦታው ከተንዳሆ እርሻ ልማት አክሲዮን ማህበር የተረከባቸው ቋሚ ሰራተኞች እንደመደበ ከተጠሪ ጋር ያደረገው የስራ ውል ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ በመሆኑ ውሉ የተቋረጠው በሕጉ አግባብ መሆኑን ገልፆ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የዱብቲ ወረዳ ፍርድ ቤትም የአመልካችን ክርክር ውድቅ ከአደረገ በኋላ ስራው ቀጣይነት ያለው በመሆኑ አመልካች ተጠሪን ከመስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ቋሚ ሰራተኛ እንዲያደርጋቸው ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለአውሲረሱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀንቷል፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረ ፈጅ ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሦስት ገጽ የሰበር አቤቱታ በስር ፍረድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝርው አቀርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪ ለተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩና ፕሮጀክቱ በማለቁ የተሰናበቱ ሁኖ እያለ ቋሚ እንዲሆኑ መወሰኑ ከስራ ውሉ ይዘትና ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 24 ድንጋጌ ውጩ በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የፕሮጀክቱ አንድ ክፍል ስራ ብቻ አልቋል በማለት የተጠሪን የስራ ውል ማቋረጥ ሕገ ወጥ ነው የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጐ ተጠሪ ህዳር 10 ቀን 2002 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ የጽሁፍ ማመልከቻ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ተገቢነት በመዘርዘር ሊፀና ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅም ታህሳስ 05 ቀን 2002 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙኙ ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ የስራ ውሉ ለስድስት ወር የተደረገ ስለመሆኑ እና የተቀጠሩበት ፕሮጀክት ማለቁን ሳይክዱ የሚከራከሩት ለስድስት ወር ጊዜ ማለቅ በኋላ ለአስራ አንድ  ቀናት መስራታቸው ውሉ መታደሱን ያሳያል ስራውም የዘላቂነት ባሕርይ ያለው ነው በሚል ሲሆን አመልካች በበኩሉ ተጠሪ የተቀጠሩበት ፕሮጀክት ማለቁ እስከተረጋገጠ እና ውሉ በአመልካች ፈቃኝነት እስከአልታደሰ ድረስ ስንብቱ ሕገ ወጥ ሊባል የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም በሚል የሚከራከር መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ተጠሪ የተቀጠሩት ለተወሰነ ስራ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ አከራካሪው በውሉ ላይ የተመለከተው ጊዜ ካለቀ በኋላ ተጠሪ ስራውን መስራታቸው የስራ ውሉ መታደሱንና ተጠሪ በቋሚነት መቀጠራቸውን የሚያሳይ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ የተቀጠሩበት የፕሮጀክቱ አንዱ ክፍል ማለቁን አረጋግጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተጠሪ ከዚህ የፕሮጀክቱ አንድ ክፍል ማለቅ በኋላ ከአመልካች ጋር በሕጉ አግባብ ያደጉት የስራ ውል ስለመኖሩ አላስረዱም፡፡ በመሆኑም ተጠሪ ከአመልካች ጋር የነበራቸው የስራ ውል በአዋጅ ቁጥር

377/96 አንቀጽ 10(1(ሀ) መሠረት ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ የስራ ውል እንጂ በቋሚነት የተደረገ አይደለም፡፡ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የነበረው የስራ ውል ጊዜያዊ ነው ከተባለ ደግሞ ስራው ፕሮጀክት መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ለክርክሩ አግባብነት ያለው የአዋጁ አንቁጽ 24(1) ድንጋጌ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የፕሮጀክቱ ስራ ሲጠናቀቅ ሰራተኛውን አሰሪው ቢያሰናብተው ስንብቱ ሕጋዊ ነው፡፡ ስለሆነም የስር ፍርድ በቶች የፕሮጀክቱ አንድ ክፍል ስራ ብቻ አልቋል በማለት የተጠሪን የስራ ውል ማቋረጥ ሕገ ወጥነው በማለት የሠጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሳ ኔ

1.   በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዱብቲ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 0091/2001 ጥር 7 ቀን 2001 ዓ.ም ተሠጥቶ በአውሲረሱ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 1458 ግንቦት 14 ቀን 2001 ዓ.ም የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2.   አመልካች እና በተጠሪ መካከል የነበረው የስራ ውል የተቋረጠው በአዋጁ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 24(1) መሠረት በሕጉ አግባብ ነው ብለናል፡፡

3.   ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s