የማስረጃ አግባብነትና ተቀባይነት-የፍርድ ቤቶች ሚና (የሰበር ውሳኔ)


የሰበር መ.ቁ. 39538

መጋቢት 21 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

ዳኞች፡-

ተገኔ ጌታነህ

ሂሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር – የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- አቶ ዮናስ ውብሸት – ባለቤታቸው ቀርበዋል

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ በስራ አጋጣሚ ወደ እጅ የገባ ንብረት ጉድለት ግምት የሆነው ገንዘብ ይተካልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ የካቲት 19 ቀን 1995 ዓ.ም በመሠረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ ተጠሪ የአመልካች መሥሪያ ቤት መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች መጋዘን ኃላፊ ሁነው ሲሰሩ ከተረከቡት የሕክምና መገልገያ መሣሪያና መድኃኒት መካከል ግምቱ ብር 217,985.66 /ሁለት መቶ አስራ ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስድስት ብር ከስልሣ ስድስት ሣንቲም/ የሆነ ንብረት ማጉደላቸውን ጉድለቱም በመሥሪያ ቤቱ ኦዲተር ምርመራ ተደርጎ መረጋገጡን ገልጾ ተጠሪ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ገንዘብ ከእነ ሕጋዊ ወለድ እንዲሁም ከወጪና ኪሣራ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሣይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪም ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስ የተረከቡት መድኃኒት አለመኖሩን ግምቱ 227,341.ዐዐ /ሁለት መቶ ሃያ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ አርባ አንድ ብር/ የሆነ መድኃኒት ወደ መጋዝኑ ተጠሪ በተመደቡበት ነሐሴ 19 ቀን 199ዐ ዓ.ም ቁጥራቸው አስራ ስድስት በሆኑ ሰዎች በግብረአበርነት ተሰርቆ እንደተወሰደ ተረጋግጦ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው መሆኑን ንብረቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት የአመልካች መሆኑና ተጠሪ ንብረት የተረከቡና ጉድለት አለ ብለው የፈረሙት መተማመኛ የሌለ መሆኑን በመዘርዘር ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር እና በአመልካች በኩል የቀረቡትን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን በመመርመር አመልካች ክሱን አላስረዳም የሚል ምክንያት በመያዝ ተጠሪን ከክሱ ሙሉ በሙሉ ነፃ አድርጎ ወስኗል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የስር ፍርድ ቤትን ውሣኔ አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረፈጅ ሐምሌ 22 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪ የሚረከቡትን ንብረት በገቢ እንዲመዘግቡ አስቀድሞ 11 ጥራዝ ሞዴል 19 የተረከቡ ለመሆናቸው መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ መሣሪያ መረከባቸውን የንብረት ገቢ መመዝገቢያ ሞዴል ባይቆርጡ ለተረከቡት ንብረት ጉድለት ኃላፊ መሆናቸውን ይኸው የተረከቧቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያ በተደጋጋሚ ተቆጥሮ የብር 217,986.66 ግምት ያለው በጉድለት መታየቱን የሚያሣዩ ማስረጃዎች ቀርበው እያለ ማስረጃ አልቀረበም ተብሎ መወሰኑ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ስለሆነ ታርሞ ለክሱ መነሻ የሆነውን ገንዘብ ተጠሪ እንዲከፍሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል ተብሎ ተጠሪ ቀርበው የአመልካችን የሰበር አቤቱታ በመንቀፍ የስር ፍርድ ቤትን ውሣኔ ተገቢነት በመግለጽ ውሣኔው መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ሲሉ ሐምሌ 14 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ ማመልከቻ ተከራክረዋል፡፡ የአመልካች ነገረፈጅም በበኩላቸው ሐምሌ 23 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም በፃፉት ሦስት ገጽ ማመልከቻ የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሉትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ተጠሪ ኃላፊነት የለባቸውም ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካች መስሪያ ቤት የመጋዝን ኃላፊ ሁነው ሲሰሩ የነበረ መሆኑን በመጋዝኑ ኃላፊ ሁነው ከተረከቧቸው ንብረቶች ውስጥ ለክሱ ገንዘብ መሠረት የሆኑት ንብረቶች መጉደላቸው በአመልካች መሥሪያ ቤት ኦዲት ምርመራ መረጋገጡን የኦዲት ሂሣብ ምርመራ ውጤት መኖሩን ተጠሪ ሣይክዱ የሚከራከሩት ንብረት አለመረከባቸውን ጉድለት አለብኝ ብለው አለመፈረማቸውን ገልፀው መሆኑን ነው ሌላው ተጠሪ አጥብቀው የሚከራከሩት ንብረቶቹ በስርቆት ድርጊት ከመሥሪያ ቤቱ መውጣታቸው ተረጋግጦ ተጠሪ ላይ ዐቃቤ ሕጉ የመሠረተው ክሱ ሲቋረጥ ከተጠሪ ጋር ባንድ ላይ በተከሰሱት ሌሎች ሰዎች የቀረበው የወንጀል ክስ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ሲሆን የፍትሐብሔር ክሱን በተጠሪ ላይ አመልካች ሲመሠርትም ለመከላከያ ማስረጃነት የቆጠሩት የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪን ከክሱ ኃላፊነት የለባቸውም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰውም የአመልካች የሰነድ ማስረጃዎች ሲታዩ ተጠሪ ለክሱ ምክንያት የሆነው ንብረት ስለመረከባቸውና ይህንኑ ንብረት ስለማጥፋታቸው የሚያስረዱ ካለመሆናቸውም በላይ ተጠሪ ንብረቱን መረከባቸውን ንብረቱን ማጉደላቸውን ወይም ለጉድለቱ የተገኘባቸው መሆኑንና ኃላፊነት አለብኝ በማለት መተማመኛ የፈረሙባቸው አይደሉም የወንጀል ክሱም በሌሎች ሰዎች እንዲቀጥል ሲደረግ በተጠሪና በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ግን እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ የቀረቡትም የሰው ምስክሮችም ስለንብረቱ መጉደል የማያውቁ ናቸው የሚሉትን ምክንያቶችን በመያዝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክሱ መነሻ የሆነው ንብረት ግምት በጉደለት መገኘቱን የአመልካች የሰነድ ማስረጃዎች ይዘትም ሆነ የሰው ምስክሮች ቃል ሲታይ የሚያስረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በእነዚህ ሰነዶት ተጠሪ መተማመኛ ፊርማ አለመስጠታቸው የሰነዶችን ማስረጃነት ዋጋ የሚያጣ አለመሆኑን ከአጠቃላይ የሂሣብ ምርራ ደንቦች የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ተጠሪ በወንጀል የቀረበባቸው ክስ እንዲቋረጥ መደረጉም የፍትሐብሔር ተጠያቂነት የሚያስቀር አይደለም፡፡ በመሆኑ የአመልካችን የሰነድና የሰው ምስክሮች ይዘት የስር ፍርድ ቤቱ ባግባቡ ሣይመለከት አመልካች ክሱን በማስረጃዎቹ አላስረዳም በማለት ማስረጃዎቹን ዋጋ ማሣጣቱ የፍትሐብሔር ጉዳይ ማስረጃ የሚቀርብበትንና የሚመዘንበትን መርህ መሠረት ባላደረገ መልኩ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ የስር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የደረሰበት ድምዳሜም ሆነ የፈዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንኑ ሣያርም በማለፍ ውሣኔውን ማጽናቱ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ሁኖ አግኝተናል፡፡

በአመልካች በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ተጠሪ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑት ንብረቶችን አጉድለው መገኘታቸውን የሚያሣዩ ናቸው፡፡ ተጠሪ በስራ አጋጣሚ ወደ እጃቸው የገቡትን ንብረቶችን ማጉደላቸው ከተረጋገጠ የሕጉ ግምት ጉድለቱ ለተጠሪ ጥቅም ወይም ለሌላ ግለሰብ ስለመሆኑ ከማስረጃ ሕጉ አጠቃላይ መርሆዎች የምንገነዘበው ጉዳይ ነው አንድ ንብረቱን በስራ አጋጣሚ አስገብቶ ጉድለቱ የተገኘበት ሠራተኛ ከኃላፊነት ሊድን የሚችለው ይህንኑ የሕጉን አጠቃላይ ግምት ማስተባበል ሲችል ነው፡፡ ተጠሪ የንብረቶቹን መጉደል በተመለከተ በአማራጭ ባቀረቡት ክርክር ንብቶቹ በስርቆት ወንጀል ተዘርፈው ስለጠፉ ኃላፊነት የለብኝም በማለት ገልፀዋል፡፡ ይህንኑ ለማስረዳትም ከላይ እንደተገለፀው የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ በፍርድ ቤት እገዛ በማስረጃነት እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህም ከተጠሪ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ምክንያት ንብረቶቹ ጠፍተዋል በማለት ተጠሪ የሚከራከሩ መሆኑን የሚያሣይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የስር ፍርድ ቤት በተጠሪ በኩል በማስረጃነት የተቆጠረውን የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ አስቀርቦ ለማስረጃነት ያለውን ዋጋ በመመልከት የግራ ቀኙን ክርክር አልዳኘም፡፡ ተጠሪ በማስረጃነት የቆጠሩት የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ መቅረብ የፍርዱን አካሄድ የተሟላ የሚያደርግ መሆኑን ይህ ችሎት ስለተገነዘበ የስር ፍርድ ቤት ይህንኑ የተጠሪ ማስረጃ በማስቀረብ እና ተገቢውን ሁሉ ማጣራት በማድረግ ጉዳዩን እንደገና በማየት እንዲወስን ማድረግ ተገቢ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ ሲጠቃለልም ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁ. ዐ9ዐ73 ሰኔ 13 ቀን 1999 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 3ዐ76ዐ ሚያዚያ 24 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡

2. የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተጠሪ በኩል ለማስረጃነት የተቆጠረውንና በጉዳዩ ላይ የተጣራውን የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ በማስቀረብ እና ተገቢ ነው ያለውን ሁሉ በማጣራት ጉዳዩን እንደገና አይቶ ተገቢውን ውሣኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343/1/ መሠረት መልሰንለታል፡፡ ይፃፍ፡፡

3. እስካሁን ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ተ.ወ

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s